1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮ ሃራም ላይ የተከፈተዉ ዘመቻ

ዓርብ፣ የካቲት 13 2007

ናይጄሪያ በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ጠንካራ ይዞታ በተባሉ አካባቢዎች ላይ የአውሮፕላን ድብደባ እየፈጸመች ነው። በተመሳሳይ ከትናንት በስተያ በአውሮፕላን ጥቃት ለናይጀሪያ በሚጎራበተዉ የኒጀር ግዛት በቀብር ስርዓት ላይ ከነበሩ ሰዎች በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

https://p.dw.com/p/1EfFO
Boko Haram Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo

የናይጄሪ ጦር ሃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች የቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በሚገኝባቸው አካባቢዎች ድብድበ መፈጸም መጀመራቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የቡድኑ መሪ አቡባካር ሼካው ቦኮ ሃራም እስላማዊ መንግስት ወይም ካሊፋት መሠረተባት ያላት የግዎዛ ከተማ እና የቡድኑ ጦር ሰፈር ይገኝበታል የተባለው የሳምቢሳ ጥቅጥቅ ደን ዋንኛ ኢላማዎች ናቸው። በቡድኑ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ 11 ከተሞችና መንደሮች ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት 300 ታጣቂዎች መገደላቸውን የዜና ወኪሉ ጨምሮ ዘግቧል። በዚህ መካከል ግን ከጎረቤት ሃገር ኒጀር በንጹሃን ሲቪል ዜጎች ላይ የአውሮፕላን ድብደባ መፈጸሙን የመንግስት ቃል-አቀባይ የሆኑት ማሩ አማዱ ይናገራሉ።
«የማን መሆኑ ያልታወቀ አውሮፕላን በኒጀር የአዳም መንደር ቦሱ ከሚባል ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 13 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከአንድ መስጊድ አጠገብ የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጸመ ጥቃት 36 ሰዎች መሞታቸውን እና 24 መቁሰላቸውን የደረሰን ጊዜያዊ መረጃ ይጠቁማል። መረጃው እንዳረጋገጠው በዚህ ስም የሚጠራ መንደር በናይጄሪያም ይገኛል።»
ሶስት ብሄራዊ የሃዘን ቀናት ያወጀችው እና ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ የወሰነችው የኒጀር ፕሬዝዳንት ማሃማዱ ኢሱፉ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ እና ጥቃቱን የፈጸሙት አውሮፕላኖች የማን መሆናቸው እንዲጣራ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ቃል አቀባዩ ማሩ አማዱ ተናግረዋል።
አውሮፕላኖቹ የኒጀርም የቻድም አለመሆናቸውን ባርሙ ሃሙ ናካታ የተባሉ የግዛቲቱ ባለስልጣንን ጠቅሶ የጀርመን የዜና ወኪል ዘግቧል። እንዲያውም በቀብር ስርዓቱ ላይ ጥቃት የፈጸሙት አውሮፕላኖች የናይጄሪያ ቀለም እንዳላቸው የዐይን እማኞች መናገራቸውን ዘገባዉ አመልክቷል። የናይጄሪያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።
የናይጄሪያ አየር ሃይል የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ጠንካራ ይዞታ ናቸው ባላቸው የሰሜን ምስራቅ ቦርኖ ግዛት አካባቢዎች ላይ ድብደባ እየፈጸመ በሚገኝበት ወቅት የኒጀር መንንግስት እና የዚንደር ነዋሪዎች ግን ስጋት ገብቷቿዋል። ኒጀር ከናይጄሪያ በምትዋሰንበት አካባቢ በምትገኘው የዚንደር ግዛት በዚህ ወር ብቻ ስድስት ጥቃቶች የፈጸመው የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ጥብቅ ፍተሻ መጀመሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ስጋቱ የመነጨው ኒጀር ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት ከናይጄሪያ፤ ካሜሩን፤ ቤኒን እና ቻድ ጎን ለመሰለፍ መወሰኗን ተከትሎ ነው።
የቻድ ጦር በበኩሉ በናይጄሪያ ግዛት ሶስት ግንባሮች በቦኮ ሃራም ላይ በጀመረዉ ጥቃት በለስ እየቀናው ነው ተብሏል። የቻድ ጦር ላለፉት አምስት ወራት በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ሥር በነበረችው የዲክዋ ከተማ፤ በቦርኖ ግዛት ዋና ከተማ በማይዱግሪ አካባቢ እና በካሜሮን ድንበር ውጊያ ላይ ነው።
የናይጄሪያ ጦርም የሞንጉኖን ከተማ እንደገና መቆጣጠር መቻሉ ተሰምቷል። ለናይጄሪያውያን ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት የጎረቤት ሃገራት ዘመቻ ሁለት መልክ አለው።
«ካሜሮናውያን እና የኒጀር ጦር ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት በሚል ሰበብ ወደ ሃገራችን መምጣታቸውን አልወደድኩትም። ይህንን በራሳችን ማድረግ አለብን ብዬ አምናለሁ። ትብብሩ በድንበር አካባቢ ብቻ የተወሰነ መሆን ነበረበት።»
«አሸባሪነት ዓለም አቀፍ ችግር በመሆኑ መልካም ዜና ነው ብዬ አስባለሁ። ከየትም ይምጣ ከየት ይህን ሽብርተኝነት ለማቆም ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልገናል።
ናይጄሪያ፤ ካሜሩን፤ ቤኒን ፤ቻድ እና ኒጀር የቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂ ቡድንን ለመውጋት 8700 ወታደሮችን ያካተተ ጠንካራ ሃይል ለማቀናጀት መስማማታቸው አይዘነጋም። ሃገራቱ አሁን በተናጠል የሚያካሂዱትም ይሁን በጥምረት የሚጀምሩት ዘመቻ ታጣቂ ቡድኑ በቀጣናው የደቀነውን ስጋት መቅረፍ ስለመቻሉ ለመናገር ገና መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

Nigeria Soldaten
ምስል picture-alliance/AP Photo
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ