1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታሪክን የማቆየት ባህል በጀርመን

ቅዳሜ፣ ግንቦት 4 2004

ጀርመናዉያን ታሪካቸዉን አስቀምጠዉ በየግዜዉ እያስታወሱ ትዉልድን የሚያስተምሩበት ባህላቸዉ፣ የሚደነቅ ነዉ። በዚህም በአንድነት የአለምን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከሚመሩት ጥቂት ሃያላን አገራት መካከል አሰልፎአቸዋል።

https://p.dw.com/p/14sp5
ምስል picture-alliance/dpa

ጀርመናዉያን ታሪካቸዉን አስቀምጠዉ በየግዜዉ እያስታወሱ ትዉልድን የሚያስተምሩበት ባህላቸዉ፣ የሚደነቅ ነዉ። በዚህም በአንድነት የአለምን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከሚመሩት ጥቂት ሃያላን አገራት መካከል አሰልፎአቸዋል። የፋሺስት ጀርመን ጦር በአዉሮጳ ያስነሳዉ ጦርነት እና ከሰባ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያለቀበት አሰቃቂ የግፍ ጭፍጨፋ በጀርመናዉያን ብሎም በአለማችን የታሪክ ጠባሳን ጥሎ ቢያልፍም ቅሉ፣ ትዉልድ ይህን ግፍ እንዳይረሳ ጀርመናዉያን ከታሪክ ማህደራቸዉ አስቀምጠዉ ሙታን እየዘከሩ ከታሪኩ ይማራሉ። የታሪካቸዉ ጠባሳ መሆኑንም ለአለም በየግዜዉ ያሳዉቃሉ። ባሳለፍነዉ ማክሰኞ በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር /May/ 8 ማለትም ሚያዝያ ሰላሳ እለት ፣ በበርካታ አዉሮጳዉያን አገራት ዉስጥ ቀኑ በነጻነት ቀንነቱ ይታወቃል፣ በክብር ታስቦም ዉሎአል። እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ1939 ዓ,ም የጀመረዉ የጀርመን ናዚ ጦር ወረራ ከፖላንድ በመጀመር በርካታ የአዉሮጳ አገራትን የወጋበት ሁለተኛዉ የአለም ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በግፍ የተጨፈጨፈበት አሰቃቂ ጦርነት በጎርጎረሳዉያኑ ግንቦት 8 1945 ዓ,ም ያበቃበት እለት ታስቦ ዉሎአል። የዶቼ ቬለ የባህል ድረ-ገጽ ይህንኑ ቀን በማስመልከት በአዉሮጳ ሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ያበቃበት በሚል ርዕስ ስር ታሪካዊ ጉዳዮችን ዳስዋል። እኛም በለቱ ቅንብራችን ይህንን ታሪካዊ ሂደት ለማስቃኘት መርጠናል።

Brandenburger Tor Flash-Galerie
ምስል picture-alliance/ ZB

በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳይን የወረረዉ የጀርመን ናዚ ጦር ሪም በምትባለዉ በፈረንሳይ ከተማ በሚገኘዉ የጦሩ ጀነራሎቹ አማካኝነት በጎርጎረሳዉያኑ ሚያዝያ 7 1945 መማረኩን ካሳወቀ ከቀናት በኋላ በአዉሮጳ ተጋግሞ የነበረዉ ሁለተኛዉ አለም ጦርነት ከሰመ።

እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር መጋቢት16 ቀን 1945 ጀርመን መዲና በርሊን ዉስጥ ተሰበጣጥረዉ የሚገኙ ጥቂት የናዚ ጦር አባላትን ለመደምሰስ በምስራቅ ወገን የሶቭየት ህብርቱ ቀይ ጦር ወደዚያዉ መገስገሱን ያዘ። ቀዩ ጦር በምስራቅ ጀርመን ድሪስደን አቅራብያ የምትገኘዉን ቶርጋዉ ከተማን በማስለቀቅ በሩስያዉ ጀነራል በዙኮቭ ቮሮርተ የሚመራዉ ጦር በሰባት ቀን ዉስጥ በርሊን እንብርት ላይ ይደርሳል።በከተማዉ የቀሩት ጥቂት የናዚ ጦር ኃይላት ጄኔራሎች «በርሊን ከተማ ትግሏን ቀጥላለች» በማለት ፕሮፖጋንዳቸዉን በራድዮ በማሰማት፣ ነዋሪዉን በማሸማቀቅ ጦራቸዉን በማደፋፈር፣ ዉግያዉን ቀጠሉ። ከምስራቅ ወገን የሶቭየት ህብረቱ ቀዩ ጦር፤ ከምዕራብ ወገን ደግሞ የአሜሪካዉ፣ የእንግሊዙ እና የፈረንሳዩ ጦር በጥምር ወደፊት በመግፋት የናዚን ጦር በማሳደድ የጀርመን እንብርት አቅራብያ ይደርሳሉ-በኤልበ ወንዝ ዳርቻ ላይ ለመዲና በርሊን ቀረብ በምትለዉ ቶርጋዉ ከተማ ላይ ። መጋቢት 25 1945 አመቱ በሙሉ እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር ነዉ፣ እዉቁ የብሪታንያ የብዙሃን መገናኛ BBC ምዕራብ ምስራቅ በአንድነት ተገናኝተዋል ሲል ዜናዉን ለመጀመርያ ግዜ ያበስራል። በዚህም በርሊን ላይ የሶቭየት ህብረቱ ቀዩ ጦር እና አልሸነፍ ያለዉ የናዚ ጦር ከባድ እና ብዙ ወታደር የወደቀበት ጦርነት ያካሂዳሉ። የናዚ ጦር አሁንም በርሊን ከተማ በትግል ላይ መሆኑን በየግዜዉ በራድዮ በማስተጋባት ፕሮፖጋንዳዉን ይቀጥላል።

Berlin DDR Grenze Mauer Checkpoint Charlie 27.10.1961 Flash-Galerie
ምስል picture alliance/dpa

ከሶስት ቀናት በኋላ መጋቢት 25 ቀን 1945 ዓ,ም አዶልፍ ሂትለር የሶቭየት ህብረቱ ቀዩ ጦር በመዲናዋ በርሊን በሚገኝዉ የመንግስቱ መቀመጫ አቅራብያ ገፍቶ መድረሱን በድንገት ሰማ ግዜ ለረጅም ግዜ አብራዉ የነበረችዉን ፍቅረኛዉን ኤቫ ብራዉንን በህግ ያገባና ዶኒትዝ ለሚባለዉ ጄኔራሉ ስልጣኑን አሰረክቦ፣ በሩስያዉያን እጅ በህይወትም ሆነ ሞቼ መያዝን አልሻም ብሎ ሚያዝያ 30 ቀን ከቀትር በኋላ ጥይቱን ጠጥቶ ይሞታል። የረጅም ግዜ ፍቅርኛዉ እና ከጥቂት ቀናት በፊት በትዳር የተሳሰሩት ሚስቱ ኤቫ ብራዉንም ባልዋ አዶልፍ ሂትለርን ተከትላ መርዝ ጠጥታ ህይወቷን ታጠፋለች። በስተ መጨረሻም እንደ ሂትለር ፍላጎትና ኑዛዜ የእሱና የሚስቱ ሬሳ ይቃጠላል። በምስራቅ በርሊን የቀዩ ጦር ከምዕራብ ወገን የአሜሪካኑ የፈረንሳዩና የእንግሊዙ ጦር የናዚን ርዝራዦች ለማጥፋት ዘመቻቸዉን ይቀጥላሉ። በርሊን ከተማን ከናዚ ጦር ለማስለቀቅ በተደረገዉ ጦርነት ያለቀዉ የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር ፣ በሁለተኛዉ አለም ጦርነት ወቅተ በአዉሮፕላን ድብደባ ካለቀዉ ህዝብ በላይ እንደ ነበረም ተዘግቦአል። በስተመጨረሻ በጎርጎረሳዉያኑ ሚያዝያ ሁለት 1945 አመተ ምህረት በበርሊን የቀረዉ የናዚ ጦር ጥምረት ተማርኮ እጁን ይሰጣል፣ በሌላ በኩል ሂትለር መንበሩን ያወረሰዉ ጄኔራል ዶኒትዝ እንቢኝ በማለት ጦሩን ሰብቆ ምርኮኛዉን የናዚን ጦር ለማስለቀቅ በበኩሉ በምዕራቡ ወገን ካለዉ ጦር ጋር ዉግያዉን ይገጥማል። ግን አልሆነለትም ከአምስት ቀናት በኋላ ፈረንሳይን የወረረዉ የናዚ ጦር ጄኔራሎች በፈረንሳይዋ ሪም ከተማ ላይ እጅ መስጠታቸዉ ያሳዉቃሉ። በዚህም አዶልፍ ሂትለር ስልጣኑን የሰጠዉ ጄኔራል ዶኒትዝ ልክ በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ግንቦት 8 ማለትም ሚያዝያ 30ቀን 1945 ዓ,ም ከለሊቱ አምስት ሰአት ላይ ለጦሩ ተኩስ እንዲያቆሙ በራድዮ ትዕዛዙን ያስተላልፋል። በምዕራቡ ወገን በፈረንሳይዋ ከተማ ሪም ላይ የተፈረመዉ የሽንፈት ማረጋገጫ በምስራቁ ወገን እንዲተገበር በርሊን ላይ በራሽያዊዉ ስታሊን ትዕዛዝ መሠረት በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ግንቦት 9 ማለትም ግንቦት አንድ ቀን የሽንፈቱ ማረጋገጫ ዉል ዳግም ይፈርማል።

Flash-Galerie Keitel unterschreibt Kapitulationsurkunde
የናዚ ጦር ሽንፈት ማረጋገጫ ዉል በጀናራሉ ፊርማ ሲጸድቅምስል picture-alliance/dpa

በዚህም ከምዕራቡ ወገን ለሶስት ሆነዉ የናዚን ጦር ሲዋጉ የነበሩት የእንግሊዝ የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ጦር መሪዎች ከምስራቅ የራሽያ ጦር ለህዝቦቻቸዉ እና ለአለም የሰላም ዜና አበሰሩ። በሁለተኛ አለም ጦርነት በአዉሮጳ ብቻ ከስድሳ ሚሊዮን ህዝብ በላይ አልቋል። 33 ኛዉ እና የዝያን ግዜዉ የዩኤስ ፕሪዝደንት ሃሪ ትሩማን በአዉሮጳ የነበረዉ ጦርነት እንዳበቃ በአዉሮጳ የነጻነት ባንዲራ እየተዉለበለበ ነዉ ሲሉ ገለጹ።

የራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በቦን ከተማ በጀርመንኛ አጠራሩ Haus der Geschichte ማለትም የታሪክ ቤት በሚል ስያሜ አንድ ታሪካዊ ቤተ- መዘክር ይገኛል። ይህ ቤተ መዘክር ጀርመን ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ማብቅያ ጀምሮ ፣ ከጀርመን መከፋፈል እስከ አንድነትዋ እና ስለሄደችበት የእድገት ጎዳናዎች በጉልህ የሚያስቃኝ ታሪካዊ ቤተ መዘክር ነዉ። በጀርመን ከሚገኙ የጀርመንን ታሪክ ከያዙ ዋንኛ ከሚባሉት 10 ቤተ-መዘክሮች መካከል በቦን ከተማ ያለዉ አንዱ በመሆኑም ይታወቃል። ከአለም ዙርያ የሚመጡ የታሪክ ምሁራን ተማሪዎች በየቀኑ እንደሚጎበኙት እና እስካሁን ይህንን ቤተ-መዘክር ከ10 ሚሊዎን ህዝብ በላይ እንደጎበኘዉም ተገልጾአል። የሁለተኛ አለም ጦርነት ሲያበቃ በራድዮ የተደመጠዉ ዜና አንዱ ምሳሌ ነዉ።

Haus der Geschichte Museum Bonn
Haus der Geschichte በመባል በሚታወቀዉ በቦን ከተማ የሚገኘዉ ቤተ መዘክርምስል picture-alliance/dpa

ሌላዋ ጀርመናዊትዋ ኤንግ በርገር የዚህን ጦርነት ገፈት የቀመሱ የዛንግዜዋ የ14 አመት ህጻን የዛሬዋ አዛዉንት ጦርነቱን እንዲህ ያስታዉሳሉ። «ስለ ጦርነቱ ሳስታዉስ ሂትለር የፈጸመዉን ነገር ሁሉ ሳይ በጣም ይዘገንነኛል፣ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም። እንደዉ በዝያ ወቅት ከሞት አፋፍ የደረስኩበት ወቅት ሁሉ ነበር። ቦንብ ሲወረወር፣ ራሽያዎች ሲተኩሱ፣ ቤት እየሰበሩ ሲገቡ ፣ በአየር ድብደባዉ ወቅትሁሉ ከሞት አፋፍ ደርሰን ነዉ የተረፍነዉ»

ሌላዉ በየቀኑ ተማሪዎች ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት ታሪክን በመረጃ ድጋፍ እዉቀትን ለመገብየት ወደ ቤተ መዘክሩ መምጣታቸዉ የተለመደ ነዉ።የ13 እና የ 14 አመት ህጻናት ናቸዉ በትምህርት ቤት በኩል ይህንኑ ቤተ- መዘክር ለመጎብኘት መጥተዉ በስእል በድምጽ እና በሌሎች ቁሳቁሶች የተደገፈዉን የታሪክ ማህደር ይቃኛሉ። በፊልም የተደገፈዉ የታሪክ ማህደር የናዚ ጦር በተለይ በአይሁዳዉያን ላይ ያደረሰዉን የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ያሳያል። ህጻናቱ በሁኔታዉ ተገርመዋል አዝነዋልም፣ በያዙት ተንቀሳቃሽ ስልካቸዉም ፎቶ ሲያነሱ ይታያል። «የግድያ ፋብሪካዎች ፣ አንዱ ከሌላዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ። ፣ የሃያ ሚሊዮን ህዝብ ሬሳ ፣ ግማሹ ተገልዋል ግማሹ ተርቦአል፣ በሞት ጣር ላይ ያሉ ሁሉ ይታያሉ፣ ግማሹ በግፍ በአስከሬን መካከል ተጥሎ ይታያል»

Haus der Geschichte Reichtagsgebäude Feierlichkeiten zur Wiedervereinigung.
በቤተ መዘክሩ የሚገኝ የስዕል አዉደ- ርዕይምስል Haus der Geschichte

የታሪክ ቤት በጀርመንኛ ስያሜዉ Haus der Geschichte በመባል በሚታወቀዉ በቦን ከተማ የሚገኘዉ ቤተ መዘክር ጀርመን በምስራቅ እና ምዕርብ መከፈልን የያዘዉም ታሪክ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። በርካታ የጀርመን ዜጎች ታሪክን ለማወቅ ይህንኑ ቤተ- መዘክር ይጎበኛሉ። በርካታ የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ወደ ምዕራቡ ለመሻገር ሲሞክሩ ህይወታቸዉ ማለፉን የሚያሳይ በፊልም በድምፅ እና በስዕል የተደገፈ መረጃም ይታያል።

በጎርጎረሳዉያኑ ህዳር 9 1989 ዓም ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኋላ የነበረዉ ሌላዉ የጀርመን ታሪክ ምዕራፍ አበቃ። ይኸዉም ጀርመናዉያን በተባበረ ፍላጎት በአንድነት ስሜት የከፈላቸዉን ግንብ ገርስሰዉ አንድ ሆኑበት፣ ታሪክን ከጦርነት በፊት፣ በጦርነት ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ ብለዉ በታሪክ ማህደራቸዉ አስቀምጠዉ ታሪካቸዉን ከልጅ ወደ ልጅ ልጆቻቸዉ ያሳልፋሉ። ከታሪካቸዉ ይማራሉ።

ባሳለፍነዉ ማክሰኞም የናዚ ጦር ያስነሳዉ የሁለተኛዉ አለም ጦርነት ያበቃበት ታስቦ ዉሎአል። በፈረንሳይም ተሰናባቹ የፈረንሳይ ፕሪዚደንት ኒኮላ ሳርኮዚ እና አዲስ ተመራጩ የፈረንሳይ ፕሪዚደንት ፍራንሷ ኦላንድ የጀርመን ጦር የተማረከበትን እና ጦርነት ያበቃበትን እለት በጋራ መድረክ አስበዉ ዉለዋል። የጀርመናዉያን፣ ያለፈ ታሪክን በወጉ ይዘዉ ለመጭዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ የሚያደርጉት ጥረት፤ በመጀመርያ ትዉልድ በታሪኩ ያለዉን በጎም ሆነ ጥቁር ሂደት አይቶ ለማንነት ግንባታ፤ እንዲሁም ለወደፊቱ ስህተቶች የሚታረሙበትንና መፍትሄ የሚፈልጉበት ስልት ቢቀሰም የሚጠቅም ይመስለናል። ለጀርመናዉያን ታሪክን የመጠበቅ ባህላቸዉ አገራቸዉ ቀና ብላ እንድትቆም፤ ህዝቧም እንዲኮራ ከፍተኛአስተዋፅኦ ማበርከቱም አያጠያይቅም።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ