1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚራዘም ፍንጭ ሰጥተዋል

ሐሙስ፣ መጋቢት 7 2009

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግስታቸውን የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘገባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊራዘም እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2ZLEy
Äthiopien | Parlament
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Opposition & Public reaction on PM speech (FINAL) - MP3-Stereo

አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ዘገባ እንደተለመደው አብዛኛው ቦታ የሰጠው ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ነው፡፡ በዘገባቸው መገባደጃ አካባቢ ከጠቃቀሷቸው ፖለቲካዊ ጉዳዩች ውስጥ ይበልጥ ቀልብ የሳበው ግን ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተናገሩት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “በሀገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ እንዲቀለበስ” ማድረጉን እና በ“ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ማምጣቱን” ገልጸዋል፡፡ 

ሆኖም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የታዩ ክስተቶች የሀገሪቱ የጸጥታ አካላት በአንድ ኮማንድ ፖስት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚጠይቁ እንደሆነ ሁነቶችን በምሳሌ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትሎ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአንድ ጊዜ ቢራዘም የተደላደለ እና እጅግ አስተማማኝ የሆነ ሰላም ለማረጋገጥ ይቻላል” የሚል ሀሳብ በህዝብ ውስጥ እንደሚንሸራሸር ለመገንዘብ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ማጣቀሻ ያደረጉት በቅርቡ ተደረገ የተባለ የህዝብ አስተያየት ጥናትን ነው፡፡ 

“በተደረገው የህዝብ አስተያየት ጥናት ወደ 82 በመቶው የሚሆነው በጥናቱ የተሳተፈው ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲቀጥል የሚል አስተያየት እንዳላቸው ለመረዳት ችለናል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸንቶ በሚቆይበት በሚቀጥለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥልቅ ጥናት በማካሄድ ለተከበረው ምክር ቤት የጥናቱን ውጤት በማቅረብ የምናጸደቅበት ሁኔታ ይኖራል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ 

Äthiopien | Parlament
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ስለ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” የሚያወሳው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 93 የተወካዮች ምክር ቤት አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው አዋጁ እንዲራዘም ፍንጭ መስጠታቸው በተቃዋሚዎች አልተወደደም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱትን የህዝብ አስተያየት ጥናት አጣጥለዋል፡፡ 

“በመሰረቱ ህዝቡን መጀመሪያ አማክረው አይደለም ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጫኑበት፡፡ ሁለተኛ ህዝቡ የሚያፍነውን ህግ እንዲቀጥል በፍጹም አስተያየት ሊሰጥ አይችልም፡፡ እንደውም በፊት የነበሩ ህጎች ‘አላነቃንቅ፣ አላሰራኝ አሉ፣ የሀዝብን መብት የሚጥሱ እና እንቅስቀሴ የሚያፍኑ ናቸው’ ነው ተቃውሞውም የነበረው፡፡ እና ለዚያ አፈና ሌላ አፈና መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የጠሩት ይሄ የመቶኛ ቁጥርም ሆነ ከህዝብ ተቀበልነው የሚሉት አስተያየት እኔ በፍጽም ከእውነት የራቀ ነው የሚመስለኝ” ሲሉ አቶ የሺዋስ ይሟገታሉ፡፡ 

የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲያዊ እና ሉዓላዊነት (አረና) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታም አዋጁ “የአፈና መሳሪያ ነው” የሚል ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ 

“መጀመሪያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢህአዴግ በሚያደርገው አፈና ህጋዊ ሽፋን ያስገኘ እንጂ ብዙ ለውጥ ያለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ አፋኝ ነው፡፡ ለስልጣኑ ሟች ነው፡፡ ህዝብን ከመግደል፣ ከማሰር ወደኋላ አይልም፡፡ እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢኖርም ባይኖርም ሰው መግደሉ፣ ማሰሩ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው አንጻራዊ መረጋጋትም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተገናኘ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ቢያራዝሙትም ብዙ የሚፈይደው ነገር አይኖርም” ይላሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ንግግር የተመለከቱ በርካታ አስተያየቶች በፌስ ቡክ ገጻችን እና በዋትስ አፕ የስልክ አድራሻችን ደርሰውናል፡፡ ብዙዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አባባልም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል የህዝብ ፍላጎት አለ መባሉን ነቅፈዋል፡፡ ጥቂቶች አዋጁ መቀጠል አለበት በሚል ተከራክረዋል፡፡

መገርሳ ጋዲሳ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ “ህዝብ እያለ ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይሆን ለሱ ምክንያት የሆኑ ችግሮች ይፈቱ ነው፡፡ ወዴት የህዝብ ጥያቄን መሸፋፈን ነው?” ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሲሳይ አየለ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ “ማራዘም መብታችሁ ነው፡፡ የተቀረው ዓለም ግን የሚረዳው ‘ተራዘመ ማለት አልተረጋጋም’ በሚል ዕሳቤ ነው” ብለዋል፡፡ ኃይለ ሚካኤል የተሰኙ ተከታታይ በበኩላቸው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያንገበግባቸው የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉና የጎዳና ላይ ነውጥ ፈላጊዎች ናቸው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ