1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትዊተር፥ 10ኛ ዓመት

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2008

የመጀመሪያው የትዊተር መልእክት የዛሬ ዐሥር ዓመት በመሥራቹ ጄክ ዶርሲ ለዓለማችን የተዋወቀው፦ ማክሰኞ መጋቢት 12 ቀን፣ 1998 ዓ.ም. ነበር። ጄክ ያስተዋወቀው የትዊተር መልእክት አንድ ቢሊዮነኛው ላይ ለመድረስ ግን ሦስት ዓመት ግድም ፈጅቶበታል።

https://p.dw.com/p/1IHtW
USA Schauspieler Selfie von Ellen DeGeneres Gruppenbild
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. DeGeneres

ትዊተር፥ 10ኛ ዓመት

በእርግጥ ዛሬ አንድ ቢሊዮን የትዊተር መልእክቶችን ለማስተላለፍ ዓመታት መጠበቅ አያስፈልግም፤ ምናልባትም ሁለት ቀን ብቻ። ይኽ ከዓለም አንዱ ጫፍ የተላከ መልእክትን እጅግ በፈጣን ኹኔታ ሌላኛው ጫፍ ለሚገኙ ሚሊዮኖች ማድረስ የቻለ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ በአጠቃላይ መገናኛ ዘርፉ ላይ ታላቅ ለውጥ አስከትሏል።

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የትኛውም ሥፍራ አንዳች ነገር ቢከሰት፤ ዜናውን አለያም መልእክቱን በፍጥነት እና በቅድሚያ ለዓለም ማድረሻው ዋነኛ መንገድ ትዊተር ኾኗል። ትዊተር በአንድ ጊዜ 140 ፊደላትን አለያም ምልክቶችን ብቻ ማስተናገድ ቢፈቅድም ቅሉ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ግን ከእለት እለት እያሻቀበ ነው። ትዊተር በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 320 ሚሊዮን ንቁ ተጠቃሚዎች አሉት። ከ500 ሚሊዮን የማያንሱ ሰዎች ደግሞ ገባ ወጣ በማለት ዳተኛ ተጠቃሚ መኾናቸው ይጠቀሳል። በነገራችን ላይ ትዊተር፦ «የጫጩት ወፍ ጭውጭውታ» የሚል ትርጓሜንም ይይዛል።

በእርግጥ ትዊተር ምን እንደኾነ እና ወደፊት ወዴት እንደሚመራ መሥራቹ ከመነሻው ለይቶ አስቀምጦታል። የትዊተር መሥራች ጄክ ዶርሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ትዊተርን እውን ሲያደርግ ዋነኛ ዓላማው እውስጡ የሚመላለሰውን ሀሳብ ወደ ዓለም ለማስተላለፍ መሸጋገሪያ እንዲሆነው ብቻ ማድረግ እንደነበር ገልጧል። ጀርመናዊው የኦንላይን ባለሙያ እና ጋዜጠኛ ማሪዮ ሲክስቱስ ትዊተር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ መልእክቶችን በትዊተር ያስተላልፋሉ። እሳቸውም የጄክን ሀሳብ ይጋራሉ።

ጀርመናዊው የኦንላይን ባለሙያ እና ጋዜጠኛ ማሪዮ ሲክስቱስ
ጀርመናዊው የኦንላይን ባለሙያ እና ጋዜጠኛ ማሪዮ ሲክስቱስምስል DW

«ትዊተር የተገለጠ ሀሳብን ሊቆጣጠሩት እና መዳረሻውንም ሊረዱት የማይቻልበት መንገድ ነው። ትዊተርን እንደ ቡና መሸጫ ካፍቴሪያ ብንመስለው የሆነ ሰው ካፌው ውስጥ ገብቶ ቡናውን ካዘዘ በኋላ ሰው ያዳምጠው አያዳምጠው ሳያውቅ የሚያዳምጠው ቢኖር እንኳን ማን እንደኾነ ሳያውቅ ዝም ብሎ ማውራት ቢጀምር እንደማለት ነው። ጋዜጣን ብንወስድ 500 ሰው ጋር ይላክ ስንት ሰው ጋር ማወቅ ይቻላል። ትዊተር ሲኾን ግን መልእክቱ ማን ጋር እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም።»

ትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ በዘመኑ የመገናኛ አውታር እና የግንኙነት ዘርፍ ይኽ ነው የማይባል ታላቅ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ትዊተር በዓለማችን መልእክቶች አጠር ብለው እጅግ በፈጣን ኹኔታ እንዲሰራጩ አስተዋጽዖ አድርጓል። ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 ዓ.ም. ትዊተር በቀን የሚያስተናግደው መልእክት 5000 ድረስ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ በ2008 ዓ.ም. ቁጥሩ በከፍተኛ ኹኔታ ጨምሮ 300,000 ትዊት በቀን መሠራጨት ችሏል። በ2009 ዓ.ም. በቀን የሚሠራጩ የትዊተር መልእክቶች እስከ 35 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። እንዲህ እንዲህ እያለ በአሁኑ ወቅት በእየ ሰከንዱ ልዩነት የሚሠራጨው የትዊተር አጭር ዜና በ2007 ዓ.ም. በቀን ይሰራጭ ከነበረው ልቋል።

internetelivestats.com የተሰኘው ድረ-ገጽ በአሁኑ ወቅት በእያንዳንዷ ሰከንድ 6,000 ግድም፤ በእየ ደቂቃው 350,000 በእየ ቀኑ 500 ሚሊዮን እንዲሁም በዓመት እስከ 200 ቢሊዮን አጫጭር መልእክቶች በትዊተር ይሠራጫሉ ሲል አስፍሯል። የትዊተር መሥራች ጄክ ዶርሲ፥

«ትዊተር ውይይትን ያጎለብታል፤ ዓለም ማየት የሚፈልገውን ንግግር ያጠናክራል። ትዊተር አንድን ነገር ለዓለም ለመንገር ፈጣኑ መንገድ ነው። በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ መላው ዓለም ምን በማለት ላይ እንዳለ መመልከቻ ፈጣኑ መንገድም ነው።»

በ86ኛው የኦስካር ሽልማት ምሽቱ አስተናጋጇ ኤለን ደጄነርስ የተላከው ትዊተር
በ86ኛው የኦስካር ሽልማት ምሽቱ አስተናጋጇ ኤለን ደጄነርስ የተላከው ትዊተርምስል picture-alliance/dpa/Screenshot Twitter

በርካታ ፖለቲከኞች፤ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች ትዊተርን በንቃት ይጠቀማሉ። ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም በርካታ ደጋፊ እና ተከታዮችን ለማፍራት ትዊተርን ያዘወትራሉ። ለአብነት ያህል አንቀንቃኟ ኬቲ ፔሪ በትዊተር 85 ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች አሏት። በትዊተር ተከታይ ብዛት እስካሁን ኬቲ ላይ የሚደርስ አልተገኘም።

በርካታ ሰዎች የተቀባበሉት እና የወደዱት ስኬታማ የትዊተር መልእክት ደግሞ ካቻምና በ86ኛው የኦስካር ሽልማት ወቅት በምሽቱ አስተናጋጇ ኤለን ደጄነርስ የተላከው ትዊተር ነበር። የኤለንን ትዊተር ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተቀባብለውታል። ይህ የትዊተር መልእክት በዘመናዊ ስልክ የተነሳ ሲኾን የሆሊውድ ታዋቂ ተዋንያት እና ተዋንያን ይገኙበታል። ትዊተሩ የሚከተለውን አጭር መልእክትም ይዟል። «የብራድሌይ እጅ ረዥም ከኾነ ብቻ። የምንጊዜም ምርጥ ፎቶ #ኦስካርስ» የሚል። በፎቶው ላይ ራሷ የኦስካር አስተናጋጇ ኤለን ደጄነርስን ጨምሮ፣ ታዋቂዎቹ የሆሊውድ የፊልም ተዋንያን እነ ብራድ ፒት፣ ፎቶውን ያነሳው ብራድሌይ ኩፐር እና ሌሎችም ድንቅ ተዋንያን በፈገግታ ያታያሉ።

ሌላው በትዊተር የ10 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለየት ያለው ክስተት የመፀው አብዮት በመባል በሚታወቀው የዐረብ ዓለም አብዮት ወቅት የታየው ነው። በዐረብ አብዮት ወቅት የአደባባይ ሰልፍ አስተናጋጆች በተደጋጋሚ እና በስፋት ትዊተርን ለሰልፍ ማስተባበሪያ ተጠቅመውበታል። በወቅቱም ኾነ ከዚያም በኋላ መደበኛ የመገናኛ አውታርን የሚጠቀሙ ጥቂት የማይባሉ የዓለማችን ግዙፍ የመገናኛ አውታሮችም መረጃዎችን ከትዊተር መልእክት መሠረት አድርገው ሲወስዱ ተስተውለዋል።

የትዊተር መለያ የወፍ ዓርማ ከመሰላል ማለትም ሀሽታግ ጋር
የትዊተር መለያ የወፍ ዓርማ ከመሰላል ማለትም ሀሽታግ ጋርምስል picture-alliance/dpa/C.Charisius

ኢትዮጵያ ውስጥ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች መሰላል የሚሉትን ምልክት ማለትም ሀሽ ታግ ትዊተር መጠቀም መጀመሩ ለማኅበረሰባዊ ፋይዳ ላቅ ያለ አስተዋጽዖ አበርክቷል። ከፊት ለፊቱ መሰላል ወይንም ሀሽታግ ተደርጎ የሚላክ ማንኛውም መልእክትን በዛ ርእስ ለሚፈልገው የትዊተር ተጠቃሚ በቀላሉ ይገኛል። በእርግጥ ሀሽ ታግ በትዊተር ዘንድ የተዋወቀው ሆን ተብሎ ሳይኾን በአጋጣሚ ነበር። ከዛሬ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ሀሽ ታግን ያስተዋወቀው 20 ያኽል ተከታዮች የነበሩት ስቴቨን ማርክስ የሚባል ሰው ነው። ኤን ቢ ሲ የተሰኘው የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያ በወቅቱ ያስተላለፈው የለንደን ኦሎምፒክ የቴሌቪዥን ስርጭት ያበሳጨው ስቴቨን ቴሌቪዥን ጣቢያው ተሰናክሏል ለማለት #NBCFail በሚል ሀሽ ታግ ይጠቀማል። በሦስት ቀናት ውስጥ በተመሳሳይ ቃል ሀሽታግ የተደረገው ከ20,00 በላይ ልቆ ስቴቨንን በጥቂት ቀናት ውስጥ ዝነኛ አድርጎታል።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ የትዊተር ተጠቃሚዎች በመደበኛነት ሀሽታግን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ለአብነት ያኽል በናይጀሪያው አክራሪ ታጣቂ ቡድን ቦኮሃራም ታፍነው የተወሰዱ ልጃገረዶች እንዲመለሱ በተጀመረው ዘመቻ ጥቅም ላይ የዋለው «ልጆቻችንን መልሱ» #bringbackourgirls የሚለው ሀሽታግ ይታወሳል። ሁለት አሸባሪ ወንድማማቾች በፈረንሳዩ የስላቅ መጽሄት ሻርሊ ኤብዶ ላይ ባደረሱት የሽብር ጥቃት እና ግድያ መላው ዓለም ሐዘኑን ለመግለጥ የትዊተር ሀሽታግን ተጠቅሟል። በወቅቱ ለተገደሉት ጋዜጠኞች አጋርነት ለመግለጥም «እኔም ሻርሊ ነኝ» የሚል በፈረንሣይኛ የተፃፈ #jesuischarlie የተባለው መልእክት በዓለም አራቱም ጥግ ተሰራጭቶ ነበር። እንደነዚህ አይነት መሰላል ያለባቸው የሀሽታግ መልእክቶች በአንድ ቀን ውስጥ የተመልካቹ ቁጥራቸው እጅግ ሲበራከት በቁጥር ከፍተኛ ተመልካች ያለውን መልእክት ትዊተር ለመወያያነት ወደፊት ገጹ ያመጣዋል። ወይንም በትዊተር አባባል ትሬንድ ያደርገዋል።

ትዊተር በሂደት አንዳንድ ለውጦችን ማከናወን እንደሚሻ ይፋ አድርጓል። የትዊተር የጀርመን ዋና ሥራ አስኪያጅ ቶማስ ደ ቡኸር እንደሚሉት ከኾነ ትዊተር በሚያደርጋቸው ለውጦች ተጠቃሚው ደስተኛ ነው።

«ምንም አይነት ለውጥ እናድርግ የሰዉ ጉጉት ምንጊዜም እጅግ ከፍ ያለ ነው። ለውጡን በምናደርግበት ወቅትም አስቀድመን የምናየው ትዊተር ምን ያኽል ለሰዎች ጠቃሚ መኾኑን ነው። እናም ለውጡን ተግብረን በምንቃኝበት ወቅት የምናየው ሰዉ አብዛኛውን ጊዜ አሃ ይኼማ ለእኔ ጥሩ ነው ማለቱን ነው።»

የትዊተር መለያ ዓርማ፥ በሰማያዊ መደብ ላይ ነጭ ወፍ
የትዊተር መለያ ዓርማ፥ በሰማያዊ መደብ ላይ ነጭ ወፍምስል picture alliance/ANP

ትዊተር በ10 ዓመት ጉዞው የመገናኛ ዘርፉ (communication) እና የማኅበረሰብ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያስከተለው። እንደ ፌስቡክ ካሉ ከሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች ጋር በመኾን መደበኛው የመገናኛ አውታር ስልት ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማሳደር ችሏል።

ቀደም ሲል እንደ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ካሉ ከመደበኛ መገናኛ አውታሮች ወደ ተጠቃሚው ማለትም፦ አድማጭ፣ ተመልካች ወይንም አንባቢ በቀጥታ መንገድ ይተላለፍ የነበረው የመልእክት ማስተላለፊያ ሥርዓት መልኩን ቀይሮ ተጠቃሚውም የዜና እና የመረጃ ምንጭ አካልም መኾን ችሏል፤ እነ ትዊተር እውን በመኾናቸው የተነሳ። ይኽ በዘመናችን የመረጃ ልውውጥ ዘርፍ ታላቅ የሚባል እመርታ ነው። የትዊተር የ140 ፊደላት እና ምልክቶች ገደብን የኦንላይን ባለሙያ እና ጋዜጠኛው ማሪዮ ሲክስቱስ ሀሳብ ገዳቢ ቢኾንም በጥልቀት ለማሰብ ግን ያስገድዳል ሲሉ ይገልጡታል።

«ትዊተርን አሁንም ድረስ የምጠቀመው ሀሳቤን ለማጠናከር ነው። ለትዊተር ሲኾን አተኩሬ ነው የማስበው። ትዊተርን ባለፉት 10 ዓመታት ተረዳሁት እንደምለው ከኾነ ይኼ የ140 ፊደላት እና ምልክቶች ገደቡን ነው። በዛ ሰው ሀሳቡን እንዲጨምቅ ይገደዳል። በእርግጥ በትዊተር ሰው ሀሳቡን ግልጽ በኾነ መልኩ አቀናብሮ መግለጥ ሲችል እና መልእክቱን ሲያስተላልፍ የበለጠ ስኬታማ ይኾናል። ያም በመኾኑ ትዊተር ሰፊ ዓምደ-መረብ ገጽታ እንዲኖረው አልሻም።»

በአንዳንድ የኦንላይን ባለሙያዎች ዘንድ የ140 ፊደላት እና ምልክቶች ገደብ ሊነሳ ነው የሚል ጭምጭምታ አልፎ አልፎ ይሰማል። በእርግጥ የትዊተር መሥራች ጄክ ዶርሲ ይህን ጭምጭምታ ውድቅ ቢያደርገውም ማለት ነው።

ትዊተር በሂደት ካደረጋቸው ዋና ዋና ለውጦች መካከል የቪዲዮ መልእክቶችንም ማካተት መቻሉ በዋናነት ይጠቀሳል። ይኽን ተከትሎ ትዊተር ካለፈው ዓመት አንስቶ ፔሪስኮም የተሰኘ የቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አገልግሎትም ጀምሯል። በማንኛው ቦታ ኾኖ ማንኛውንም ክስተት በቪዲዮ በቀጥታ ማሰራጨት ያስችላል ትዊተር የገዛው ፔሪስኮም አገልግሎት።

የትዊተር መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አሜሪካዊው ጄክ ዶርሲ
የትዊተር መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አሜሪካዊው ጄክ ዶርሲምስል picture alliance/epa/A. Gombert

ይኽ ሁሉ ሲሆን ትዊተር አሁንም ድረስ ቀጥተኛ የማስታወቂያ ገቢ የለውም። ስለዚህም ድርጅቱ አንዳንድ የትዊተር አባላት በሚያደርጉት የስፖንሰር ክፍያ ገቢ ለማግኘት እየሞከረ ነው። ትዊተር በገበያው ላይ ለመቆየት በእርግጥም እንደ ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ስናፕሻት፣ ኢንስታግራምን የመሳሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎች አሉበት።

በጄክ ዶርሲ "stat.us" በሚል ተጀምሮ ከ“Twttr” ወደ "Twitter" የተቀየረው ይኽ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ከምድራችንም አልፎ ከኅዋ የምርምር ጣቢያም መልእክት የሚተላለፍበት ስልት መኾን ችሏል። ከዛሬ 6 ዓመት በፊት አሜሪካዊው ጠፈርተኛ ቲሞቲ ጆን ክሪመር ከናሣ የኅዋ ጣቢያ ቀጣዩን መልእክት በማስተላለፍ ከምድራችን ውጪ የተላለፈ የመጀመሪያው የትዊተር መልእክት ተብሎ ተመዝግቦለታል። መልእክቱ እንዲህ ይላል፦« ሰላም ትዊተረኞ! አሁን ከዓለም አቀፍ የኅዋ ጣቢያ በቀጥታ የትዊተር መልእክት ማስተላለፍ ችለናል። ከኅዋ የመጀመሪያው ትዊተር! ተጨማሪ እንልካለን የእናንተን ትልኩ?» ይላል። ትዊተር በ10 ዓመት ቆይታው ከአንድ ሰው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጠቀሙት፤ ከምድር አልፎ ኅዋ ላይ የደረሰ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ መኾን ችሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ