1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሪታንያ የቀድሞ ቅኝ ገዢ የዛሬዋ ታዳጊ

ዓርብ፣ ጥር 6 1997

የብሪታንያዉ ቻንስለር ጎርደን ብራዉን አገራቸዉ ባንድ ወቅት በቅኝ ገዢነት ተቀራምታት የነበረችዉ አፍሪካን ካለችበት የድህነት አረንቋ ለመታደግ በአህጉሪቱ ለአንድ ሳምንት ለማድረግ ያቀዱትን ጉብኝት ትናንት ከኬንያ ጀመሩ።

https://p.dw.com/p/E0f3

በኬንያ በነበራቸዉ ቆይታም ለአምስት ሰዓታት ያህል በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኘዉን ኪቤራ የተሰኘ ጎስቋላ መንደር በመጎብኘት ነዉ ያሳለፉት።
ኪቤራ የተሰኘዉ አካባቢ በአፍሪካ ያልተለመደ ጥቅጥቅ ያለ አስፋፈርና በርካታ ኗሪዋች ያሉበት ኋላ ቀር አካባቢ በመባል የሚታወቅ መንደር ነዉ።
በዚህ መንደር የቆሻሻዉ ክምችትና የሚፈጥረዉ ሽታ በአካባቢዉ ችምችም ብለዉ የሚገኙትን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ኗሪዎች ያሉባቸዉን ቤቶች የሚነቀንቅ ነዉ።
በአካባቢዉ የተሟላ የንፅህና አገልግሎት ባለመኖሩ የኪቤራ ኗሪዎች በፅዳት ጉድለት ለሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ህይወታቸዉ ተጋልጧል።
የቻንስለሩ ይህን መሰሉን የአፍሪካ የድህነት ገፅታ ማየት መቻል ምናልባትም ብሪታንያ ከዚህ በፊት የአህጉሪቱን የድህነት ሁኔታ ለማስተካከል ከቀየሰችዉ እቅድ ተጨማሪ እንድታዘጋጅ ይረዳል ተብሎ ተገምቷል።
ይህም የአይኤምኤፍ ድጋፍን ጨምሮ የአለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ የድሃ አገራትን እዳ እንዲሰርዙ ማድረግን ሁሉ ሊያካትት ይችላል።
ብራዉን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም ብሪታንያ በከፍተኛ ደረጃ የብድር ጫና ላለባቸዉ አገራት መቶ በመቶ የእዳ ስረዛ ለማድረግ እንደምትፈልግና መጠነኛ እዳ ላለባቸዉ አገራት ደግሞ ተጨማሪ እቅድ እንዳላት ገልፀዋል።
ከፍተኛ የብድር ጫና ላለባቸዉ አገራት ይህን መሰሉ የእዳ ስረዛ ሃሳብ የመነጨዉ በ1986ዓ.ም በአይኤምኤፍና በአለም ባንክ አማካኝነት ነበር።
የዚህ ሃሳብ መነሻዉ በከፍተኛ ሁኔታ በእዳ የተዘፈቁት ድሃ አገራት ያሉባቸዉን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ለመቅረፍ ሊያዉሉት የሚገባቸዉን የገንዘብ አቅም እዳቸዉን ለመክፈል ላይ ለማዋል መገደዳቸዉ ከታየ በኋላ ነዉ።
በአሁኑ ወቅት 40 የሚሆኑ መንግስታትን የዚህ አይነቱ የእዳ ስረዛ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን ሶስት አራተኛዉን ቁጥር የያዙት የአፍሪካ አገራት ናቸዉ።
በተጨማሪም የብሩታንያ አለም አቀፍ የገንዘብ አቅርቦት አዲሱ እቅድ ለአፍሪካ እስከዛሬ ይደረግ የነበረዉን ድጋፍ አሁን ካለዉ 50 ቢሊዮን ዶላር እጥፍ ለማድረግ ነዉ።
ከመጪዉ አስርት አመታት ጀምሮ በያመቱ ከበጀቱ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነዉ የአፍሪካን የትምህርት ቤቶች ሁኔታ ለማሻሻል ይዉላል።
ከዚህም ሌላ የአፍሪካ አርሶ አደሮች በበለፀጉት አገራት ከሚገኙት አቻዎቻቸዉ ጋር በገበያ ለመወዳደር እንዳይችሉ ያገዳቸዉ ያልተመጣጠነ የንግድ ሁኔታ መስመር መያዝ አለበት ስትል ቢሪታንያ ጥሪዋን አቅርባለች።
አገራቸዉ ያቀረበችዉ የልማት አማራጭ ሃሳብ ባፋጣኝ ስራ ላይ ከዋለም የምዕተ አመቱ የልማት እቅድ ግቦችን እንደታሰበዉ መምታት ይቻላል በለዉ እንደሚያምኑ ነዉ ብራዉን የገለፁት።
የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሊየርም አገራቸዉ በዚህ አመት ያላትን የቡድን ስምንት አገራት ፕሬዝደንትነት አጋጣሚ በመጠቀም በተለይ ለአፍሪካ አገራት ሊደረግ ስለሚገባዉ የእዳ ስረዛ የበኩላቸዉን እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ቀጥሎም በተራ የሚዞረዉን የአዉሮፓ ህብረት የፕሬዝዳንትነት ስልጣን በመጪዉ ሐምሌ ብሪታንያ ስትረከብ ተጨማሪ እርዳታ ለአፍሪካ ይደረግ የሚለዉን ሃሳብ እንደምትገፋበት ተናግረዋል።
ባለፈዉ አመት ብሊየር በአህጉሪቱ እየተባባሰና እየከፋ የመጣዉን የድህነትና የሙስና ችግር ለማስወገድ የተሻለ መንገድ ያሉትን የአፍሪካ ኮሚሽን አቋቋሙ።
በርካቶች ሃሳቡን በፀጋ ቢቀበሉትም ይህ እዳ የመሰረዝ ነገር ምን አስከትሎ ይመጣ ይሆን በሚል ፍርሃት አንዳንዶች በጥርጣሬ ዉስጥ ናቸዉ።
በናይሮቢ የልማት አማካሪ የሆኑት ኤድዋርድ ኦዩጊ በዚህ በተሰወረዉ ቅድመ ሁኔታ ዉስጥ ለተጎዱት አገራት የሚሸታቸዉ ድብቅ ተልዕኮ አለ ይላሉ።
በተጨማሪም የአፍሪካ አገራትን ከእዳ ክፍያ ነፃ የማድረጉ ተግባር ወደአዲስ እዳ በአዲስ መንፈስ እንዲዘፈቁ የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸዉ።
ይህ ሁሉ ሃሳብ በዙሪያዉ ቢኖርም የብሪታንያዉ ብራዉን ካለፈዉ አመት የተፈጥሮ ጥበቃ የሰላም ኞቬል ተሻለሚ ከዋንጋሪ ማታይ ጋር ኬንያን ከደን መራቆት ለመታደግ የዛፍ ተከላ ተግባር አከናዉነዋል።
በመቀጠልም ጎረቤት ወደ ሆነችዉ አገር ወደ ታንዛንያ የተጓዙ ሲሆን በዚያም በዋና ከተማዋ በዳሬሰላም አካባቢ ከሚኖሩት ኗሪዎች ጋር ስላለባቸዉ የዉሃና የንፅህና አገልግሎት ችግር ተወያይተዋል።
ቻንስለሩ የአፍሪካ ጉብኝታቸዉን የሚያጠቃልሉት ዛሬ በሞዛምቢክ እሁድ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ይሆናል።
ብሪታንያ አፍሪካን የምትታደግበትን አዲሱን እቅዷን በቁርጠኝነት የያዘችዉ ይመስላል በእዳ እስከ አንገታቸዉ የተዘፈቁት በርካታዎቹ የአህጉሪቱ መንግስታትም ዘንባባ ዘንጥፈዉ እንኳን ደህና መጣሽ እያሏት ነዉ።