ቫኑዋቱ ደሴት በዝናባማ አውሎ ንፋስ ተናወጠች
ቅዳሜ፣ መጋቢት 5 2007ማስታወቂያ
እንደ አካባቢው ባለሥልጣናት ከሆነ አውሎ ንፋሱ የተነሳ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሞተዋል። በመዲናይቱ ፖርት ቪላ መኖሪያ ቤቶች እና የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። የከተማይቱ ማዕከላይ ሐኪም ቤት ሕንፃም በአንድ ጎኑ ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል።
ነጎድጓዳማዉ አውሎ ነፋስ ባደረሰው ጉዳት የተነሳ ከበርካታ ደሴቶች ጋር ግንኙነቱ በመቋረጡ የሟቾችን ኹነኛ ቁጥር እና የጥፋቱን መጠን እስካሁን በውል መለየት እንዳልተቻለ ተገልጧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ጽ/ቤት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ የሟቾቹ ቁጥር ከ44 ከፍ ይላል። የዉኋ መጥለቅለቅ አደጋም ተጋርጦአል።
በአየር ንብረት ዘገባ ደረጃ አሰጣጥ መሠረት «ፓም» የሚል ስያሜ ያገኘው ይኽ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ንፋስ ደረጃው አምስት ነው ተብሏል። ይህ ተፈጥሮዋዊ አደጋ ከ80 በላይ በሆኑት የቫኑዋቱ ደሴቶች ላይ ሲከንፍ እየተምዘገዘገ የነበረዉ በሠዓት ከ340 ኪሎ ሜትሮች በላይ እንደነበርም ተጠቅሷል።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ