1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሣሣቂው ጋዝ ፣ፕላኔታችንን አስለቃሽ እንዳይሆን!

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 4 2001

አሣሣቂው ጋዝ፣(Laughing Gas) የሥነ ቅመማ (ኬሚስትሪ)ጠበብት በሳይናሳዊ ስሙ፣ Nitrous Oxide(N2O)በሚል ነው የሚያውቁትም ሆነ የሚጠሩት። ከዚሁ ጋር በጠቅላላ 5 ቱን የታወቁ የናይትሮጂን ቅልቅል ንጥር ነገሮች በቤተ-ሙከራ ማግኘት ይቻላል።

https://p.dw.com/p/JZ5w
በአንታርክቲካ ፣ የተሸነቆረው የኦዞን ሽፋን ፣ምስል AP

እነርሱም፣ አሁን እንዳልነው ናይትረስ ኦክሳይድ፣ ናይትሪክ አክሳይድ፣ ናይትሮጂን ትራይኦክሳይድ፣ ናይትሮጂን ፔንቶክሳይድና ናይትሮጂን ፔሮክሳይድ ናቸው። ናይትረስ ኦክሳይድ የተሰኘውን ቀለም-የለሽና ከሞላ ጎደል ደስ የሚል መዓዛ ያለው ጋዝ፣ እ ጎ አ በ 1772 ዓ ም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው ፣ ጆሰፍ ፕሪስትሊ የተባለው እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ነው። ከዚያም ሩብ ምዕተ-ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ፣ ከ 200 ዓመት ገደማ በፊት ሌላው ታዋቂው አንግሊዛዊ ሳይንቲስት ሃምፍሬይ ዴቪ፣ የተወሰነ መጠን ካለው ኦክስጂን ጋር በመቀላቀል የሚገኘው ጋዝ፣ ሲተነፍሱት ሣቅ በሣቅ የሚያደርግ፣ በደስታ የሚያስፈነድቅ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን አረጋገጠ። በመሆኑም «አሣሣቂ ጋዝ» የተሰኘውን ስያሜ አገኘ። ይህን ጋዝ (ናይትረስ ኦክሳይድ) የጥርስ ሃኪሞች፣ በጥርስ ህመም ሳቢያ የሚሠቃዩ ሰዎችን ለማከም፣ በማደንዘዣነት ይጠቀሙበታል። ናይትረስ ኦክሳይድ፣ ለተወሰነ ጊዜ እንቅልፍ የማስወሰድ ባኅርይም ያለው ነው። የሚመረተው፣ ልክ ከ 200 ዓመት ገደማ በፊት ሳይንቲስቱ ሃምፍሪ ዴቪ እንዳደረገው ሁሉ በአሁኑ ዘመንም ቢሆን፣ በተመሳሳይ ዘዴ ነው። ቤተ-ሙከራ ውስጥ፣ በጥንቃቄ፤ Ammonium Nitrate ን በ 200 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ የሙቀት ኃይል ሲያግሉት ንጥር ነገሩ ወደ ናይትረስ ኦክሳይድና የውህ እንፋሎትና ተን ይለወጣል።

የናይትረስ አክሳይድ ለማግኘት በቤተ-ሙከራ እርምጃ ሲወሰድ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። የናይትሮጂን ቅልቅል እንዳለባቸው ንጥረ- ነገሮች ሁሉ፣ «አሞኒየም ናይትሬት» ም ፣ በንጽጽር አስተማማኝ አይደለም። ሌላ ተጨማሪ ንጥር ነገር ትንሽም ቢሆን የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። አለበለዚያ ግን በዚህና ወይም ከመጠን በላይ ሲሞቅ፣ ፍንዳታ ሊያስከትል ይችላል።

«አሣሣቂው ጋዝ»፣ ናይትረስ ኦክሳይድ ፣ ከአካባቢ ጥበቃ አኳያ፣ በአሁኑ ዘመን «አስለቃሹ ጋዝ » ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጠበብት አሁን እንደሚሉት ፣ ከፀሐይና ከሌሎችም ከዋክብት ወደ ምድራችን የሚፈነጥቁ አንዳንድ እጅግ አደገኛ ጨረሮችን በከባቢ አየር እርከን ላይ እንደ ጋሻ ሆኖ የሚከላከለውን ፣ «ኦዞን» ፣ በማውደም ፣ ናይትረስ አካሳይድ ወደር አልተኘለትም። «አሣሣቂው ጋዝ ፣ አሁን «ኦዞን ገዳይ» የሚል ሥም አግኝቷል። አጣዳፊና ጥብቅ እርምጃ ካልተወሰደም ፣ እ ጎ አ እስከ 2050 ዓ ም፣ የናይትረስ አካሳይድ፣ ኦዞን አውዳሚነት፣ 50 ከመቶ ከፍ ማለቱ አይቀርም።

ምድራችን ፣ ከአፈር፣ ቋኝና ውሃ አካሏ አንስቶ ፣ በቅርበት ያለው አካባቢዋ በ 4 የተያያዘ የአየር እርከን ይከፈላል። መላዋን ፕላኔት ከጠጣር አለትም ሆነ ቋጥኝ ጋር የከበባት ሊቶስፌር የተሰኘው ነው።

ሊቶስፌር፣ ከ«ማውንት ኤቨረስት» ማለትም (ከምድራችን እጅግ ከፍተኛው ተራራ አንስቶ እስከ የመጨረሻው የውቅያኖስ ጥልቀት(በሰላማዊው ውቅያኖስ፣ ማሪያና ሰርጓዳ ቦታ ድርስ ያለውን ያጠቃልላል። )

ሃይድሮስፌር፣የምድራችንን ወሃ ፣ ውቅያኖስ ሃይቅና የመሳሰለውን በውስጡም ያለውን ህይወት ይመለከታል። b

ባዮስፌር፣ ከየብስ 3 ሜትር ጥልቀት አንስቶ ከየብስ በላይ 30 ሜትር ከፍታ ድረስ፣ ከባህር ልክ በላይም 200 ሜትር ከፍታ ድረስ ያለውን ያካትታል።

አትሞስፌር፣ ፕላኔታችን ን ዙሪያዋን የከበበው አየር ነው። 4 ቱ መሠረታዊ የምድር እርከን ስሞች ከግሪክኛ የተወሰዱ ሲሆን፣ ሊቶ =ድንጋይ፣ ሃይድሮ=ውሃ፣ ባዮ=ህይወት፣

አትሞ=አየር ማለት ነው።

ከዚሁ ከአትሞስፌር በላይ ደግሞ 5 የአየር--የደመና እርከኖች አሉ።

ትሮፖስፌር፣ በምድር ዋልታዎች ከ የብስ እንዲሁም ከባህር ልክ አንስቶ 7 ኪሎሜትር ፣ በምድር ሰቅ ደግሞ 17 ኪሎሜትር ከፍታ ድርስ ያለውን ይሸፍናል። ትሮፖስፌር አብዛኛውን ጊዜ፣ ከምድር የላይ አካል በሚነሳ የጋለ አየር ወይም ተን የሚሞቅ ሲሆን ከፍታው እየጨመረ ሲሄድ ይቀዘቅዛል።

እስትራቶስፌር፣ 51 ኪሎሜትር ድርስ ይዘልቃል።

እንግዲህ Ozone የተባለው ፕላኔታችንን ከአደገኛ ጨረሮች ጋሻ ሆኖ የሚከላከለው የአየርም ሆነ የጋዝ እርከን የሚገኘው፣ ከምድራችን ከፍ ብሎ በ 17 እና -51 ወይም በ 16 እና 48 ኪሎሜትር መካከል ላይ ነው።

ሞሶስፌር፣ በ51 ኪሎሜትር ገደማ አንስቶ 80፣ 85 ኪሎሜትር ድረስ ይዘልቃል። በፕላኔታችን ዙሪያ እጅግ ቀዝቃዛው ክፍልሜሶስፌር ሲሆን በአማካዩ ከዜሮ በታች የ 100 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ አለው።

ቴርሞስፌር ፣ ከሜሶስፌር ቀጥሎ ያለው የአየር እርከን ሲሆን በዚህ ቦታ ሙቀቱ 1,500 ድርስ ከፍ ሊል ይችላል። ዓለም አቀፉ የኅዋ ጣቢያ ምኅዋሩን ጠብቆ የሚሽከረከረው በ 320 እና 380 ኪሎሜትር ርቀት በ ቴርሞእስፌር እርከን ነው።

ኤክሶስፌር፣ ይህ ከቴርሞእስፌር ቀጥሎ ከ 350 እስከ 800 ኪሎሜትር ያለውን እርከን የሚይዝ ነው። የኤክሶስፌር አየር በአመዛኙ በሃይድሮጂንና ሄሊየም ጋዞች የተመላ ነው።

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኦዞን እርከን የሚገኘው በእስትራቶስፌር ነው።

እ ጎ አ በ 1970ኛዎቹ ዓመታት ፍጻሜ ላይ የኦዞን ዋናው ጠንቅ የክሎሪን፤ ፍሎሪንና ካርበን ውሁድ ንጥር (ክሎሮፍሉዎሮካርበንስ)CFC ነው ተብሎ ዘመቻ ተጀመረ CFC እ ጎ አ በ 1928 ዓ ም የማቀዝቀጃ ዋና አንቀሳቃሽ ንጥር የነበረውን አሞንያን እንዲተካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካዊው ኢንጂኔር ቶማስ ሚድግሊ የተቀናበረ እንደነበረ አይዘነጋም።

እ ጎ አ በ 1987 ዓ ም፣ የሞንትሪአል ፕሮቶኮል በተሰኘ ስምምነት መሠረት «ኦዞን-ገዳዩ» CFC እንዳይመሠረት፣ ተወሰነ። በካባቢ አየር የኦዞን መሸንቆር እንደሚያገግምም ምልክት ታዬ። ይሁን እንጂ ከዚሁ CFC እጅግ በከፋ መልኩ ለኦዞን ጠንቀኛ የሆነ ጋዝ መኖሩ ሳይውል-ሳያድር፣ ግንዛቤን አስጨበጠ። በዩናይትድ እስቴትስ፣ የአየር ንብረትና የውቅያኖስ ይዘት ምርምር ባልደረባ ራቪ ራቢሻንካራ እንዲህ ይላሉ።

«ናይትረስ ኦክሳይድ፣ ኦዞንን የሚያሟጥጥ ኃይል እንዳለው በስሌት የደረስንበት ጉዳይ ነው። ይህ የሚያሳየው፣ ዩናይትድ እስቴትስ፣ የናይትረስ ኦክሳይድ መለቀቅ፣ በአሁኑ ጊዜ ዋንኛው የኦዞኑ አውዳሚ መሆኑን ነው። ናይትረስ ኦክሳይድን ለመግታት በቀጣዩ ማዕተ-ዓመት እጅግ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።»

የዚህ ጠንቀኛ ጋዝ ጭማሪ መጠን ምን ያህል እንደሆነና እንዴትም ሊጨምር እንደቻለ ራቪ ራቪሻንካራ ሲያስረዱ-

«በአጠቃላይ ፣ በያመቱ የአንድ ከመቶ ሩብ ጭማሪ አለ። ለናይትረስ ኦክሳይድ መስፋፋት መንስዔው ፣ በተለይ የሰዎች የግብርና እንቅሥቃሤ ነው። አፈር ለማደበሪያ ሲባል ናይትረስ ኦክሳይድ ይመረታል። ሌላው የሚቃጥል ነገር ነው። ሌሎች፣ (የዚህ ጠንቀኛ ጋዝ) ምንጮች፣ የሥነ-ቅመማ እንቅሥቃሴዎች ሲሆኑ ናይትረስ ኦክሳይድ በዚህ መልኩ ይመረታል።» ተክሌ የኋላ፣