1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይናና የአ.ሕብረት፤ የንግድ ውዝግቡና መፍትሄው

ሰኞ፣ ሰኔ 6 1997
https://p.dw.com/p/E0eb

የሕብረቱ ኮሚሢዮን የአውሮፓ ጨርቃ-ጨርቅና አልባሣት አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕርምጃውን በፍጥነት ከተለወጠው የንግድ ሁኔታ ጋር ያጣጥም ዘንድ ወዲያው ጥሪ አድርጓል። በስምምነቱ መስፈን የአውሮፓው ሕብረት ቻይናን በገበያ አዛቢነት በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ለመክሰስ ያሰማው ዛቻ ዋጋ ሊያጣ በቅቷል።

ለውዝግቡ መንስዔ የሆነው ለአያሌ ዓመታት ሲሰራበት የኖረው በዓለም ገበያ ላይ የጨርቃ-ጨርቅ ምርትን ኮታ የሚገድብ ውል ዘመን ማክተም ያስከተለው ሁኔታ ነበር። ስምምነቱ ካበቃ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ወዲህ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበዮች የሚዘልቀው የቻይና የጨርቃ-ጨርቅና የአልባሣት ምርት መጠን እጅግ ነው የጨመረው። በገዢዎቹ አገሮች የገበያው መዛባት ተጻራሪ ዕርምጃዎችን ማስከተሉም አልቀረም።

ቀድሞ በጥብቅ ደምብ ይተዳደር በነበረው ገበያ ላይ የተፈጠረው ነጻ ንግድ ዕድሜ እርግጥ ከአምሥት ወራት ሊያልፍ አልቻለም። ይህም የሆነው አሜሪካ የቻይናን ምርቶች ወደ አገር በማስገባቱ ጉዳይ ገደብ በማድረጓና የአውሮፓ ሕብረትም ቤይጂንግን በዓለም ንግድ ድርጅት ፊት ለመክሰስ በመነሣቱ ነው። አሁን የአውሮፓው ሕብረት የንግድ ኮሜሣርና የቻይናው የንግድ ሚኒስትር በአንድ አስታራቂ ሃሣብ በመስማማት ከክስ እንዳይደረስ ሲያደርጉ ዕርቁ በቤይጂንግና በዋሺንግተን መካከል የሰፈነውን ውዝግብም ዕልባት ለማስያዝ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ዕምነት አለ።

በስምምነቱ መሠረት ቻይና ዘመኑ ባከተመው ውል ላይ የተጠቀሰውን የመሸጋገሪያ ደምብ በማክበር አውሮፓ ዕርምጃዋን እስከፊታችን 2008 ፤ ማለት በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት በነጻው የጨርቃ-ጨርቅና የአልባሣት ንግድ አኳያ አዲስ ከተፈጠረው የገበያ ሁኔታ ጋር እንድታጣጥም ጊዜ ትሰጣለች። አውሮፓውያኑም በአንጻሩ ጊዜው ካለፈበት ገበያን ዘግቶ የመያዝ፤ የመከላከል ዕርምጃ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል።

ቻይናና አሜሪካም ከተመሳሳይ ስምምነት ከደረሱ የዓለም ንግድ ድርጅት በፊታችን ታሕሳስ ወር ሆንግኮንግ ውስጥ የሚያካሂደው ጉባዔ ከመድረሱ በፊት አንድ ትልቅ ችግር ተፈታ ማለት ነው። ነጻውን ንግድ የሚገድቡ መሰናክሎች መወገዳቸው ሰፊ የብልጽግና ጥቅም የሚያመጣ በመሆኑ በመሠረቱ ሁሉም የውዝግቡ ተሳታፊዎች ይሹታል። ግን ይህ እንዲሳካ በዓለምአቀፉ ገበያ ላይ ውድቀት እንዳይከተል ማድረጉና እኩልነትን ማሰፈኑ ቅድመ-ግዴታዎች ናቸው።

የአውሮፓ ሕብረት ያለፈው የኮታ ደምብ ያስቀመጠውን መሸጋገሪያ አንቀጽ በመመርኮዝ ቻይና አሁን በሰፈነው አስታራቂ መፍትሄ እንድትገታ ሊጫን በቅቷል። በሽግግሩ መርህ መሠረት በዓለም ገበያ ላይ የሚቀርበው የቻይና ምርት በዓመት ከ 7.5 በመቶ በላይ መጨመር አይፈቀድለትም። ባለፉት ወራት ይህ ገደብ ከመጠን በላይ ታልፎ ነበር። በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት ቻይና ያቀረበችው የጨርቃ-ጨርቅ ምርት ካለፈው ሲነጻጸር በአማካይ 187 በመቶ በሆነ መጠን ከፍ ብሎ ነው የታየው። በዚህም የቻይና ምርት አቅራቢዎች መሸጋገሪያውን ደምብ መጣሳቸው ግልጽ ነው።

በሻንግሃዩ የኤውሮ-ቻይና አስታራቂ ስምምነት አሥር ውዝግቡ ይበልጥ አተኩሮባቸው የነበሩ የምርት ዓይነቶች የገበያ ዕድገት በዓመት በ 8 እና 12.5 ከመቶ በሆነ መጠን መካከል የሚንሸራሸር እንዲሆን ከአንድነት ተደርሷል። ይህም የሚጸናው እርግጥ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ነው። ከዚያን ወዲያ የአውሮፓ ገበያ ነጻ ይሆናል። በሌላ አነጋገር አውሮፓውያን አምራቾች ሁኔታቸውን ለማጣጣም ጊዜ ለማግኘት ችለዋል ማለት ነው።

በሌላ በኩል የቻይና የገበያ ድርሻ ከዓመቱ መጀመሪያ ወዲህ በዚህ በአውሮፓ ማየሉ በተለያዩ አገሮች ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። በተለይ የጊዜውን ሂደት በመገንዘብ አስፈላጊው መዋቅራዊ ለውጥ በጊዜው ባልተደረገባቸው አልባሣትን በሰፊው በሚያመርቱ አገሮች፤ ለምሳሌ በስፓኝ፣ ፖርቱጋል፣ ግሪክና ኢጣሊያ ብዙዎች ፋብሪካዎች በመዘጋት አደጋ ላይ ወድቀውና የመስኩ ሙያተኞችም ለሥራ-አጥነት ተጋልጠው ነው የሚገኙት። በጉዳዩ ብዙም ጉዳት ያልደረሰባት ርካሽና ቀላል አልባሣትን በአገር ውስጥ የማታመርተው ጀርመን ናት።

ለማንኛውም አሁን ሻንግሃይ ላይ የተደረገው ስምምነት አሣሪነት በሶሥት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያበቃል። የአውሮፓ ገበዮች ለቻይና ምርቶች ጨርሰው ነጻ ይሆናሉ ማለት ነው። ቻይና ይህን ዕድል ደህና አድርጋ እንደምትጠቀምበት ደግሞ አንድና ሁለት የለውም።