1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትውልደ ኤርትራዊው የስደተኞች ተቆርቋሪ

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2007

«እኔ ያሳለፍኩት መከራ በሌሎች መደገም የለበትም» ይላል ። ለዚህም ፣ መሰል ዓላማ ካላቸው ደጋፊዎቹ ጋር እየሠራ ነው ።የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ ባቋቋማቸው ፕሮጀክቶች አፍሪቃውያን ስደተኞችን ይረዳል ።

https://p.dw.com/p/1GTI9
Bildergalerie Flüchtlingsunterbringung in Deutschland
ምስል imago/epd

ትውልደ ኤርትራዊው የስደተኞች ተቆርቋሪ

ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ በሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ጀርመን የሚገኙ ወገኖቹንና ሌሎች አፍሪቃውያንን ይረዳል ። ስደተኞች በራሳቸው እንዲተማመኑ እንዳይገለሉ ቅስማቸው እንዳይሰበርና ራሳቸውን አሳድገው የህብረተሰቡንም ከበሪታ እንዲያገኙ ማድረግ ከፕሮጀክቶቹ ዓላማዎቹ ውስጥ ዋነኛዎቹ ናቸው ። ዘርአይ ኪሮስ አብርሃም ይባላል ከተወለደበት ከኤርትራ በ7 ዓመቱ በረሃ አቋርጦ ከእናቱና ከእህቱ ጋር ሱዳን ተሰዶ አምስት ዓመት ከቆየ በኋላ የዛሬ 25 ዓመት ነበር ጀርመን የመጣው ። በጎርጎሮሳዊው 1990 መጨረሻ ላይ ጀርመን የመጣው የያኔው ታዳጊ ወጣት ዘርአይና ቤተሰቦቹ ከፍራንክፈርት ወጣ ብላ በምትገኘው ሃናው ከተማ ነበር መጀመሪያ የገቡት ። በለጋ እድሜው ለተሰደደው ለወጣቱ ዘርአይ ህይወት በጀርመን ቀላል አልነበረም ።«በስደት ነው ጀርመን የመጣነው ለና አንዳንድ ሁኔታዎች አስደንጋጭ ነበሩ ። ጀርመን ውስጥ ጠንክረን ሰርተን የተሻለ ህይወት እንኖራለን ብለን ነበር የመጣነው ። ሁሉም ይሳካልናል ብለን ነበር የምናስበው ። ሆኖም መጀመሪያ ስንመጣ የጠበቅነው አይደለም የገጠመን ። እናቴ ወደ ዚህ ሃገር ስትመጣ በመንግሥት ድጎማ ለመኖር አልነበረም ።ስለሚሰጠው ድጎማም የምናውቀው ነገር አልነበረም ። እዚህ የመጣችው ጠንክራ ለመሥራትና ልጆችዋን ለማስተማር ነበር ። ሆኖም እዚህ ስትመጣ የሥራ ፈቃድ አላገኘችም ። አያያዙም ትንሽ አስቸጋሪ ነበር ።እናም የባህል ግጭት ነበር ያጋጠመኝ »
ዘርአይ በሱዳኑ በዚያን ጊዜው የኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅት የፖርት ሱዳን ትምህርት ቤት ነበር ትምህርቱን የተከታተለው ።እዚያም ከመደበኛ ትምህርት ጋር ይከታተል በነበረው የፖለቲካ ትምህርትና ባነባቸው መፃህፍት ምክንያት ያዳበረው አስተሳሰብ በጀርመን ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ ለመኖር ጊዜ ወስዶበታል ።


«ነጮች ይህን ያን አደረጉን እየተባል አመጡብን እየተባልኩ ስላደግኩ ነጮችን ጠላቶቼ አድርጌ ነበር የማያቸው ። በዚህ አስተሳሰብ ስላደግኩ ይህ በዐዕምሮየ ተቀርፆ ስለቆየ ጀርመን ውስጥ ከህብረተሰቡ ጋር መዋሃዱ ለኔ አስቸጋሪ ነበር ። በጥቁርነቴ የምኮራ አፍሪቃዊ ነበርኩ ። እናም እነርሱ ከና ጋር አይደሉም ። የኛን ጥሩ አይመኙም ጠላቶቻችን ናቸው ጦርነት ውስጥ ከተቱን ሲባል እየሰማሁና እያነበብኩ ነበር ያደግኩት ይህም ያበሳጨኝ ነበር ። እዚህም አመፀኛ እንድሆን አደረገኝ »
ዘርአይበዚህ አስተሳሰቡ ምክንያት በጀርመን በራሴ እስር ቤት ውስጥ ነበር የምኖረው ይላል ።ኋላ ላይ ግን ይህን አስተሳሰቡን የሚያስለውጥ አጋጣሚ ተፈጠረ
«እነዚህ ሁሉ ልምዶች ተደማምረው ጀርመን ውስጥ ወደ መጥፎ መንገድ ወሰዱኝ አመፀኛ ሆንኩ የዕፅ ሱሰኛ ነበርኩ ።ኣንድ ቀን ዘርአይ መለወጥ አለብህ ራስህን መቀየር አለብህ ይሉኝ ነበር ።አንድ ቀን አንድ ሰው ከመፀ,ሀፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር የሚናገር ጥቅስ ሰጠኝ ከዚያ በኋላ አስተሳሰቤን ለውጬ ስለ ጀርመን በዐዕምሮየ የተቀረፀው ተቀየረ ።»
ከዚህ በኋላም ዘርአይ ወገኖቹን ለመርዳት የሚያስችለው ፕሮጀክት አዘጋጀ ። ፕሮጀክት ሞሰስ ሲል የሰየመው የዚህ ግብረ ሰናይ ሥራ ዓላማ እርሱ ያለፈበትን መንገድ በሌሎች እንዳይደገም ማድረግ ነው ነው።
«የሌሎች እርዳታ አለበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቡድን እንገኛናለን ። በተለይ ለኔ ጀርመን የሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞችና ሌሎች እኔ ያሳለፍኩትን ጉዞ መድገም የለባቸውም ነው የምለው ። ይሄ ነበር የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ።እዚህ ያሉትን ልጆች ወጣቶች መደገፍ አለብን ። ስለነርሱ መናገር ወይም ዝም ብሎ ማየት ብቻ ሳይሆን አንድ ነገር እንስራ ከ2005 ዓም ጀምሮ በትግርኛ የምክር አገልግሎት እንሰጥ ነበር በ2013 መጨረሻ በአጠቃላይ በስደተኞች ጉዳይ ላይ መሥራት ጀመርን »
ለወጣቶች ማህበራዊ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ፍርንክፈርት ላይ ሥራ የጀመረው የሞሰስ ፕሮጀክት በ2013 አገልግሎቱን ለሌሎች ሃገራት ዜጎችም መስጠት ጀመረ ።
«በ2013 ስንጀምር የስደተኞች ሁኔታ በሙል ተቀየረ ። እናም ጉዳዩን ስናጤነው ለምን በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን መካከል ልዩነት እናደርጋለን ። ሌሎች አፍሪቃውያንንስ ለምን አንረዳም ። ሁላችንም አንድ ቀለም ና ተመሳሳይ ችግር ነው ያለን ብለን አፍሪቃውያን ላይ ማተኮር ጀመርን ።»
በዚሁ ፕሮጀክት ስር ቲም አፍሪቃ የተባለ ኤርትራውያን ብስክሌተኞችን ያሰባሰበ ቡድን መስርቷል ። ለዚህ ቡድን ምስረታ ምክንያት የሆነው በአንድ አጋጣሚ የሰማው ታሪክ ነበር
«በሞሰስ ፕሮጀክት ውስጥ ለአንድ ሰው ሳስተረጉም ሰውየው አስመራ ብስኪሌተኛ እንደነበረ ነገረኝ። አሁንም በዚሁ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለውአጫወተኝ ። እዚህ ብስኪለተኛ መሆን አለመቻሉ በጣም ቅር እንደሚለው ፣ከኤርትራ ጀምሮ የሚያውቃቸው ሌሎች ብስክሌተኛ ጓደኞች እንዳሉትም እነርሱም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነግሮኛል »
ዘርአይ በኤርትራ ብሔራዊ ስፖርት የሆነውን ብስክሌት ከጀርመን ህብረተሰቡ ጋር መቀራረቢያና መደባለቂያ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ይቻላል የሚል እምነት አለው ።
በሞሰስ ፕሮጀክት ለኤርትራውያን ስደተኞች የቋንቋ ትምህርትና ሌሎች የትርጉምና የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት ግብረ ሰናይ ተግባር የጀመረው ዘርአይ እዚያው ፍራንክፈርት ኡቡንቱ ሃውስ የተባለ የስደተኞች መገናኛ የሃሳብ መለዋወጫ የባህል ና የስነ ጥበብ መድረክ እንዲሁም ሴሚናሮችና ዐውደ ጥናቶች ማካሄጃ ማዕከል ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው ።በቅርቡ እንደሚከፈት የሚጠበቀው ይህ ማዕከል ዘርአይ እንደሚለው ለስደተኞች የስራ እድል የሚያስገኝም ይሆናል ።»
ስደተኞችን የመርዳት ሃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሊሆን አይገባም የሚለው ዘርአይ በተለይ በውጭ ሃገራት ብዙ ጊዜያት የቆዩና አቅሙ ያላቸው የውጭ ዜጎች ወገኖቻቸውን መርዳት እንዳለባቸውያሳስባል። ኣዚህ ጀርመን ስደተኞች መግባታቸውን የሚቃወሙ ደግሞ ስደት በነርሱም የነበረ መሆኑን ሊረዱትና ታሪካቸውንም ሊያጤኑት ይገባል ይላል ።
«ስደተኞች በመምጣታቸው የሚያማርሩ ጀርመኖች ታሪካቸውን የረሱ ከየት እንደመጡ ምን እንዳሳለፉ የረሱ ይመስለኛል ።ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንደጀመሩ እነርሱም በተለያዩ ሃገራት ተሰደው እንደነበር የረሱ ናቸው ።ከ20 ዓመት በፊት ጀርመን ምሥራቅ ምዕራብ ተብላ በተከፈለች ጊዜ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሰዎች ይሰደዱ ነበር ። ይህ በመሠረቱ ለነርሱ አዲስ አይደለም ።ይህ ምን ማለት እንደሆነና የስደት ታሪካቸውንም ረስተዋል ።ማንም ሰው ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ መስራት ይፈልጋል ። ስለዚህ የስደተኞችን መብት ማስከበር ምቾትን የሚያጓድል አይደለም ። ስደተኞች ጠንካራ ሠራተና ሆነው ለጀርመን ማህበረሰብ ብዙ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ ።
በአሁኑ ጊዜ ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ከሚጎርፉ የዓለማችን ስደተኞች ኤርትራውያን ሶስተኛውን ደረጃ ይይዛሉ ። እነርሱን በቁጥር የሚበልጡት ሶሪያውያንና አፍጋናውያን ናቸው ። እድል ቀንቷቸው በጎርጎሮሳዊው 2015 በአደገኛው የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የመጡት ኤርትራውያን ቁጥር 23 ሺህ 878 ይገመታል ። ዘርአይ የኤርትራውያንን ስደት የሚያቆም መፍትሄ የሚለውን ተናግሯል ።
«በኤርትራ የመንግሥት ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ኤርትራውያን መሰደዳቸው አይቆምም ። በተለይ ወጣቶች የሳዋው ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት እስካልተቀየረ ድረስ ሰዎች ይሰደዳሉ ። ሁሉም ህይወቱን መምራት ይፈልጋል እንደዚህ ዓይነቱ መንግስት ወጣቶችን አፍኖ እንዲይዝ መደገፍ ትልቅ ወንጀል ነው ። ምክንያቱም ይህን አገዛዝ መደገፍ ማለት ህዝቡ እንዳይወጣ ማፈን ማለት ነው ። »
ኂሩት መለሰ

21.01.2013 Karte Eritrea Asmara eng
Deutschland Martin Patzelt nimmt Flüchtlinge aus Eritrea auf
ምስል picture alliance/dpa/P. Pleul

አዜብ ታደሰ