ቤን አኩር ቱኑዝያዊው የዲሞክራሲ ተሸላሚ
ሐሙስ፣ ጳጉሜን 1 2004ቱኒዝያዊው የህግ ባለሞያ ያድ ቤን አኩር እዚህ ቦን ውስጥ አለም ዓቀፍ የዲሞክራሲ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ። ቤን አኩር እጎአ ከጥር 2011ቱ የቱኒዝያ ህዝባዊ አብዮት በኋላ የመጨረሻው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ያበቃው የቱኒዝያ የተሃድሶ ኮሚሽን ሃላፊ ነበሩ ። ቤን ለዚህ ሽልማት የበቁት የቱኒዝያው ለውጥ እንዲሳካ ላደረጉት አስተዋፅኦ ነው ። የዶቼቬለዋ ሳራ ሜርሽ ያቀረበችውን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
እጎአ ጥር 14 2011 አም ምሽት ላይ የየቀድሞው የቱኒዝያ ፕሬዝዳንት ሲን አል አቢዲን ቤን አሊ ሃገሪቱን ጥለው መውጣታቸውን ሲሰሙ ያድ ቤን አኩር ከት ብለው ነበር የሳቁት ። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በፌስ ቡክ የተነዛ ወሪ ነበር የመሰላቸው ። ለ 23 አመታት ቱኒዝያን በብረት ጡጫ የገዙት አምባገነኑ መሪ እንዲህ በአንዴ ይጠፋሉ ብለው አላሰቡም ነበር ። ከጥቂት ቀናት በኋላ የህግ ባለሞያው ቤን አኩር በቱኒዝያ የፖለቲካ ተሃድሶ እንዲያካሂድ በተቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ ተሰየሙ ። ወደ ስራ የገቡትም በደስታና በትጋት በበቱኒዝያ በአፋጣኝ ዲሞክራሲ የማስፈን ተስፋ ጨብጠው ነበር ።
« ግብታዊ አብዮት ነበር ። ግርማ ሞገስ ባለው መሪ ሳይሆን ነፃነትና ዲሞክራሲ በጠየቁ ወጣቶች ነበሩ የሚመራው ። መልእክታቸው ዘመናዊነት ነበር ። ይህ አብዮት ከዚህ ቀደም ዲሞክራሲ የምእራባውያን ግኝት ነው የሚለውን የኖረ አስተሳሰብ አስወግዷል ። የሆነው ሁሉ ካለ አንዳች የውጭ ጣልቃ ገብነትነት ነው የተከናወነው ። »
በመሰረቱ የቤን አኩርና የኮሚሽኑ ባልደረቦች እቅድ የቀድሞውን የቱኒዝያ ህገ መንግሥት ማሻሻል ነበር ። ሆኖም ከህዝቡ በኩል ግፊቱ ከፍተኛ ነበርና አዲስ የህግ ስርዓት መዘርጋት የግድ ሆነ ። በመጨረሻም ጊዜያዊው መንግሥት ተስማምቶ እጎአ ጥቅምት 2011 በቱኒዝያ የመጀመሪያው ነፃ የህዝብ ተወካዮችና የህገ መንግሥት አርቃቂ ምክር ቤት ምርጫ ተካሄደ ። ቤን አኩር የሚመሩት ኮሚሽን ግን በዚህ ተግባር ብዙም አልተሳተፈም ። ያም ሆኖ በሚቀጥለው አመት አጋማሽ ላይ ህገ መንግግስቱ ተረቆ ያበቃል የሚል ግምት አለ ። ቤን አኩር ግን በተስፋ ና በቀቢፀ ተስፋ መካከል ናቸው ።
«በዲሞክራሲያዊ ህይወት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች ሁሌም በስኬት የተሞሉ ላይሆኑ ይችላሉ ። አጠቃላዩን ሥርአት ከመሠረቱ ነው የምንገነባው ። ዲሞክራሲያዊ ባህል ያለን የአውሮፓ አገር አይደለንም ። ይሁንና ሀ ብለም እንጀምራለን ።»
የቱኒዝያው አብዮት ከተካሄደ ከ 18 ወራት በኋላ የ67 አመቱ የ የቤን አኩር የቀድሞው ተነሳሽነት ቀንሷል ። ከአብዮቱ ወዲህ የቱኒዝያ የፖለቲካ ገፅታ እየተካረረ ሄዷል ። በተደጋጋሚ ጊዜያት የግራ መስመር ተከታዮችና ወግ አጥባቂ ኃይሎች ግፊት ያደርጋሉ ። የተለያዩ ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት የሽግግሩ መንግሥት አብዛኛው ሥልጣን አንሃንዳ የተባለው የሙስሊም ፓርቲ ነው ። ይህ ፓርቲ ደግሞ በአብዮቱ ሳይሳተፍ በየትኛውም መንገድ ሃይማኖታዊ አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው እንደ ቤን አኩር ።
« የምርጫው ውጤት ከአብዮቱ መንፈስ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ። በተቃውሞው ወቅት አንድም ሃይማኖታዊ መፈክር አልነበረም »
በቤን አኩር ቤተሰብ ፖለቲከኝነት የነበረ ነው ። አባታቸው የሰራተኞች ማህበር መሪ ፣ የህግ ባለሞያ ና ከዚህም በላይ የቱኒዝያውያን ሙፍቲ ነበሩ ። ወጣቱ ያዶህ በሃገራቸው በቱኒስያ ህግ አጥንተው በፓሪስ ፈረንሳይ ደግሞ በህግ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል ። እምብዛም በፖለቲካው ተሳታፊ ያልሆኑት ቤን አኩር ለመጀመሪያ ጊዜ እጎአ በ 1987 ቤን አሊ ሥልጣን ሲይዙ ነበር የህገ መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ መስራት የጀመሩት ። እጎአ በ1992 ፀረ ዲሞክራሲ የሆኑትን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች በመቃወምም ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ ። ወደ ፖለቲካው የተመለሱት ከቱኒዝያው አብዮት በኋላ ነው ። በቤን አኩር እምነት እስልምናና ዲሞክራሲ በትክክል አብረው መጓዝ ይችላሉ ። ሃገራቸው ቱኒዝያም ይህን መንገድ እንድምትከተል ተስፋቸው የፀና ነው ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ