1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትራንስ አትላንቲኩ የነጻ ንግድ ድርድር

ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2005

የአውሮፓ ሕብረትና ዩ ኤስ አሜሪካ ትናንት አየርላንድ ውስጥ ቡድን-ስምንት በመባል የሚታወቀው የሰባቱ ሃያላን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታትና የሩሢያ መሪዎች ጉባዔ አኳያ ትራንስ አትላንቲክ የነጻ ንግድ ውል ለማስፈን ድርድር ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/18rrn
ምስል Getty Images

የሁለቱ ወገን የነጻ ንግድ ክልል ሃሣብ ታላቅ የኤኮኖሚ ጥንካሬ ተሥፋን የጣለውን ያህል በተለይም በዚህ በአውሮፓ በአንዳንድ ወገኖች ጥርጣሬና ስጋትን ማስከተሉም አልቀረም። ትራንስ አትላንቲኩ የነጻ ንግድ ጽንሰ-ሃሣብ እርግጥ አዲስ ባይሆንም የአሁኑን ያህል እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ቀደም ያለ ጊዜ አይታወስም። በጎርጎሮሳውያኑ 2008 ዓ-ም ከአሜሪካ ተነስቶ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ምድራችንን ያዳረሰው ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በተለይ የጎዳው የበለጸጉትን ምዕራባውያን መንግሥታት መሆኑ በግልጽ የታየና የሚታይም ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል አዳጊው ዓለም በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ የደረሰበትን የኤኮኖሚ ፈተና በፍጥነት በመቋቋም ከችግሩ ሲያገግም ቻይናን የመሳሰሉት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙ ሃገራት በንግድና በኤኮኖሚ እያየሉ መጥተዋል። ይህም በዓለም ላይ ያለውን የሃይል አሰላለፍ በጣሙን መቀየሩ አልቀረም። ዛሬ ብራዚልን፣ ሩሢያን፣ ሕንድን፣ ቻይናንና ደቡብ አፍሪቃን የሚጠቀልለውን ብሪክስ በሚል አሕጽሮት የሚጠራ ስብስብ ብንወስድ ይሄው በዓለም ንግድ ላይ ያለው ድርሻና የሃብት ክምችት እጅግ ከፍተኛ ነው። የቡድን-ሃያ ሚናም እንዲሁ ቀውሱን ተከትሎ እያደገ መምጣቱ ይታወቃል።

Freihandelsabkommen Filmförderung
ምስል Bernd Sobolla

እንግዲህ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በመካከላቸው ነጻ የንግድ ውል በማስፈን በተለይም ቻይናን ለመቋቋም ማለማቸው ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። በዓለምአቀፉ ንግድ ላይ መልሶ በመጠናከር ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ይፈልጋሉ። እርግጥም የነጻ ንግዱ ክልል ቢሰፍን እስካሁን ጠንካራ የነበረው ትራንስ አትላንቲክ ግንኙነት ይበልጥ ጥልቅ እየሆነ እንዲሄድ ማድረጉ እንደማይቀር የአሜሪካው ፕሬዚደንት የባራክ ኦባማም ዕምነት ነው።

«የአውሮፓ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ግንኙነት በዓለም ላይ በሁል-አቀፍነቱ ሰፊው ነው። ግማሹን የዓለም ገቢ የሚጠቀልል ሲሆን በያመቱ የሚደረገው ንግድና የሚሰጠው አገልግሎት ዋጋ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል። አንዱ በሌላው ወገን የሚያደርገው መዋዕለ-ነዋይም በአራት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን ከአትላንቲክ ባሻገር በሁለቱ ክፍል-ዓለማት የ 13 ሚሊዮን የሥራ ቦታዎች ዋስትና ነው። እናም ሽርክናው ቢጠናከር ትስስሩን ይበልጥ ጥልቅ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም»

የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ቀረጥንና የተለያዩ የጥራት መስፈርቶችን የመሳሰሉ የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ ሃሣቡን ዕውን ለማድረግ ይፈልጋሉ። በትራንስ አትላንቲኩ የነጻ ንግድ ውል ድርድር መጀመር ደግሞ የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክልም ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የገለጹት። ዕርምጃው ዕድገትን ለማራመድ እንደሚበጅ ተናግረዋል።

«የዚህ መሰሉ የነጻ ንግድ ውል ሃሣብ ትልቅ ደጋፊ ነኝ። ልምዳችን ያሳየን ይህን መሰሉ ውል በሰፈነበት ቦታ ሁሉ ዕድገት፣ ግድና ተሃድሶ እንደሚያብብ ነው»

Freihandelsabkommen Filmförderung
ምስል R.Rivas/AFP/GettyImages

ስምምነቱ ቢሰፍን በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ብቻ የነዋሪውን ንጹህ ገቢ በነፍስ-ወከፍ በ 5 ከመቶ ሊያሳድግ እንደሚችል በጉዳዩ የቀረበ ጥናት አመልክቷል። በዚህ በጀርመን የቤርትልስማን ድርጅት ጥናት አያይዞ እንዳመለከተው በተለይ ደግሞ ከአሥር በመቶ በላይ በሆነ መጠን የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት ብሪታኒያና ዩ ኤስ አሜሪካ ናቸው። በሌላ በኩል ታዳጊ ሃገራት፤ እንዲሁም የአሜሪካ የቆዩ የንግድ ሸሪኮች ሜክሢኮና ካናዳ ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለማንኛውም የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ የነጻ ንግድ ውል ለሕብረቱ የሚኖረውን ጠቀሜታ ከማመልከት ወደ ኋላ አላሉም። በእርሳቸው ዕምነት ውሉ ገቢር ቢሆን የአውሮፓን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በ 0,5 ከመቶ ከፍ ሊያደርግ የሚችል ነው። ይህም ብዙ ሚሊያርድ ገቢ፤ አያሌ አዳዲስ የስራ ቦታዎች ማለት ሲሆን በኤኮኖሚ ዕድገት ችግር ተወጥሮ በቆየው በአውሮፓ ለሰሚው ጆሮ እጅጉን የሚጥም ነው።

« በአንድነት በዓለም ላይ ታላቁ የሆነውን የነጻ ንግድ ክልል ለመፍጠር እንፈልጋለን። ስምምነቱ ሰፍኖ በተግባር መተርጎም ከያዘ የአውሮፓ ኤኮኖሚ ከአጠቃላይ ምርቱ አንጻር 0,5 ከመቶ ዕድገት የሚያስቆጥር ይሆናል። ይህም በሌላ አነጋገር በያመቱ በብዙ ቢሊዮን ኤውሮ የሚቆጠር ገቢ አያሌ አዳዲስ የስራ ቦታዎች ማለት ነው»

ከረጅም ጊዜ አንጻር ደግሞ በምርታማነት ማደግ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትም ይቻላል። ይህን የሚሉት የሕብረቱ የንግድ ኮሜሣር ካሬል-ዴ-ጉህት ሲሆኑ ጉዳዩ ኩባንያዎችንና ፖለቲከኞችን የሚያበረታታ ነው። እርግጥ በሌላ በኩል በብራስልስ የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት ውክልና በአውሮፓና በአሜሪካ ካዝና መሟጠጥ የተነሣ ችግሩን በመንግሥታት ደረጃ መወጣት እንደማይቻል ያስገነዝባል።

Freihandelsabkommen Filmförderung
ምስል imago stock&people

ለነገሩ ለዚህም ነው ሁለቱ ወገኖች ነጻ ንግድን ለማስፈን መጣር የሚኖርባቸው። በተለይ በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረው የጀርመን ኤኮኖሚ ደግሞ በዚህ ይበልጥ ተጠቃሚ ነው የሚሆነው። እንግዲህ ከኤኮኖሚ ስሌት ቢነሱ ሁሉም ነገር የነጻውን ንግድ ውል የሚደግፍ ይሆናል። ነገር ግን በብራስልስ የብሩገል የኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ አንድሬ ሣፒር እንደሚሉት የአውሮፓው ኮሚሢዮን በተሥፋ ያስቀመጠው የዕድገት አሃዝ ጭብጥ ቢመስልም ቅሉ የሕብረቱን የዕድገትና የስራ አጥ ችግር ለመፍታት በቂ አይሆንም።

በዚህ ጉዳይ ተጠራጣሪ ሆነው የሚገኙት የተጠቃሚው ጠበቆችና በአውሮፓ ፓርላማ የአረንጓዴው ወገን ፖለቲከኞች ናቸው። ፈረንሣዊው አረንጓዴ እንደራሴ ያኒክ ያዶት ለምሳሌ ወደፊት ከአሜሪካ በጂን ቴክኒክ ባሕርዩን የቀየረ ምርት ወይም በመድሃኒት የዳበረ የከብት ስጋ ወደ ሕብረቱ ገበዮች እንዳይገባ ያስጠነቅቃሉ። በእርግጥም የምግብ መርት ደህንነት ዋስትናን በተመለከተ ሁለቱ ወገኖች በጣሙን የተራራቁ ናቸው።

በዳታ ጥበቃ ረገድም እንዲሁ! ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ የጸጥታ ተቋማት የአውሮፓ ዜጎችን የኢንተርኔት የግል ዳታዎች በሰፊው ይዘዋል። በአውሮፓ ፓርላማ የሶሻሊስቱ ወገን መሪ ሃነስ ስዎቦዳ ሰሞኑን አመኔታ ጠፍቷል ሲሉ ነበር የተናገሩት። እንደራሴው የአውሮፓ ሕብረት ለንግድ ውሉ ሲል የዳታ ጥበቃ ዋስትናውን አሳልፎ መስጠት የለበትም ባይ ናቸዉ።

«ዳታውን በተመለከተ ዋስትና እንፈልጋለን። የዳታዎች ጥበቃ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ለመስማማት ስንል በቀላሉ መስዋዕት የምናደርገው ነገር አይደለም»

ከዚሁ ሌላ ባሕላዊ ሃብቶችን እንበል ፊልምን በተመለከተ በአውሮፓና በአሜሪካ ያለው ግንዛቤ የተራራቀ ነው። የፈረንሣይ የኪነት ሰዎች፣ ፊልም ሰሪዎችና ተዋንያን የአውሮፓ ባሕል ለሆሊዉድ እንዳይቸበቸብ ሲሉ የፊልሙ ኢንዱስትሪና መሰል ዘርፎች ከንግድ ድርድሩ እንዲወጡ ፍሬያማ ግፊት ለማድረግ በቅተዋል። የአውሮፓ ብዙ-ወጥ ፊልሞች በሆሊዉድ የገንዘብ ልዕልና መፎካከር አቅቷቸው እንዳይጠፉ ትልቅ ስጋት ነው ያለው።

የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ሚኒስትሮች ለትራንስ አትላንቲኩ የነጻ ንግድ ውል ድርድር የበኩላቸውን ውሣኔ ለማስፈን በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባ ይሄው አከራካሪ ርዕስ ሆኖ ነበር። ለማንኛውም ድርድሩን በተመለከተ የአውሮፓው ፓርላማ ዘጋቢ ቪታል ሞሬይራ እንዳሉት በመሠረቱ የባሕል እጦት ፍርሃቻ ሊኖር አይገባም።

«የአውሮፓ ብዙ-ወጥ ባሕል ለድርድር አይቀርብም። ይህ በአውሮፓ ሕብረት ውል ውስጥም በአንቀጽ ሶሥት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ነው። ታዲያ ማንኛውም ስምምነት ውሉን ካላከበረ ሕግ-መንግሥቱን የሚጻረር ይሆናል። እናም በፍርድቤት ክስ ሊያስነሣ የሚችል ጉዳይ ነው»

Symbolbild Flaggen USA & EU & Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa

አውሮፓውያን እንደሚያደርጉት ሁሉ አሜሪካም በበኩሏ ለምሳሌ የፊናንስ አገልግሎቱን ዘርፍ ለራሷ ከልላ መያዙን ትሻለች። ሁለቱም ወገን እንግዲህ ከድርድሩ ተነጥሎ እንዲቀር የሚፈልጉት ነገር አለ ማለት ነው። እናም ይህ ከሆነ ትራንስ አትላንቲኩ የነጻ ንግድ ውል ቢሰፍንስ ምን ይጠቅማል የሚል ጥያቄን ማስነሣቱ አይቀርም። በብራስልሱ መርማሪ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ በአንድሬ ሣፒር ዕምነት በድርድሩ መጨረሻ ቢበዛ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ቢነሣ፤ ምናልባትም በተወሰነ ደረጃ የጋራ ቴክኒካዊ መስፈርቶችን ማስፈኑና በባንኩ ዘርፍ የጋራ መርህን ዕውን ማድረግ ቢቻል ነው።

በሌላ በኩል እጅግ ጠቃሚ ስለሆነው ስለ ቻይና ጉዳይ በይፋ አንድም ነገር አልተባለም። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ድርድሩ የተነሣው በቻይና ምክንያትና ለቻይና አለን፤ ገና አስፈላጊ ነን የሚል መልዕክትም ለማስተላለፍ መሆኑ ግልጽ ነው።

«ይህ በእርግጥ በቻይና ላይ ያተኮረ ነገር ነው። ለቻይና ገና አሁንም ጠቃሚ ነን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ የተሰወረ አይደለም»

ለኤኮኖሚው ባለሙያ ታዲያ ይህ የኋልዮሽ ሂደትን ያህል ነው። ከዚህ ይልቅ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ በጋራ የተሰናከለውን የዓለም ንግድ ድርድር መልሶ ለማንቀሳቀስ ቢነሱና በዚያውም ቻይናን፣ ብራዚልን፣ ሕንድንና የተቀሩትን ሃገራት ከጥረታቸው ለማስተሳሰር ቢሞክሩ በተሻለ ነበር። አንዱ ያለ ሌላው ሊሆን አይችልም። ለማንኛውም አሁን በመጀመሪያ በድርድሩ የአሜሪካና የአውሮፓ ጋራ ፍላጎት ምን ያህል ገፍቶ ሊሄድ እንደሚችል መታዘቡ ይመረጣል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ