1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቫሌታ፤ የአፍሪቃ እና አዉሮጳ መሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2008

በስደተኞች ቀዉስ ላይ ማልታ መዲና ቫሌታ ላይ የተቀመጡት የአዉሮጳና የአፍሪቃ መሪዎች ወደ አዉሮጳ ሕገ-ወጥ ስደተኝነትን ለመከላከል የሚያስችል ዉልን አፀደቁ። የአዉሮጳ መሪዎች ከአፍሪቃ የሚጎርፈዉን የስደተኛ ለመቀነስ ለአፍሪቃ ሃገራት ለልማት ማስፋፊያ እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ይሆናል ያሉትን 1,8 ቢሊየን ዩሮ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/1H4pq
Valetta Malta Treffen Migration 2015 Europa Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/L.A. Azzopardi /Detail

በስደተኞች ቀዉስ ላይ ማልታ መዲና ቫሌታ ላይ የተቀመጡት የአዉሮጳ እና የአፍሪቃ መሪዎች ወደ አዉሮጳ ሕገ-ወጥ ስደተኝነትን ለመከላከል የሚያስችል ዉልን አፀደቁ። የመንግስታቱ መሪዎች ዛሬ በሁለተኛ ቀን ጉባዔያቸዉ በተፈራረሙበት የቅድ ስምምነት ላይ የሕገ-ወጥ ስደተኝነትን ለመዋጋት የሚያስችል እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ለሥራ አልያም ለትምህርት ወደ አዉሮጳ ሕብረት ሃገራት መግባት የሚያስችል ስምምነት ላይ መስማማታቸዉ ተመልክቶአል። ለስደተኞች መርጃ የሚሆን ከአዉሮጳ ሕብረት 1.8 ቢሊዮን ይሮ መመደቡም ተመልክቶአል። የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር በመግለጫቸዉ የሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለመዋጋት የሕብረቱ አባል ሃገራት ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚሰጡ ተስፋቸዉን ተናግረዋል። ይኸዉም ከሕብረቱ ሃገሮች የሚጠበቀዉ ገንዘብ በእጥፍ እስከ 3.6 ቢሊዮን ይሮ መሆኑ ታዉቋል። ዣን ክሎድ ዩንከር ስለ ጉባዔዉ በሰጡት ቃለ-ምልልስ
«ስብሰባዉ በወንድማማችነትና በመከባበር ሁኔታ ነዉ የተጠናቀቀዉ። በሁለቱም ወገን የሚታየዉ አንድ አይነት ችግር ሜዲተራንያን ላይ መኖሩን ነዉ። አፍሪቃዉያንን መርዳት አለብን። ምክንያቱም እኛ ካለብን ችግር የበለጠ ከፍተኛ ችግር ስላለባቸዉ ነዉ»
የሕብረቱ ሃገራት የሚሰጡት ገንዘብ፤ ወጣት ዜጎችን ለመደጎም እንዲሁም ከአዉሮጳ ወደ የሀገራቸዉ የሚመለሱትን ዜጎች በኑሮ ለማቋቋም እንደሚዉል ተመልክቶአል። የቀረዉ ገንዘብ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋዉሩትን ለመዋጋትና የድንበር ጥበቃን ለማሻሻል እንደሚዉል ተገልፆአል። አፍሪቃ ከአዉሮጳ ሕብረት በየዓመቱ ከ 20 ቢሊዮን ይሮ በላይ የምታገኝ ሲሆን ይህ ማልታ ላይ ስደተኝነትን ለመዋጋት ሊሰጥ የታቀደዉ ገንዘብ ተጨማሪ መሆኑ ተዘግቦአል። በማልታ ዋና ከተማ ቫሌታ ለሁለት ቀናት በዘለቀዉ ጉባዔ ወደ 80 የሚሆኑ የአፍሪቃና የአዉሮጳ ሕብረት መንግሥታትና የመንግሥታት ተጠሪዎች መገኘታቸዉ ታዉቋል።

EU Afrika Gipfel 2015
ምስል Getty Images/AFP/F. Monteforte

የኅብረቱ መሪዎች ወደአዉሮጳ የተሻገሩ በርካታ ስደተኞችን ወደየአባል ሃገራቱ ለማከፋፈል ያቀዱት እጅግም ተግባራዊ የሆነ አይመስልም። ያም ሆኖ ግን የስደተኞች መፍለቂያ ከሚባሉ የአፍሪቃ ሃገራት ጋር በተለይ የኤኮኖሚ ስደተኞችን ባሉበት ሊያስቀር የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት አቅደዋል። የሁለት ቀናቱ ጉባኤ ሲጠናቀቅ የደረሰባቸዉን የዉሳኔ ነጥቦች በተመለከተ ብራስል ከሚገኘዉ ዘጋቢያችን ገበያዉ ንጉሤ ጋር ስቱዲዩ ከመግባታችን በፊት በስልክ ተወያይተናል።


ገበያዉ ንጉሤ


ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ