1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦትስዋና የዴሞክራሲ አብነት

ዓርብ፣ መስከረም 20 2009

የትንሺቱ ደቡባዊ አፍሪቃ ሐገር መሪዎች ከግዛታቸዉ ወጣ እያሉ አምባ ገነኖችን መወረፍ የጀመሩት፤ የፖለቲካ ተንታኝ ሞሪማ እንደሚሉት «ፒር ሪቪዊ ሜካኒዝም» የተሰኘዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመገማገሚያ መርሕ ከተሽመደመደ በኋላ ነዉ።መርሑ የአፍሪቃ መሪዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነበር።አልሰራም።

https://p.dw.com/p/2QmrE
Botswana Feierlichkeit zum 48. Unabhängigkeitstag
ምስል picture alliance/AA/K. Mathe

ቦትስዋና ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችበትን 50ኛ ዓመት በዓል ዛሬ (30.09.16) ማክበር ጀምራለች።ደቡባዊ አፍሪቃዊቱ ሐገር ላለፉት ሐምሳ ዓመታት ሠላምን በማስፈን፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስረፅና ሙስናን በመዋጋት ከብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 

ቦትስዋና ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችበትን 50ኛ ዓመት በዓል ዛሬ (30.09.16) ማክበር ጀምራለች።ደቡባዊ አፍሪቃዊቱ ሐገር ላለፉት ሐምሳ ዓመታት ሠላምን በማስፈን፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስረፅና ሙስናን በመዋጋት ከብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች።ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሐገሪቱ መንግሥት በነፃ ጋዜጠኞችና መገናኛ ዘዴዎች ላይ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች፤ የአስመራጭ ኮሚሽኑ አደረጃጀት እና አብዛኛዉ ሕዝብ በተወሰኑ የሐገሪቱ አናሳ ጎሳዎች ላይ ያለዉ አመለካከት አኩሪ ታሪኳን እንዳያበላሸዉ ማስጋቱ አልቀረም።ፊሊፕ ዛንደነር ያዘጋጀዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።
 
የቦትስዋና 50 ዐመት የነፃነት ዘመን ሲዘከር-ከአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት የመለየቷ ሐቅም ነዉ የሚመሰከረዉ።የርስ በርስ ግጭት አታዉቅም።ሰላም ናት።የተጭበረበረ ምርጫ አልተመዘገበባትም።«ምርጫችን ሁል ጊዜ ነፃና ሚዛናዊ ነዉ።» ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝ ንዱላሞ አንቶንይ ሞሪማ-በኩራት።
                                   
«የመጀመሪያዉ አጠቃላይ ምርጫ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫ አስተናግደናል።ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግሥት ጫና ተደረገብን የሚል አቤቱታ ያልተሰማበት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ነዉ-ያለን።የሕግ ሥርዓታችን፤ ዳኞቻችን ነፃ ናቸዉ።አንዳዶቹ እንዲያዉም በጣም ጥንቃቄ በሚፈልጉ ክሶች ላይ መንግስትን ተጠያቂ አድርገዉ በይነዋል።መንግሥትም ዉሳኔዉን ተቀብሏል።»
ሙስናም ብዙ አታዉቅም።የሙስናን ጉዳይ የሚያጠናዉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ በሚያወጣዉ መዘርዝር ቦትስዋና ከአፍሪቃ የመጀመሪያዉ ተርታ ላይ ናት።ዘንድሮ ከዓለም 28ኛ።
በአልማዝ ማዕድን የበለፀገች ናት።የተፍጥሮ ሐብት የሹማምንቶችና የታማኞቻቸዉ መበልፀጊያ በሆነባት አፍሪቃ-ቦትስዋና ላይ የሐገር ልማት መሠረት ነዉ።ምጣኔ ሐብቱን ከማዕድን ጥገኝነት ለማላቀቅ መንግስት እየጣረ ነዉ።
የቀድሞዉ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ፌስቱስ ሞጌ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር የ2008ቱን የሞ ኢብራሔምን ሽልማት አግኝተዋል።አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኘዉ  ሽልማት ሥልጣናቸዉን በሰላማዊ ምርጫ ላስረከቡ የአፍሪቃ መሪዎች የሚሰጥ ነዉ።
ቦትስዋና የአፍሪቃ አምገነኖችን ጎነጥ ማድረግ ጀምራለችም።ከሰወስት ዓመት በፊት ዚምባቡዌ ዉስጥ የተደረገዉ ምርጫ በድጋሚ እንዲደረግ ጠይቃ ነበር።ባለፈዉ ዓመት የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ሕገ-መንግሥት ጥሰዉ ለሰወስተኛ ዘመነ-ሥልጣን «ተመረጥኩ» ማለታቸዉን ቦትስዋና ነቅፋዋለች።
የትንሺቱ ደቡባዊ አፍሪቃ ሐገር መሪዎች ከግዛታቸዉ ወጣ እያሉ አምባ ገነኖችን መወረፍ የጀመሩት፤ የፖለቲካ ተንታኝ ሞሪማ እንደሚሉት «ፒር ሪቪዊ ሜካኒዝም» የተሰኘዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመገማገሚያ መርሕ ከተሽመደመደ በኋላ ነዉ።መርሑ የአፍሪቃ መሪዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነበር።አልሰራም።
                             
«ታቦ ኢምቤኪ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት የነበሩ ጊዜ የአፍሪቃ ፒር ሪቪዉ ሜካኒዝም የተባለ ደንብ ነበር።አልሰራም።ሐገራቸዉን በትክክል የማይመሩ መሪዎች አሽመደመዱት።በዚሕ ምክንያት ፕሬዝዳንቶቻችን፤ ሥልጣናቸዉን አላግባብ የሚጠቀሙና ሕዝባቸዉን የሚያሰቃዩ መሪዎችን ከማዉገዝ ሌላ፤ ሌላ ምርጫ የላቸዉም።»
ቦትስዋና ወደ ዉጪ ጎረቤትችዋ ስትቃኝ፤ የዉስጥ ጉድፏም ብቅ-ደመቅ እያለ ነዉ።ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሥራቸዉ የሚያስፈልግ ገንዘብ ከመንግሥት አይሰጣቸዉም።የምርጫ ኮሚሽኑም ለሐገሪቱ ገዢ ፓርቲ የሚያዳላ በመሆኑ በግልፅ እየተወቀሰ ነዉ።ፕሬዝደንት ያን ካማ ሥልጣን የያዙበት ምርጫ ከሁለት ዓመት በፊት ሲደረግ ተቃዋሚዎች፤ የፖለቲካ አቀንቃኞች በፀጥታ ሐይላት መደብደባቸዉ ተዘግቧል።
ሰንዴይ ስታንዳርድ የተባለዉ ጋዜጣ እንደዘገበዉ በአቀንቃኞች ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ የፕሬዝዳንቱ የራሳቸዉ እጅ ሳይኖርበት አልቀረም።የጋዜጣዉ ዋና አዘጋጅ ኦዉትሳ ሞኮኔ ታስሮም ነበር።ሳን የተባለዉ ጎሳ አባላት ከተፍጥሮ ጋር ባላቸዉ ቁርኝት ምክንያት «የጫካ ሰዎች» እየተባሉ መነቀፍ፤ መንጓጠጥ-መናቃቸዉ የቦትስዋናን የዲሞክራሲ፤የእኩልነትና የፍትሐዊነት መደላድል እንዳያጨናጉለዉ ያሰጋል።
                                             
«መከራከሪያዉ ሐሳብ  የጫካ ሰዎች የሚባሉት የተፈጥሮ ጥበቃን ያደናቅፋሉ የሚል ነዉ።ቦትስዋና ራስዋን ተፈጥሮን የምትጠብቅ ሐገር አድርጋ ነዉ የምትቆጥረዉ።ለሐገር ጎብኚዎች ሲባልም።አደን በመላ ሐገሪቱ ክልክል ነዉ።የቻካዎዎቹ ሰዎች ጥበቃዉን ያደናቅፋሉ በሚል አካባቢያቸዉን እንዲለቁ ይገደዳሉ።»
ሊንዳ ፖፐ ናቸዉ።በጀርመን የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ተጠሪ።

Rohdiamant Frankreich Paris
ምስል Reuters/C.Platiau
Botswana Ian Khama
ምስል Reuters/S. Sishi

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ