1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አልፋቤት ኢትዮጵያ» እና የያንበሊው ፕሮጀክት፣

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2003

ጥቂት ታዋቂ ድምጻውያን፤ ከ 20 ዓመት ገደማ በፊት «ሁሉም ቢተባበር ፣ የት ይደረስ ነበር!» የሚል አንድ ኅብር ዜማ አውጥተው እንደነበረ የሚታወስ ነው።

https://p.dw.com/p/RC08
ምስል Fotolia/ChaotiC_PhotographY

ሁሉም በሚወደው ሙያ ተሰልፎ ተባብሮ ቢሠራ፣ ለአገር ለወገን ሊሰጥ የሚችለውን ሰፊ ጠቀሜታ ለማስታወስ መሰለኝ ድምጻውያኑ ያን ያሉት!

እንደሚታወቀው በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ፣ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፤ በቀሰሙት ገንቢ ሙያ ፣ ራሳቸው በመሰለፍም ሆነ ሙያም ባለሙያዎችን በማስተባበር በጥቂቱም ሆነ በሰፊው ወገንን የሚጠቅም ተግባር ለማከናወን ይችላሉ። ሁኔታዎች ይበልጥ የሚያበራታቱ ከሆኑም ድጋፋቸውም ሆነ አስተዋጽዖቸው በቀላል የሚገመት አይሆንም። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፤ በዚህ በጀርመን ሀገር ከሚገኙ የተለያዩ ማኅበራት መካከል «አልፋቤት ኢትዮጵያ» የተሰኘው ድርጅት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በጉራጌ አውራጃ በተከለው ታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ ይሆናል የምናተኩረው ፣ አብራችሁን ቆዩ።

(ሙዚቃ)-------

የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት የውሃ፤ የነፋስና በከርሠ፣ምድር የሚገኝ የእንፋሎት ኃይል በሰፊው የሚገኝባት ኢትዮጵያ ፤ በሥነ-ቴክኒክ በመታገዝ፣ በአነዚህ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ለመጠቀም ተፈጥሮ ያደላት አገር ብትሆንም፣ አብዛኛው ህዝቧ ገና የዚህ የተፈጭሮ ፀጋ ተቋዳሽ ለመሆን አልበቃም። ያም ሆኖ፤ አልፎ -አልፎ፣ በአርአያነት ሊታዩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መሞከራቸውን እንሰማለን። በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፤ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድር ፣ በጉራጌ አውራጃ፤ ያንቤሊ በተባለ መንደር ፤ በአንድ ሰበካ ፣ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ኢትዮጵያውያንና ጀርመናውያን ፤ በደቡብ ጀርመን ብሩህዛል በተሰኘች ንዑስ ከተማ ባቋቋሙት አልፋቤት ኢትዮጵያ በተሰኘው ማኅበራቸው አማካኝነት ፤ በፀሐይ ኃይል፤ ኤልክትሪክ የሚያመነጭና ፤ ለትምህርት ቤት ፣ ብሎም ለአካባቢው አባዎራዎች የሚበጅ ፕሮጀክት እንዲተከልና አገልግሎት እንዲሰጥ አብቅተዋል። አልፋቤት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ማኅበር ነው? ለምን ዓላማስ ነው የተቋቋመው፤ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ኤታና ሁዋ---

(ድምፅ)------

ባለፉት 2 ዓመታት ገደማ ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙትና በያንቤሊ መንደር ለተተከለው ፕሮጀክት መሳካት ዐቢይ አስተዋጽዖ ካደረጉት ጀርመናውያን መካከል፣ የባንክ ባለሙያው ሄር ክሪስቶፍ ሄንድል ስለፕሮጀክቱ እንዲህ ይላሉ----

«እንደተመለከትኩት ከሆነ ይህ ፕሮጀክት የአካባቢውን ሰዎች ከባድ ኑሮ ለማቅለል ፣ በጎ ተግባር ማከናወን የሚችል ነው። ሳሙኤል ኤታና ሁዋ ፤ በትክክል ፣ ስለፕሮጀክቱ ጠቃሚነት አስረድቷል፤ እኔ በዚያ ፕሮጀክቱ በተተከለበት ቦታ ባገኘኋቸው ሰዎች በጣም ነው የተደነቅሁ። የእነዚህን ጨዋና የሚወደዱ ሰዎች አመኔታ በማግኘቴ(በማትረፌ) ደስ ብሎኛል፤ በቆየሁበት በያንበሊ መንደር ፣ እርካታ ነው የተሰማኝ ። ወደዚያ ተመልሼ በመሄዴም በጣም ነበረ ደስ ያለኝ። ባለን አቅም፣ (ማኅበራችን ፣ ለጊዜው 15 አባላት ነው ያሉት)ለዚያ አካባቢ ፤ እኔ የበኩሌን ድርሻ ማበርከት በመቻሌ ፣ ደስ ነው የሚለኝ። እንደሚመስለኝ፤ ይህ ፕሮጀክት ቀጣይነት ያለው ነው። በአዎንታዊ መልኩ! በመጪው ዓመት በዚያ በመገኘት ሁሉም ነገር ፣ ምን ዓይነት እርምጃ እንዳሳዬ ለመመልከት ተስፋ አለን። ከሳሙኤል ሁዋ ጋር ሥራውን እንቀጥላለን። »

ኢትዮጵያን ለመሰለ አዳጊ አገር ታዳሽ የኃይል ምንጭ ያለውን ተፈላጊነትና ጠቀሜታ እርስዎ እንዴት ያዩታል?

«የፀሐይ ኃይል፣ የራሱ የሆነ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ከማዕከሉ በመሠራጨት ድጋፍ ይሰጣልና ! ፕሮጀክታችንም ይህን የሚያደርገው በፀሐይ ኃይል የሚሠራ መሣሪኢ ለት/ቤት በመትክል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በፀሐይ ኃይል ስለሚሠራ የኃይል ምንጭ ተፈላጊነት መጠን በትክክል ለመናገር የሚያስችል ግምገማም ሆነ ጣናት አላደረግሁም ፤ ሆኖም እጅግ ተፈላጊ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ፣ በደቡቡ መስተዳድር እንደታየው ፣ የተለያዩ መንደሮችና ብሔረሰቦች ይህን እንደሚፈልጉ፣ ድጋፍ የሚሰጡ ቁም ነገር ያላቸው፣ አብረው ሊሠሩ የሚችሉ ተባባሪዎች ቢያገኙ እንደሚሹ ተገንዝበናል።»

(ድምፅ) አቶ ሳሙኤል ኤታና ሁዋ---

አድማጮቻችን ፣ አቶ ሳሙኤል ኤታና ሁዋንና ሄር ክሪስቶፍ ሄንድልን በማመሥገን የዛሬውን ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብር እዚህ ላይ እንደመድማለን፤ ተክሌ የኋላ ነኝ ፤ የሳምንት ሰው ይበለን!

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ