ቫሌታ፤ የአዉሪሮጳ እና የአፍሪቃ ሃገራት ጉባኤ
ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2008ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መበራከቱን ተከትሎ ከስደተኞች መፍለቂያ ሃገራት ጋር መፍትሄ ለመሻት በተዘጋጀዉ በዚህ ጉባኤ 65 ሃገራት እንደሚሳተፉ የጀርመን የዜና ወኪል ከቫሌታ ዘግቧል። የአዉሮጳ መሪዎች የአፍሪቃ አቻዎቻቸዉ ለኤኮኖሚ ስደተኞች በየሀገራቸዉ መፍትሄ እንዲያበጁ እስከ3,6 ቢሊየን ዩሮ ርዳታ ሊሰጡ ማቀዳቸዉ ተገልጿል። የፖለቲካ ተንታኙ ፎዑም ኪማራ በበኩላቸዉ የአዉሮጳ መሪዎች የስደተኛ መፍለቂያ የሆኑ ሃገራትን ሰላም ማረጋገጡ ላይ ቢያተኩሩ እንደሚበጅ ያመለክታሉ።
«የአዉሮጳ መሪዎች በመጀመሪያ የችግሩ ምንጭ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፤ ችግሩ የተፈጠረዉ አንዳንድ የአዉሮጳ መንግሥታት የእነዚያን ሃገራት ሰላም በማናጋታቸዉ ነዉ፤ ይህ ደግሞ አለመረጋጋትን ፈጠረ በዚህም ምክንያትም ሰዎች መጠጊያ ፍለጋ በየአቅጣጫዉ ተሰደዱ። ስለዚህ አሁን በእነዚያ ሃገራት ዉስጥ ሰላማን ማረጋገጥ ላይ ማትኮር ይኖርባቸዋል። ብቸኛዉ መፍትሄ ያ ነዉ የሚመስለኝ።»
በተቃራኒዉ የአፍሪቃ መሪዎች ዜጎቻቸዉ በየሀገሩ ተሰደዉ በየጊዜዉ ወደሀገር ቤት የሚልኩት የዉጭ ምንዛሪ እንዲስተጓጎል እንደማይፈልጉ የፈረንሳይ የዜና ወኪል አመልክቷል። የአዉሮጳ መሪዎች ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር የስደተኞችን ጎርፍ በመከላከል፤ በቂ ምክንያት የሌላቸዉ ስደተኞች ወደየመጡበት በመመለስና የሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም ትብብራቸዉ ለማጠናከር አቅደዋል። የአዉሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ቱስክ የሁለት ቀኑ የጋራ ጉባኤ «የተግባር» እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ነዉ ብለዋል። ከአፍሪቃ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ ከ30 በላይ ሃገራት በዚህ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ። በስደት የሚገኙት የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኤልሳቤት ጭሩም ስደተኞችን ለማስቀረት ሲባል ለኤርትራ መንግሥት ገንዘብ እንዳይሰጥ፤ ይልቁንም ኤርትራዉያን በስደት ለሚኖሩባቸዉ ሃገራት ቢዉል እንደሚበጅ መጠየቃቸዉ ተዘግቧል።
ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ