1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ነፋስ ፣ ፀሐይና የአየር ጠባይ ትንበያ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2005

የአየር ጠባይ ትንበያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ላተኮሩ ኩባንያዎች መረጃዎችን በማቅረብ ላይ በመሆኑ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ፤ ጀርመን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ለኃይል ምንጭ ኩባንያዎች አገልግሎት የሚሰጡ ከ 20 የማያንሱ የአየር ጠባይ ጠቋሚ

https://p.dw.com/p/16Bf2
ምስል DW/F.Hajasch
Meteorologie Wetter Wolken Cirrus-Wolken
ምስል picture-alliance/dpa

ድርጅቶች ተቋቁመዋል። ቁጥራቸው ወደፊት እየጨመረ እንደሚሄድም ነው የሚነገረው። ቶማስ እሽፔርሊንግ ፣ በኮሎኝ ከተማ የሚገኘው 18 ሠራተኞች ያሉት «ዩውሮ ዊንድ» የተሰኘው የአየር ጠባይ ትንበያ አቅራቢ ድርጅት ኀላፊ ናቸው። ድርጅታቸው፤ ከነፋስም ፤ ከፀሐይም ላቅ ያለ የኅይል ምንጭ የሚገኝበትን ጊዜ ጠቋሚ ነው።

«በምን ያህል የነፋስ ፍጥነት በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አው፣ የኃይል ምንጭ ማግኘትም ሆነ ማጠራቀም እንደሚችሉ እናሰላለን። በፀሐይ ብርሃን፣ በየ ካሬሜትሩ ምን ያህል «ዋት» የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት እንደሚቻልም እንዲሁ! በሰዓት ምን ያህል ኪሎዋት ኤሌክትሪክ እንደሚገኝና ጥቅም ላይ እንደሚውልም እንከታተላለን።ይህ ሁሉ መረጃም፤ ለኃይል ምንጭ ኩባንያዎች እንዲቀርብላቸው እናደርጋለን። »

Sonnenuntergang am Leuchtturm von Westerhever
ምስል AP

ከ «ዩውሮ ዊንድ» በአየር 5 ኪሎሜትር ያህል ፈንጠር ብሎ የሚገኘው Rhein Energie የተሰኘው የኤልክትሪክ ኃይል አመንጪ ኩባንያ ከዚሁ ከ«ዩውሮ ዊንድ» በየሰዓቱ ነው መረጃ የሚሰበስበው። የዚሁ ኩባንያ ተጠሪ፣ ዖማር ራምዳኒ---

«የአየር ጠባይ ትንበያው ተግባር ትክክለኛነት በጣም ተፈላጊው ነጥብ ነው። ትንበያው ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ ቁጥር የኤሌክትሪክ ኃይል በታሰበው መጠን ማመንጨቱም ከዚሁ ጋር ይያያዛል። የምንመካው፤ በዚህ ከሞላ ጎደል ትክክለኛ በሆነው መረጃ ነው። »

የጀርመን ፌደራል መንግሥት፣ አገሪቱ ቀስ በቀስ ከአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር እንድትሠናበት እቅዱን ካሳወቀ ወዲህ ስለ ኃይል ምንጭ አሰባሰብና ስለአየር ጠባይ ሁኔታ ፤ ለኅይል ምንጭ ኩባንያች መረጃ የሚሰጡ ኩባንያዎች ተፈላጊነት ይበልጥ እየጨመረ መሄዱ እንደማይቀር ነው የሚነገረው።

Sonnenenergie aus Griechenland
ምስል picture-alliance/dpa

ጨው ፣ --ለምግብ ማጣፈጫ የሚውለውን ጨው ማለታችን ነው። በፈሳሽነትና በጣጣር መልኩ ፣ ከውቅያኖስ ውሃና ከደረቀ ኩሬ፤ ከአፈርና ቋጥኝ ይገኛል ። በተፈጥሮ የሶዲዮምና የክሎሪን ቅልቅል የሆነው «ሶዲዮም ክሎራይድ»፣ መደበኛ ጨው፤ የማዕድ ጨውም ይባላል። በተመጠነ መልኩ ለምግብ ማጣፈጫነት እንደሚጠቅም የታወቀ ነው። መጠን ሲያልፍ ግን ጣጣው ብዙ ነው። ኃይለኛ የደም ግፊትና የተለያዩ የጤና ጠንቆችንም ያስከትላልና! ታዲያ ፤ በአሁኑ ወቅት ፤ በዓለም ዙሪያ ፣ ከመጠን በላይ ጨው የበዛበት ምግብ በመመገብ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡት መካከል በ 8 እና 18 ዓመት የዕድሜ እርከን የሚገኙ አሜሪካውያን ልጆች መሆናቸውን ከትናንት በስቲያ የቀረበ አንድ ሳይንሳዊ ጥናት ጠቁሞአል። እንደተባለው በ 8 እና በ 18 ዓመት መካከል የሚገኙ አሜሪካውያን ልጆችና ወጣቶች፤ ሀኪሞች ከሚያዙት እያንዳንዱ ሰው በቀን ሊወስደው ከሚችለውም ሆነ ከሚገባው 1,500 ሚሊግራም ጨው ፤ ከእጥፍም በላይ 3, 387 ሚሊግራም ጨው ያለበት የተለያየ ምግብ ይመገባሉ ።

ይህ ሊታወቅ የተቻለው በ 6,235 ሰዎች አመገገብ ላይ ጥናት ከተካሄደ በኋላ ነው። አብዛኛውን ጨው፣ ከ ¾ኛ በላይ የሚሆነውን የሚያገኙትም፣ ታሽገው የቆዩ ምግቦችን አዘውትረው በመመገብ ነው።

InterSolar Europe 2012 Soitec
ምስል DW

ከመጠን ያለፈ ጨው የበዛበትን ምግብ መመገብ፣ ኃይለኛ የደም ግፊት የሚያስከትል ሲሆን ፤ ይህም በፊናው፣ ለልብ ጠንቅ በመሆን ፤ የልባ ድካምን ፤ በከፊል ለአንጎል ደም ሳይዳረስ የሚቋረጥበትንም ሆነ የሚቆምበትን አደጋ ያስከትላል። በአንጎል ላይ የሚደርስ «ድንገተኛ ጥቃት» ሊባልም ይችላል። በአንጎል ላይ የተጠቀሰው አደጋ የሚከሠተው፤

የደም ዝውውር ለተወሰኑ ሴኮንዶች ሲቋረጥ ነው። የደም ዝውውር ሲቋረጥ ደግሞ አንጎል ደምና ኦክስጅን ያጣል። የአንጎል ሴሎችም ይሞቱና በአንጎል ላይ የማይጠገን ጉዳት ያስከትላሉ። ሰው ድንገት ራሱን ስቶ እስኪወድቅ በአንጎል ላይ የሚደርስ ጥቃት የሚያጋጥመው በ 2 ዐበይት ምክንያቶች ነው።

አንደኛ፤ ጠባብ በሆነ የደም ሥርም ሆነ የደም መተላለፊያ ቧንቧ፣ ደም ከረጋ፣-- የደምን መርጋት ደግሞ በሰውነት ውስጥ ቅባትና የመሳሰሉ መብዛት ሊያስከትል ይችላል። በዚህም ሳቢያ እንግዲህ የልብ ድካምም ሆነ የአንጎል ጥቃት ሊከሠት ይችላል ማለት ነው። ደም እንዲረጋ በማድረግ ረገድ ፣ ከላዔ-ፅንስ መድኃኒትም ሚና አለው። ይህ ደግሞ ከ 35 በላይ ዕድሜ ባላቸውና በሚያጨሱ ሴቶች ላይ ይበልጥ ያይላል ነው የሚባለው።

ሁለተኛው ምክንያት፤ በአንጎል ክፍል፤ የደም ቧንቧ መፈንዳት ወይም መከፈትና ደም ወደ አንጎል ሲፈስ ነው።

Symbolbild Nachhaltigkeit Natur
ምስል Gabriele Rohde/Fotolia

በአጠቃላይ የደም ግፊት፤ ለአንጎል ድንገተኛ ጥቃት ዋናው ሰበብ ነው። ከዚህ በተረፈ፤ ሥርዓት ያልጠበቀ የልብ ትርታ፣ የስኳር በሽታ፣ በዘር የሚተላለፍም ሆነ የሚወረስ፤ የቅባት በሰውነት ውስጥ መጠን ማለፍና የመሳሰሉትም ግምት ውስጥ የሚገቡ ናቸው።

ለደም ግፊት ፣ በሎም ለልብ ድካም ወይም ለአንጎል ድንገተኛ ጥቃት ይበልጥ የሚጋለጡ ሰዎች፤ ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘዴ ያላቸው ናቸው። እነርሱም፣

ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው፤ አብዝተው አልኮል መጠጥ የሚጠጡ፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቅባት ወይም ጨው የበዛበት ምግብ የሚመገቡ፤ ሲጋራም ሆነ ሲጋር የሚያጨሱ፣ በኮኬይንም ሆነ በተለያዩ ሱስ አስያዥ ቅመማት የሚጠቀሙ ናቸው።

በዩናይትድ እስቴትስ ጨው ስለበዛበት ምግብ የተደረገው ጥናት ፣ በእርግጥ አስደንጋጭ ነው። በትምህርት ቤቶች፣ ለተማሪዎች የቀረበው አዲሱ የአመጋገብ መርኀ -ግብርም ሆነ የምግብ አዘገጃጀት ፣ አስተዋጽዖው ከፍ ያለ መሆኑ ቢታመንበትም ገና ይበልጥ አልተስፋፋም።

ጨው የበዛበት ምግብ ፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል ፤ ለማንኛውም አገር ልጅ ፤ ወጣትም ሆነ ጎልማሳ የሚበጅ አይደለም። ጨው፣ ለምን በሚታሸግ ምግብ ላይ ይጨመራል?

Riffgat Offshore Windpark Fundamente
ምስል Riffgat

በቆርቆሮ፤ በብልቃጥም ሆነ በሌላ ዓይነት ዕቃ የታሸገ ምግብ፣ ሳይበላሽ ረዘም ላላ ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ ጨው ጠቀሜታ እንዳለው የታወቀ ነው። ታዲያ፤ ምግቡ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ያድርግ እንጂ ለተመጋቢው ዕድሜን የማሳጠር እንጂ የማስረዘም ዋስትና እንደማይሰጥ ከጥናቱ መረዳት ይቻላል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ