1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪካ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8 2003

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብን አሻፈረኝ ብለው የከረሙት የኮትዲቯሩ ሎረን ባግቦ ከተደበቁበት ምሽጋቸው የተያዙት በዚሁ ሳምንት ነበር። ሊቢያ የቀውስ ቀጠና እንደሆነች አለች አሁንም።

https://p.dw.com/p/RIOK
ምስል dapd

ሰላም ጤና ይስጥልን?የዛሬው ትኩረት በአፍሪካ በእርግጥ ኮትዲቯርንና ሊቢያን መርጧል መሳይ መኮንን ነኝ መልካም ቆይታ።

ባለፈው ሰኞ በመንግስታቱ ድርጅት የኮትዲቯር አምባሳደር የአራት ወሩ በትራጄዲ የተሞላው ድራማ መጠናቀቁን የገለጹት ባግቦ ከተሸሸጉበት ጎሬያቸው ከነባሌቤታቸው እንደተያዙ ነበር። ጥቅምት ተካሂዶ በነበረው ምርጫ በቀድሞው የዓለም ባንክ ከፍተኛ ሃላፊ በነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲ ተፎካካሪያቸው አላሳኔ ዋታራ የተሸነፉት ሎረን ባግቦ እኔ ነኝ ያሸነፍኩት ብለው ሲያውጁ ያቺ በካካዋ ምርት የዓለም ገበያ እምብርት የሆነችውን ኮትዲቯር ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊከቷት እንደሚችሉ ስጋት ማስጠንቀቂያው ይሰማ የነበረው ያኔውኑ ነው። እንደተፈራው እንደተሰጋውም አልቀረም። የባግቦ ደጋፊዎችና ታማኝ የሆነው ጦራቸው አቢጃንን የሰላማዊ ህዝብ የስቃይ የመከራ ሥፍራ አደረጓት። ሰው ይገደል ይሰደድ ጀመር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቃዋሚውን ህጋዊ የኮትዲቯር መሪ ብሎ እውቅና ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ባግቦ ስልጣኑ እንዲያስረክቡ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት እስከ ማዕቀብ መጣል ያሉ እርምጃዎችን ቢወስድም፡ ባግቦን የሚያንበረክክ ሊሆን አልቻለም። የሙጥኝ ካሉበት መንበረ ስልጣናቸው በሃይል ለማውረድ ነገ ዛሬ እያለ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በሚያመነታበት ጊዜ ድንገት የተቃዋሚው አሸናፊ ፕሬዝዳንት ደጋፊ የሆኑ አማጺያን እየገሰገሱ ባግቦ አፍንጫ ስር ተጠጉ። በአንድ ሳምንት። ከቤተመንግስታቸው ውስጥ ጉድጓድ አስምሰው ባዋቀሩት ምሽግ ውስጥ ሆነው ሊፋለሙ የቆረጡት ባግቦ በመጨረሻም ታሪካዊ በሆነ ውርደት እጃቸውን ሰጡ። የአራቱ ወራቱ ደም ያፋሰሰው ፍጥጫም ለጊዜው መቋጪያውን አግኝቷል። በክብር እንዲለቁ ሲለመኑ የከረሙት ባግቦ መጨረሻቸው አሳፋሪ ውርደት ሆኖ ተጠናቀቀ። ሰኞ ለት ከተደበቁበት የተያዙት ሎረን ባግቦ መራርዋን ጽዋ ተጎነጩ። ባግቦን ለመያዝ በተደረገው ዘመቻ የተሳተፈና ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የዋታራ ወታደር ባግቦ ሊያዙ በነበረበት ቅጽበት እባካችሁ አትግደሉኝ ማለታቸውን ገልጿል። የዚያኑ ለት አዲሱ የኮትዲቯር መሪ ሆነው ሥራ የጀመሩት አላሳኔ ዋታራ የባግቦ ደጋፊዎች በፍርሃትም ይሁን በበቀል ተነሳስተው ጠብ እንዳይጭሩ ወዲያውኑ ጥሪ አድርገዋል። ዋታራ ባግቦና ሚስታቸው ለፍርድ ይቀርባሉ ሲሉም ተናግረዋል።

Elfenbeinküste Alassane Ouattara
አላሳኔ ዋታራምስል AP

የሎረን ባግቦ መያዝ፡ በእርግጥ አምባገነንነት መጨረሻው ክፉ አወዳደቅ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዋል። የጀርምን መንግስት የአፍሪካ ጉዳይ ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር እንደሚሉት የባግቦ ፍጻሜ ለኮትዲቯር ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲውም ድል ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በመጨረሻም ዲሞክራሲ አሸነፊ ሆነ ሲሉ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ዋዴ ደግሞ ይህ ለአፍሪካ ትልቅ ድል ነው ብለዋል። አሜሪካ የባግቦ ፍጻሜ ለጨቋኝ መሪዎች የማስጠቀቂያ ደውል እንደሆነ አስታውቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን የህዝብን ድምጽ መንጠቅ እንደማይቻል ያሳየ ሽግግር ብለውታል ክስተቱን።

"ይህ ሽግግር ለአምባገነኖችና ጨቋኝ ለሆኑ የአፍሪካና ሌሎች ሀገራት መሪዎች ጠንካራ የሆነ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። በምርጫ ወቅት የህዝባቸውን ድምጽ ማፈን እንደማይቻላቸው፡ አሻፈረኝ ብለው በስልጣን ለመቆየት ቢሞክሩ መዘዙ ከባድ እንደሚሆንባቸው በግልጽ ያሳየ ክስተት ነው። "

በእርግጥ ባግቦ ለአራት ወራት ሲያስቸግሩ ከርመው መጨረሻቸው አሳፋሪ ሆኖ ተጠናቋል። አላሳኔ ዋታራም ቤተመንግስት ገብተዋል። ኮትዲቯር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ ዳር ዳር እያለች ናት። ሆኖም በቀላሉ የመረጋጋቷ ነገር ብዙዎችን ጥርጣሬ ውስጥ ከቷል። ባግቦን ለመያዝ የተደረገው ዘመቻ ራሱ አዲስ ውዝግብን ፈጥሯል። ሩሲያ የመንግስታቱ ድርጅት ከዓላማው ያፈነገጠ ወገንተኝነት አሳይቷል። ባግቦን በመያዙ ዘመቻ በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል በማለት ውንጀላ አቅርባለች። ይህም የጸጥታው ምክርብ ቤትን በቀጣይ ፍጥጫ ውስጥ ይከተዋል የሚል ስጋት አሳድሯል። የመንግስታቱ ድርጅት በእርግጥ የሩሲያን ውንጀላ አስተባብሏል። ባግቦን የያዙት የዋታራ ሃይሎች ናቸው። የእኔ እጅ የለበትም ሲል አስታውቋል። በሌላ በኩል ሥልጣናቸውን እያደላደሉ ያሉት አላሳኔ ዋታራ ባግቦን በሰሜናዊ ኮትዲቯር በሚገኝ አንድ ሚስጢራዊ ቦታ በቁም እስር እንዲሆኑ አድርገው ሀገራቸው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንድትመለስ እየጣሩ ናቸው። ትምህርት ቤቶች ከ10ቀናት በኋላ እንዲከፈቱ አዘዋል። በሁለት ወራት ውስጥም ሁሉም ሀገሪቱን የተረጋጋች ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የስብዓዊ መብት ኮሚሽን አሽናፊው የዋታራ ሃይል የበቀል እርምጃ በመውሰድ ሀገሪቱን ዳግም ወደ እልቂት ሊወስዳት የሚችል ፍንጮች ታይቶኛል ሲል ስጋቱን ገልጿል። በእርግጥ የሎረን ባግቦ ወታደሮችና ደጋፊዎች ላይ አልፎ አልፎ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ኮትዲቯር ተመልሳ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳታመራ ፍራቻው ብዙዎች ዘንድ አለ።የባግቦ ቀጣይ እጣፈንታም ሌላው ዋታራን የሚጠብቅ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ይነገራል። ለዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀሎች ተመልካች ፍርድ ቤት ተላልፈው የመሰጠታቸው ነገር በእርግጥም ያበቃለት የሚጠበቅ እርምጃ ነው ተብሏል። ፈረንሳይ ፓሪስ ነዋሪ የሆነችው የባግቦ ሴት ማሪ አንቶይኔተ ሲንግሌተን ለአባትዋ ጥብቅና ለማቆም በፓሪስ አንድ የህግ ቡድን አቋቁማ ልትሟገትላቸው መዘጋጀቷም ተሰምቷል። ለጊዜው የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀሎች ተመልካች ፍርድ ቤት በባለፉት አራት ወራት የተፈጸመውን ሰብዓዊ ጥፋት ሊያጣራ መሆኑን አስታውቋል። የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ህግ ሊዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ እንደገለጹት ከ900 በላይ ሰዎች ያለቁበትና በሺዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ድርጊት ለመመርመር ዝግጅቱ ተጠናቋል።

በሊቢያ የ42 ዓመቱን የኮነሬል ሞአመር ጋዳፊን መንበረ ስልጣን የነቀነቀው አመጽ ከተጀመረ ትላንት ሁለት ወሩን ደፈነ። ቤንጋዚና ትሪፖሊ እንደተፋጠጡ፡ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አንድ አቋም መያዝ እንደተሳነው፡ በዚህም መሃል የሊቢያ ምድር ከሰማይ በጦር ጄቶች፡ ከመሬት በከባድ መሳሪያዎች እሳት እንደከሰለ ይኧው፡ ሶስተኛ ወሩን ዛሬ አንድ አለ። በሳምንቱ ክፍተኛ ትንቅንቅና ከባድ ውጊያ የተካሄደባት ሚሱራታ የተሰኘች ከተማ ከመቼውም ጊዜ በላይ እልቂት እየተፈጸመባት እንደሆነ ይነገራል። የጋዳፊ ሃይሎች ትላንት ወደ ሚሱራታ 120 ሮኬቶችን መተኮሳቸውንና ቢያንስ 8 ሰዎች ገድለዋል። በሚሱራታ እየተፈጸመ ያለው ሰብዓዊ ጥፋት ዓለም ዓቀፍ የዕርዳታና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው።የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዳፊ የሚሱራታ ነዋሪዎችን በክላስተር ቦምብ እየደበደቡ ነው ሲል ከሷል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ሀገራት ማህበር ኔቶ በሚሱራታ እየተፈጸመ ያለውን እልቂት ማስቆም ካልቻለ፡ የዘር ማጥፋት ሊከናወን እንደሚችል አማጺያን አስጠንቅቀዋል። እንደ ብዙዎች እምነት የኔቶ አባል ሀገራት አንድ ወጥ አቋም አለማያዛቸው ለጋዳፊ ትልቅ እፎይታ ሆኗል። ጥምሩን ጦር በበላይነት ስትመራ የነበረችው አሜሪካ ከባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ አንስቶ ዘመቻው ሙሉ በሙሉ በኔቶ እንዲመራ ካደረገች በኋላ የሊቢያ ነገር መላ ቅጥ የጠፋ ሆኗል፡፡የኔቶ ዘመቻ እንዲህ ውጥረት ውስጥ እያለ ግን አባል ሀገራቱ እርምጃው ተገቢና ህጋዊ ነው ብለው መሟገታቸውን አላቆሙም።የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊሊያም ሀግ ከዚህ አንጻር ጠንከር ያለ አቋም ይዘዋል።

ፈረንሳይ ኔቶ ዘመቻውን በብቃት እየመራው አይደለም ስትል ቅሬታዋን አቅርባለች። የኔቶ አባል ሀገራት ለሁለት ተከፍለው አንድ አቋም ላይ መድረስ ባለመቻላቸው መፍትሄው ከወታደራዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ወደ ሚሆንበት ምዕራፍ የደረሰ ይመስላል። በተለይም የአሜሪካ ከዘመቻ ቀስ እያለች መንሸራተቷ ፈረንሳይንና እንግሊዝን አስጨንቋቸዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ የሊቢያ ጉዳይ በውጊያውም ሆነ በዲፕሎማሲያዊው መስኮች ጠንካራ እንቅስቃሴዎች የተካሄዱበት ነበር። ብራዚል፡ሩሲያ፡ህንድ፡ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ቡድን ባወጣው መግለጪ የሃይል እርምጃው በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። ሩሲያ በተናጠል ኔቶ የመንግስታቱ ድርጅትን የሃላፊነት ወሰን የተላላፈ እርምጃ እየወሰደ ነው ስትል ከሳለች።በእርግጥ ኔቶ ከውስጥም ከውጭም ተወጥሮ ዘመቻውን በመጠኑም ቢሆን ማካሄዱን አላቆመም። የኔቶ ዋና ጸሀፊ አንደርስ ራስሙሰን ጋዳፊ ስልጣን ላይ እያሉ ሊቢያውያን ሰላም ያገኛሉ ማለት የማይታሰብ ነውና ዘመቻው ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።

«ኔቶ ዘመቻውን አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ ነው። በሰላማዊ ሊቢያውያን ላይ ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ እስካለ ድርስ ዘመቻው የሚቆም አይደለም። እናም ጋዳፊ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ያ ስጋት ይጠፋል ማለት አይቻልም።»

የኔቶ የሊቢያ ዘመቻ እንዲህ ውሉ በጠፋበት ሰሞን ኳታር ዶሃና ግብጽ ካይሮ የሊቢያ ጉዳይ አጀንዳ የሆኑባቸው ስብሰባዎች ተካሂደዋል።የካይሮው የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ተፋላሚ ሃይላት ንግግር ስለሚጀምሩበት ሁኔታ የመከረ ቢሆንም እስከአሁን ያን ለማድረግ የተጀመረ ጥረት የለም። በአፍሪካ ህብረት በኩል የቀረበውን የድርድር ሀሳብንም ቤንጋዚዎች አንቀበልም ብለዋል። በእርግጥ ምዕራብውያን አንድ መሆን አለመቻላቸው የሊቢያውያንን ጣር እንዲረዝም አድርጓል። አሜሪካ የኔቶ አባል ሀገራት ህብረት እንዲፈጥሩ ጥሪ አድርጋለች።በእርግጥ አሜሪካ የዘመቻው ፊት አውራሪ ለመሆንና ተጨማሪ ሃይል ለኔቶ እንድትሰጥ እንዳቀደች በበርሊኑ የኔቶ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተገኙት ሂላሪ ክሊንተን ፍንጭ መስጠት አልፈለጉም። በፈረንሳይ በኩል የተጠናከረ ወታደራዊ ጥቃት እንዲጀመር ውስጥ ውስጡን እየተካሄደ ያለው ግፊት በእርግጥ አይሏል። አማጺያን ኔቶ የሚያደርገው ዘመቻ በቂ ባለመሆኑ ነገሮች እየከፉ መጥተዋል በማለት ምርር ያለ ወቀሳ ማሰማታቸውን አላቋረጡም። ምዕራባውያን ሀገራት አለበለዚያ እንዲያስታጥቋቸው፡ ስልጠናም እንዲሰጧቸው፡ ጋዳፊን የማስወገዱ ትግል ከዚያ በኋላ የነሱ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ያ ካልሆነ፡ ምዕራብያውያኑ መሳሪያና ስልጠና ካላቀረቡላቸው ወዳጆቻችን እንጠይቃለን ሲሉ አማጺያን አቋማቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል። ለጊዜው ኳታር አማጺያኑን እስከ አፍንጫቸው ላማስታጠቅ ፍላጎቱም አቅሙም ያላት ሀገር ናት ተብሏል። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲህ በልዩነት ማዶ ለማዶ ተራርቆ ባለበት በዚህን ጊዜ ሊቢያ ከሰነበተችበት ዕልቂት ለአፍታም እፎይ አላለችም። ዛሬም ሚሱራታ በቦምብ እየተደበደች ናት።