1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱሊሲሌ ማዶንሴላ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 13 2008

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ቱሊሲሌ ማዶንሴላ የዘንድሮው የጀርመናውያኑ እና አፍሪቃውያኑ ተቋም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። የ53 ዓመቷ ጠበቃ ቱሊሲሌ ማዶንሴላ የደቡብ አፍሪቃን ሕገ መንግሥት፣ የሀገሪቱን ሰላም እና የሰብዓዊ መብቶችን

https://p.dw.com/p/1Is3P
Südafrika Thuli Madonsela Public Protector spricht in einem Interview mit der AFP
ምስል Getty Images/AFP/S. Heunis

[No title]

ለማስከበር ያሳዩት አስገራሚው ቁርጠኝነት እና በሙስና አንፃር ያደረጉት ትግላቸው ለዚሁ ሽልማት እንዳበቃቸው መንበሩ በርሊን የሚገኘው በምህፃሩ «ዴ አ ኤስ» የተሰኘው የጀርመናውያኑ እና አፍሪቃውያኑ ተቋም ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል።

ጀርመናዊውድርጅት «ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል» ቱሊሲሌ ማዶንሴላን ሙስናን ጠንክr።ው በመታገላቸው «በሙስናአንፃር የቆሙ ብረታማዊቱ እመቤት » የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። በርግጥም ፣ የቱሊሲሌ ማዶንሴላ ቁርጠኝነት እንደ ብረት የጠነከረ ሆኖ ነው የተገኘው።

የቱሊሲሌ ማዶንሴላ ስራ ያልተመቻቸው አንድ የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ሚንስትር ቱሊሲሌ ማዶንሴላን የ«ሲ አይ ኤ ሰላይ» ብለው ሲፈርጁዋቸው፣ አንድ ከመንግሥቱ ጋር ቅርበት ያለው የተማሪዎች ማህበር « ወፍራም የማያምር አፍንጫ ያላቸው ሴትዮ» እያለ ሲያፌዝባቸው ተሰምቶዋል። ከፍተኛ የገዢው የአፍሪቃውያን ብሄረተኞች ኮንግረስ፣ በምህፃሩ «ኤ ኤን ሲ» ካድሬዎችም ቱሊሲሌ ማዶንሴላ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት እያሉ ሕዝብን የሚያሰጉ ጉዳዮችን የሚያጎሉ ጥቅም ፈላጊ፣ ወገንተኛ ወይም በስልጣናቸው አላግባብ ይጠቀማሉ በሚል በሕዝብ ዘንድ እምነት እና ከበሬታ ለማሳጣት ብዙ ጊዜ ሞክረው ነበር።

እንዲያውም ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት የሞት ዛቻ እንደደረሳቸው ተሰምቶዋል፣ አንድ የደቡብ አፍሪቃ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ቱሊሲሌ ማዶንሴላን በኬፕታውን ለሚገኝ አንድ የባለጉልበተኞች ቡድን ኃላፊ ከ50,000 ዩሮ በላይ በመክፈል ለማስገደል መታሰቡ ተመልክቶዋል።

ይኸው ዘገባ ከወጣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ የኢንተርኔት ምጸታዊ ገጽ እንደ ቀልድ ቱሊሲሌ ማዶንሴላ ተገድለዋል የሚል ጽሑፍ ያወጣ ሲሆን፣ ድርጊቱ እንደዋዛ የማይታለፍ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ያገኙት ቱሊሲሌ ማዶንሴላ፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለሩጫ እንኳን ብቻቸውን መውጣት አልቻሉም። የማስፈራሪያው ዛቻ ግን የ53 ዓመቷን እመበለት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ከመወጣት እንደማያግዳቸው የኔልሰን ማንዴላ ተቋም ሊቀ መንበር፣ ፕሮፌሰር ንዣቡሎ ንዴቤሌ አስታውቀዋል።

Thulisile Madonsela erhält den Deutschen Afrika-Preis 2016
ምስል Deutsche Afrika Stiftung e.V.

« በያዙት የሕዝብ እምባ ጠባቂነት ስልጣናቸው፣ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ እሴቶች ጠበቃ መሆናቸውን አስመስክረዋል። በማያወላውለው የኃላፊነት ሚናቸውም የደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሲ በጣም ህያው መሆኑን አሳይተዋል። »

ለዚሁ ቁርጠኝነታቸው በነፃ የተመረጡት የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ አርአያ እንደሆኑዋቸው ቱሊሲሌ ማዶንሴላ ይናገራሉ።

« በአንፃራቸው ያነጣጠረውን ማህበራዊውን ኢፍትሓዊነት ለሁሉም ማህበራዊ ፍትሕ ማስገና ምክንያት ቀይረውታል። ሕገ መንግሥታችን በጠቅላላ እውን ሊሆን የቻለው የማህበራዊ ኢፍትሓዊነት ሰለባ በሆኑ እና በዚህ አንፃር አንድ ነገር ማድረግ አለብን ብለው በወሰኑ ሰዎች ፅኑ ስሜት ነው። »

ቱሊሴሊ ማዶንሴላ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት ያገኘውን የደቡብ አፍሪቃን ሕገ መንግሥት ባረቀቀው ሕገ መንግሥታዊ ኮሚሽን ውስጥ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አብረው በጋራ ሰርተዋል።

ማንዶሴላ ለተነሱለት ዓላማ እስከመጨረሻ ድረስ ሳይታክቱ እንደሚሰሩ አብረዋቸው የተጓዙ ሁሉ ያውቁታል። የትዳር ጓዳቸውን ከጋብቻ በኋላ ወዲያው በሞት የተነጠቁት ቱሊሴሊ ማንዶሴላ ሁለቱን ልጆቻቸውን ብቻቸውን ማሳደግ ግድ ነበር የሆነባቸው፣ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያውን ዲግሪያቸውን ያገኙት በስደት እያሉ ሲሆን፣ እጎአ ከ1990 ዓም ወዲህ ሁለተኛውን ዲግሪያቸውን በማግኘት በሙሉ ጠበቃነት በመስራት ላይ ይገኛሉ። እጎአ በ2009 ዓም የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የሕዝብ እምባ ጠባቂ» ተቋም ኃላፊ ብለው ሲሾሙዋቸው፣ የተቋሙ በር ለሁሉም ዜጋ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኘው ሕዝብ ሳይቀር ክፍት እንዲሆን፣ እንዲሁም፣ ስራቸውን ካለ አድልዎ እና ካለ ፍርሀት እንዲያከናውኑ በማሳሰብ ጭምር ነበር።

የሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና የአፍሪቃውያን ብሄረተኞች ኮንግረስ፣ የ«ኤ ኤን ሲ» መሪ ጄኮብ ዙማ ይህን ማሳሰቢያ ያኔ ለቱሊሴሊ ማዶንሴላ ባቀረቡበት ጊዜ ይኸው ማሳሰቢያ በሳቸውም ላይ ዞሮ ሊመጣ ይችላል የሚል እሳቤ አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ፣ ቱሊሴሊ ማዶንሴላ በስልጣን አላግባብ መጠቀምን በተመለከተ ለምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባቸው፣ ፕሬዚደንት ዙማ እና ቤተሰባቸው በክዋዙሉ ናታል ግዛት በምትገኘው የንካንዳላ ከተማ ያለውን መኖሪያ ቤታቸዉን አሻሽለው ለማሰራት ሕዝብ ለመንግሥት ከከፈለው ግብር ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ወደ 13 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል በሚል ወቀሳ ገንዘቡን መልሰው እንዲከፍሉ ጠይቀዋል። ይኸው የማንዶሴላ ዘገባ፣ እርግጥ፣ የ«ኤ ኤን ሲ» እንደራሴዎች አብላጫውን ድምፅ በያዙበት ምክር ቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በዚሁ ጊዜም ነበር የገዛ ፓርቲያቸው አቻዎቻቸው ቱሊሴሊ ማዶሴላን ፀረ ዓብዮተኛ፣ ሰላይ እና የተቃዋሚ ቡድኖች አገልጋይ እያሉ ስማቸውን ማጉደፍ የጀመሩት።

Jacob Zuma Korruption Prozess
ምስል Getty Images/AFP/R. Jantilal

ምክር ቤቱ ማመልከቻቸውን ውድቅ ባደረገባቸው ጊዜ፣ በውሳኔው አንፃር በምክር ቤት ከተወከሉት ሁለት ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባንድነት በመሆን በሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ። ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤትም ክሱንን ከተመለከተ በኋላ የእምባ ጠባቂዋን ዘገባ ባለፈው መጋቢት ወር የተቀበለበት ውሳኔ እንዳስደሰታቸው ማዶንሴላ ገልጸዋል።

የኔልሰን ማንዴላ ተቋም ሊቀ መንበር፣ ፕሮፌሰር ንዣቡሎ ንዴቤሌ እንዳስረዱትም፣ የህገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ውሳኔ ማዶንሴላ እና በተቋማቸው የሚሰሩት ሁሉ ስራቸውን በትክክል እንዳከናወኑ ሁነኛ ማስረጃ መሆኑን ያረጋገጠ ውሳኔ ሆኖዋል።

« መስሪያ ቤታቸው ያደረገው ጥረት ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ ከፍተኛ ሕግ መሆኑን፣ እንዲሁም፣ ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልሆነ እና መሆንም እንደሌለበት አረጋግጦዋል። »

Südafrika Pretoria Anti-Korruptionsmarsch
ምስል picture-alliance/dpa/K. Ludbrook

«ታይም» የተባለው የዩኤስ አሜሪካ መጽሔት ፕሬዚደንት ዙማን የመንግሥት ገንዘብ አላግባብ ተጠቅመዋል በሚል ክስ ያስነሳው የ«ንካንዳላ» ዘገባ ከወጣ በኋላ ፣ ማዶንሴላን በ2014 ዓም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፈዋል ካላቸው 100 ታዋቂ ሰዎች አንዷ አድርጎ መርጧቸዋል። ጠበቃዋ እና የሕገ መንግሥቱ አስከባሪ ማዶንሴላ በደቡብ አፍሪቃ የድሆች ተሟጋች ሆነው ነው የሚታዩት። የእምባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊ ከ300 ሰራተኞቻቸው ጋር ባንድነት በመሆን ለውድ ጠበቆች የሚከፍሉት ገንዘብ የሌላቸውን በዝቅተኛ መደብ የሚገኙትን የደቡብ አፍሪቃ ዜጎች ብሶት እና ቅሬታ እየተመለከቱ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ያፈላልጋሉ። ቱሊሲሌ ማዶንሴሊ እጎአ በ2009 ዓም በተቋሙ ስራ ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ለተቋማቸው ወደ 40,000 ቅሬታዎች የቀረቡ ሲሆን፣ መስሪያ ቤታቸው ለ25,000 ሁነኛ መልስ በማስገኘት ጥሩ ውጤት አስመዝግቦዋል።

በተቋሙ ጥረት በጡረታ የሚገኙ ዜጎች የጡረታ ገንዘባቸውን ሊከፈሉ፣ ተማሪዎች የተመደበላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ሊያገኙ፣ የተጭበረበሩ ሰነዶች ሊሰረዙ ችለዋል። ፕሬዚደንቱ ሳይቀሩ አላግባብ ተጠቅመውበታል የተባለውን የመንግሥት ገንዘብ እንዲመልሱ ተፈርዶባቸዋል። ቱሊሲሌ ማዶንሴላ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ ተወጥተዋል። ወላጆቻቸው ቱሊሲሌ ወይም ሲተረጎም የእግዚአብሔር ስጦታ የሚል መጠሪያ የሰጡዋቸው የእምባ ጠባቂው ተቋም ኃላፊ ማዶንሴላ በመላ ደቡብ አፍሪቃ ከሁሉም ሰው በላይ የተከበሩ ግለሰብ መሆናቸውን «ዩጎቭ» የተባለው የሕዝብ አስተያየት መርማሪ ተቋም አስታውቋል።

የቱሊሲሌ ማዶንሴላ የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊነት ስልጣን ዘመን እጎአ የፊታችን ጥቅምት 2016 ዓም የሚያበቃ ሲሆን፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የሀገሪቱ ምክር ቤት ኮሚቴ በቅርቡ ተተኪያቸን እንደሚመርጥ ተገልጾዋል። በታዛቢዎች ግምት መሰረት፣ ማዶንሴላን የሚተካው ግለሰብ ቀላል ስራ አይደለም የሚጠብቀው።

« እርስዎን የሚተካው ግለሰብ፣ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊነት ማንፀባረቅ እና ይህችን ሀገር ለመገንባት የሚያስፈልገንን መሰረት ማቅረብ ይኖርበታል። »

ክላውስ ሽቴከር / አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ