1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማርኛ በጉግል

ረቡዕ፣ የካቲት 23 2008

ጉግል የአማርኛ ቋንቋን ከሌሎች 13 ተጨማሪ ቋንቋዎች ጋር በይፋ መተርጎም መጀመሩን ከገጠ ዛሬ ሁለት ሣምንታትን አስቆጠረ። የካቲት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጀመረው የጉግል የትርጉም ሥራ የመጀመሪያ ከመኾኑ አኳያ ስህተቶች ቢታዩበትም በጥንቃቄ የተተረጎሙ ቃላት እና ሐረጎችንም መመልከት ይቻላል።

https://p.dw.com/p/1I5An
Google Logo Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/O. Spata

አማርኛ በጉግል

በኢንተርኔቱ ዓለም ግዙፍ የሆነው ጉግል ከዚህ በፊት የትርጉም አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 90 ቋንቋዎች በተጨማሪ 13 ቋንቋዎችን መተርጎም ጀምሯል። ከሣምንታት በፊት አዲስ መተርጎም ከጀመሩት ቋንቋዎች ውስጥ የአማርኛ ቋንቋም ይገኝበታል። ጉግል የአማርኛ ቋንቋ ትርጉም አገልግሎት የሚሰጠው እንዴት ነው? የአገልግሎቱ ፋይዳስ ምንድን ነው?

ጉግል ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊት ማሽንን መሠረት ያደረገ የትርጉም ሥራ የጀመረው በአራት የዓለም ቋንቋዎች ነበር። እንግሊዝ፣ ዐረብ፣ ቻይና እንዲሁም ሩስያ ላይ ትኩረት አድርጎ የተጀመረው የጉግል የትርጉም ስራ ዛሬ አማርኛን ጨምሮ በብዛት 103 ቋንቋዎችን የሚያካትት ኾኗል። ለመሆኑ ጉግል የትርጉም ሥራውን እንዴት ነው የሚያካትተው። የመጀመሪያ እና ድኅረ ምረቃ ዲግሪያቸውን በኮምፒውተር ሣይንስ የያዙት የሶፍትዌር ዴቨሎፐር ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ አየለ።

አማርኛ ቋንቋ በጉግል የትርጉም ሥራ አገልግሎት ውስጥ መግባቱ ለቋንቋው እድገት የሚኖረው አስተዋጽዖ ላቅ ያለ ነው። የትርጉም ሥራው መጀመር የሣይንስ እና ስነ-ቴክኒክን ጨምሮ፣ የፍልስፍና እና ሌሎች ቃላት ከሌሎች ቋንቋዎች ወደ አማርኛ እንዲመለሱ ከአማርኛም ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ የሚኖረው ድጋፍ ከፍተኛ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የትርጉም አገልግሎት የመስጠት ሙያ ላይ የተሰማሩ አቶ አብርሀም ሞሼ መዝገበ-ቃላት የቆዩ በመኾናቸው አዳዲስ ቃላትን ለመተርጎም ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል። በእርግጥ የሚሻሻል ነገር ቢኖረውም እንደጅማሬ ጥሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።

አንድ ቋንቋ በጉግል የትርጉም ሥራ አገልግሎት ለማግኘት ጉግል በመሠረታዊነት ያስቀመጠው መሥፈርት ቋንቋው በጽሑፍ የሚገኝ መኾኑ ነው። ከዚያም ባሻገር በቋንቋው በርካታ ጽሑፎች የኢንተርኔቱ ዓለም ላይ ወይንም ድር ውስጥ መገኘታቸው ትኩረት እንደሚሰጠውም ጉግል በአምደመረቡ አስፍሯል። ጉግል በዋናነት ለትርጉም የሚጠቀመው በቋት ውስጥ ያከማቻቸውን ቃላት በመውሰድ ነው።

አማርኛ ከአረብኛ ቀጥሎ ዓለም ላይ በስፋት ከሚነገሩ የሴሜቲክ ቋንቋዎች ሁለተኛው ነው። በጉግል የትርጉም ስነ-ቴክኒክ ዘርፍ የሚወጡ ማናቸውንም ይፋዊ መረጃዎች የሚቆጣጠረው ጎግል መተርጎሚያ በአምደመረቡ ይኽንኑ አስፍሯል። ጉግል የትርጉም አገልግሎት ሲሰጥ ከኢንተርኔቱ ዓለም በመረጃ ቋቱ አሰባስቦ ካከማቻቸው የአማርኛ ቃላት እና ጽሑፎች በቀጥታ ይጠቀማል። የባለቤትነት መብት ያላቸው አቅርቦቶችንም አገልግሎት ላይ ያውላል። ለምሳሌ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትርጉም ለማከናወን ጉግል ወርድ ኔት የተባለውን በባለቤትነት የተያዘ የትርጉም ቋት ይጠቀማል። ከዚያም ባሻገር ማንኛውም የጉግል የኢሜል አድራሻ ያለው ሰው በአድራሻው ገብቶ መተርጎም እና የተተረጎሙትንም ማረም ይችላል።

ጥራት ያላቸው ትርጉሞች እየተበራከቱ በሄዱ ቁጥር የጉግል የአማርኛ ትርጉም አገልግሎት ጠቀሜታው እየጎለበተ ሊሄድ ይችላል። በእርግጥ የአማርኛ ሰዋሰው ከእንግሊዝኛ፣ አለያም ከጀርመንኛ አለያም ከሌሎች ቋንቋዎች የተለየ መኾኑ የትርጉም ሥራው ላይ ተግዳሮት መፍጠሩ አልቀረም።

Google Logo
ምስል picture-alliance/dpa/D.Deme
Amharisch Google-Übersetzer auf Handy
ምስል Google

ካለፉት ሁለት ሣምንታት አንስቶ በጉግል መተርጎም መጀመራቸው በይፋ የተነገረላቸው 13ቱ ቋንቋዎች አማርኛ፣ ቆሳ፣ ሾና፣ ኮርዲካ፣ ፍሪዚያ፣ ኪርጊዝ፣ ሃዋዪ፣ ኩርድ፣ ሉግዘምቡርግ፣ ሳሞዋ፣ የስኮት ጋዬሊክ፣ ሲንዲ እና ፓሽቱ ናቸው። ጉግል የአማርኛ ቋንቋን በጽሑፍ ከመተርጎሙ ባሻገርም ወደፊት በድምጽም እየተናገሩ በመቅዳት ቋንቋውን በኢንተርኔቱ ዓለም በስፋት ለመጠቀም እንዳሰበ የሶፍትዌር ዴቨሎፐር ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ አየለ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ በጉግል የትርጉም አገልግሎት ለሚሰጡት 103 ቋንቋዎች በዓለም ዙሪያ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስተዋጽዖ አድርገዋል። ወደ 200 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ ቃላትም በተለያዩ የዓለማችን ቋንቋዎች እንደተተረጎሙ ጉጉል በገጹ አስነብቧል። አማርኛ ቋንቋ በጉግል የትርጉም አገልግሎት መጀመሩ ለቋንቋው ታላቅ እመርታ ነው። አሁን የሚታዩ የትርጉም ስህተቶቹን ለመቀነስ ግን አቅሙ ያላቸው ሰዎች የጉግል ማኅበረሰብ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ