1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና፤ አምሥት ዓመት የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነት

ረቡዕ፣ ኅዳር 27 1999

ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ከሆነች ወዲህ ሰሞኑን አምሥት ዓመት ይሞላታል። ታዛቢዎች እንደሚናገሩት ይህ ጊዜ ለቤይጂንግ ስኬታማ ሆኖ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/E0dI
በዓለም ንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ ሼንዩ
በዓለም ንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ ሼንዩምስል AP

ሕዝባዊት ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ከሆነች ወዲህ በሚቀጥለው ሣምንት መጨረሻ ላይ አምሥት ዓመት ይሆናታል። ሰፊ ገበያ ያላት አገር የነጻውን ንግድ ዓለም በመቀላቀል ያደረገችው ዕርምጃ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ስኬታማ ነው። እርግጥ በሌላ በኩል ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት የንግድ ሽኩቻ እያደገ መሄዱም አልቀረም። ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅትን የተቀላቀለችው ቀደም ሲል 15 ዓመታት ከፈጀ አድካሚ ድርድር በኋላ ነበር። በመጨረሻም ቤይጂንግ የንግድ ሕግጋቷን ከድርጅቱ በማጣጣም፣ ወደ አገር ለምታስገባው ምርት የምትጠይቀውን ቀረጥ በመቀነስና ገበዮቿን ለመክፈት ቃል በመግባት ተደራዳሪዎቿን ማግባባቱ ይሳካላታል።

የቻይና መንግሥትም በበኩሉ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገቱን ዘላቂ ለማድረግና የውጭ ሃብትን ወደ አገር ለመሳብ ነጻውን ንግድ ከመቀላቀል የተሻለ ምርጫ እንደሌለ ለመረዳት ብዙም አላዳገተውም። ለዚህም ውስጣዊ ለውጡን በማጠናከር የገበያ ኤኮኖሚን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ግፊት ተደርጓል። ለቻይና በብዙ ጥረት የተሳካው የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባልነት ለአገሪቱ ዕርምጃ እጅግ ነእ የጠቀመው። ኤኮኖሚዋ ባለፉት አምሥት ዓመታት በያመቱ አሥር ከመቶ ገደማ ዕድገት እያሣየ ነው የመጣው።

በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት ቻይና ከሺህ ሚሊያርድ ዶላር በሚበልጥ የንግድ መጠን ከአሜሪካና ከጀርመን ቀጥላ ሶሥተኛዋን ታላቅ የንግድ አገር ጃፓንን ከቦታዋ ልትፈነቅል በቅታለች። በ 2001 ከአምሥት ዓመት በፊት ቻይና በሰባተኛ ደረጃ ላይ ነበር የምትገኘው። የሻንግሃይ የዓለም ንግድ ማዕከል ባልደረባ ሄ-ሆንግቻንግ እንደሚሉት ለዚህም የድርጅቱ ዓባልነት እጅግ ነው የጠቀማት። በተለይ በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረው ዘርፍ የነበሩበት የተለያዩ መሰናክሎች ጥቂት እየሆኑ ሄደዋል። ይህ ደግሞ የውጭ ሃብት ወደ አገር እንዲገባ በማድረጉ በኩል የተሻለ ጥርጊያ መክፈቱ አልቀረም። የቻይና የኤኮኖሚ ደምቦች የዓለም ንግድ ድርጅትን መርሆች እየተቃረቡ ለመሄድ ችለዋል። ይህም የውጭ ሐብትን በመሳቡም ሆነ ዋስትናውን በማረጋገጡ ረገድ ትልቅ ዕርምጃ ነው።

እርግጥ በዚህ ቻይና ባመራችበት ከነጻው ንግድ የመጣጣም ሂደት ብዙዎች የመጠቀማቸውን ያህል በሌላ በኩል ፍቱን ያልነበሩት የመንግሥት ኢንዱስትሪዎችና የእርሻው ልማት ዘርፍ ተጎጂዎቹ መሆናቸው አልቀረም። ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅትን በመቀላቀል ቀድሞ ለገበሬዎች የምትሰጠውን ድጎማ መቀነስና ከዚሁ ተያይዞም የእርሻ ምርት ገበዮቿን ለውጭ አቅራቢዎች መክፈት ነበረባት። በዚሁ የተነሣም ለምሳሌ የቻይና ገበሬዎች በርካሽ ዋጋ አተርና ጥጥ ከምታቀርበው ከአሜሪካ ሊፎካከሩ አልቻሉም። በሌላ በኩል ይሁንና የቻይና የጨርቃ-ጨርቅ፣ የኤሌክትሮ፣ የጫማና የመጫወቻ ኢንዲስትሪዎች ምርት ሌሎች አገሮችን በማጥለቅለቅ የመፎካከር ብቃት አሳጥቶ ነው የሚገኘው።

በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ዋጋን በማጣጣል ድርጊት ለዓለም የንግድ ድርጅት ከቀረቡት አቤቱታዎች ሲሦው ቻይናን የሚመለከት ነበር። በሰሜን ጀርመን የኪል ከተማ የኤኮኖሚ ኢንስቲቲዩት የዓለም ንግድ ድርጅት ባለሙያ ዲን ሽፒንአንገር እንደሚሉት ለዚህ ምክንያቱ የቻይና የተፎካካሪነት ብቃት እያደገ መምጣቱ ነው። ይህ ደግሞ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት መንግሥታት መካከልም ያለ ጉዳይ ነው። ፉክክሩ በጠበቀ ቁጥር፤ ለምሳሌ በቦይንግና በኤየርቡስ መካከል እንደታየው፤ ምርጫው ወደ ፍርድቤት መሄድ ነው። በሌሎች ምርቶች ዘንድም ሁኔታው ከዚህ አይለይም። አንዱ ሌላውን ዋጋን በማራከስ ይወነጅላል።

የዋጋ ማጣጣሉ ክስ ብዙ ክብደት ሊሰጠው የማይችል ቢሆንም በቻይናና በኢንዱስትሪው ዓለም መካከል በሚደረገው ፉክክር ሌላ የሚያመዝን ወቀሳ አይታጣም። ለምሳሌ የጀርመን ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ዕውቀትን አሳልፈው እንዲሰጡ መገደዳቸውን ያነሳሉ። እርግጥም የውጭ ኩባንያዎች ቻይና ውስጥ መሥራት ከፈለጉ ቤይጂንግ ዕውቀትን እንዲያስተላልፉና የጋራ ተቋም Joint Venture እንዲከፍቱ የምታስገድድባቸው የተለያዩ ደምቦችና ሕግጋት አሉ።

ሆኖም ከቴክኖሎጂው ማስተላለፍ ግዳጅ ይልቅ አስቸጋሪ ሆኖ የሚገኘው ቻይና የምርት ባለቤትነትን መብት በመጋፋት የምታደርገው ግልበጣ ወይም ኩረጃ ነው። በአውሮፓው ሕብረት የንግድ ኮሜሣር በፔተር ማንደልሶን አባባል ለአውሮፓ ቻይናን የመፎካከር መሳን ትልቁ ችግር ይህ ነው። ይሁን እንጂ በቤይጂንግ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መሆን ተጠቃሚዋ ቻይና ብቻ አይደለችም። በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያለችውና ገበያዋ ግዙፍ የሆነው አገር የነጻውን ንግድ ዓለም መቀላቀሏ በረጅም ጊዜ ሁሉንም እንደሚበጅ አንድና ሁለት የለውም።