1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናዋዝ ሸሪፍ ከፓኪስታን ተጋዙ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 5 1999

የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ፓኪስታን ከመግባት ከመታገዳቸውም ሌላ ከአራት ሰዓታት ቆይታ በኃላ ወደ ሳውዲ አረቢያ መጋዛቸውን ዜና ምንጮች ዘግበዋል ።

https://p.dw.com/p/E87l
ናዋዝ ሸሪፍ በኢዝላምአባድ አውሮፕላን ማረፊያ
ናዋዝ ሸሪፍ በኢዝላምአባድ አውሮፕላን ማረፊያምስል AP

« ወደ ፓኪስታን የምንሄደው ብሄራዊ ግዴታችንንና ሀላፊነቶቻችንን ለመወጣት ነው ። ምክንያቱም የፓኪስታን ህዝብ አደራ አለብኝ ። እንዲሁም የፓኪስታን ህዝብ አምባገንነትን ለመጣልና ያልተበረዘ ዘላቂ ዲሞክራሲ ለማስፈን የሚካሄደውን ትግል እንድመራ እየጠበቀኝ ነው ። »
የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ነዋዝ ሸሪፍ ከለንደን ሳይነሱ ወደ ኢዝላምአባድ ከማቅናታቸው በፊት ለንደን ላይ ከሰጡት መግለጫ የተወሰደ ። ሸሪፍ ከለንደን ሳይነሱ ሀገራቸው የሚሄዱበትን ምክንያት ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት በመጪው ዓመት ታህሳስ በሚካሄደው ምርጫ ለመካፈል ነው ወደ ፓኪስታን የሄዱት ። ለንደን እያሉ እንደተናገሩትም ትልቁ ግባቸው የፕሬዝዳንት ፔርቬዝ ሙሻረፍን መንግስት ማስወገድ ነው ። የፓኪስታን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሸሪፍ ወደ ሀገራቸው የመመለስ መብት እንዳላቸው መንግስትም ሸሪፍ ወደ ሀገራቸው እንዳይመጡ መከልከል እንደሌለበት ባለፈው ወር ብይን አሳልፏል ። ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ቢያሳልፍም ሸሪፍ ግን ሀገራቸው ፓኪስታን መግባት አልተፈቀደላቸውም ሸሪፍን ያሳፈረው አውሮፕላን ኢዝላምአባድ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ ባኃላ ሸሪፍ ከአውሮፕላን ሳይወርዱ ባለስልጣናት ባሉበት ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ቆይተዋል ። ከዚያም ከአውሮፕላኑ በወረዱበት ወቅት የሀምሳ ሰባት ዓመቱ ፖለቲከኛ ነገሩ ግራ እንደገባቸው ነበር አብሮአቸው ለተጓዘው ጋዜጠኛ የተናገሩት ።
« በግልፅ ለመናገር ምን እየተደረገ እንደሆነ አላውቅም ። ከዚህ ቀደም ይህ ሆኖ አያውቅም ። አጠቃላዩን ጉዳይ እያስመሰሉ ነው ። ምንም አናውቅም ። አንዳንድ መረጃዎች አሉኝ ። ወደ ዕንግዳ መቀበያው ክፍል ከመውሰድ ይልቅ ወደ ሌላ ቦታ ሊወስዱን ይችላሉ ። ምናልባትም ሌላም ነገር ሊኖራቸው ይችላል ። ወደ ሌላ ስፍራ በአውሮፕላን ሊልኩን ይችላሉ »
ኢዝላምአባድ እንደደረሱ ወዲያው በቁጥጥር ስር ውለው የሙስና ክስ የቀረበባቸው ሸሪፍ እንደጠረጠሩትም ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ በሌላ አውሮፕላን ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጋዙ ። መንግስት ሸሪፍን በዚህ መልኩ ከሀገር ማባረሩ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው ይላል ። ዕርምጃው የተወሰደው ለህዝቡ ጥቅም ሲባል ነው ያለው መንግስት ሸሪፍ የተጋዙት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ነው ሲልም የድርጊቱን ትክክለኛነት አስቀምጧል ። ሸሪፍ ከመምጣታቸው አስቀድሞም የፓኪስታን ፖሊስ ልዩ ልዩ ዕርምጃዎችን ወስዷል ። የፓኪስታን የሙስሊም ሊግ ፓርቲ የተባለውን የሸሪፍን የፖለቲካ ማህበር መሪዎች ቃል አቀባያቸውንና ደጋፊዎቻቸውንም አስሯል ። በየክፍላተ ሀገራቱ የሚገኙት ደጋፊዎቻቸውም ወደ ዋና ከተማይቱ ወደ ኢዝላምአባድ እንዳይሄዱም የታገዱ ሲሆን የኢዝላምአባድ አውሮፕላን ማረፊያም እንዲሁ ታጥሮ ነበር ። ከሸሪፍ ደጋፊዎች አንዳንዶቹ ጊዜያዊውን አጥር በመጣስ መሪያቸውን በአውሮፕላን መረፊያ ተገኝተው ለመቀበል ሲሞክሩ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ። ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ከሀገራቸው ወደ ሳውዲ አረቢያ የተጋዙት ናዋዝ ሸሪፍ ከሰባት ዓመት በፊት ከሀገራቸው የተባረሩት ከመንግስት ጋር ተስማምተው ነው ። ያኔ በአውሮፕላን ጠለፋና በሙስና ወንጀል ተከሰው የዕድሜ ልክ ዕስራት የተበየነባቸው ናዋዝ ሸሪፍ ምትክ ለአስር ዓመታት በውጭ በስደት ለመቆየት ተስማምተዋል ። ከአስሩ ዓመት ሰባቱን በስደት የጨረሱት ሸሪፍ በታህሳስ መጨረሻ ላይ በሚካሄደው ምርጫ እካፈላለሁ ሲሊ ነው ። ስምነታቸውን አፍረሰው ነው ዛሬ ኢዝላምአባድ የሄዱት ። በርሳቸው የፓኪስታን ጉዞ ምክንያት አራት ሺህ ደጋፊዎቻቸው ተይዘዋል ። በደጋፊዎቻቸውና በፖሊስ መካከል በተነሳ ግጭትም አምስት ሰዎች ቆስለዋል ።