1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤምባ ዕድሜ ልክ እሥራት ይጠብቃቸዋል

ቅዳሜ፣ መጋቢት 17 2008

የቀድሞ የኮንጎ ምክትል ፕሬዝዳንትና «የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ» መሪ ዣን ፒየር ቤምባ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ዴን ሐግ፤ ኔዘርላንድ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ሰኞ ብይን አስተላልፏል። የዓማፂ መሪው ከ14 ዓመታት በፊት ለተፈፀሙ ግድያዎችና የቁም ስቅሎች ዋነኛ ተጠያቂ መኾናቸው በተደጋጋሚ በመጠቀሱ ብይኑ የተጠበቀ ነበር።

https://p.dw.com/p/1IJPN
Den Haag Internationaler Strafgerichtshof IStGH / ICC
ምስል picture-alliance/dpa/M. Beekman

[No title]

ቁጥራቸው 1500 የሚደርስ «የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ» በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (MLC) ወታደሮች እንደ ጎርጎስሪዮስ አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም. በጎረቤት ሀገር መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ በርካታ ሴቶችን፤ ወንዶችን እና ሕፃናትን በማሰቃየት እንደገደሉ ይጠቀሳል። ዣን ፒየር ቤምባ በበኩላቸው ወታደሮቻቸው ከእሳቸው ቁጥጥር ውጪ የነበሩ መኾናቸውን በክስ ሒደቱ ወቅት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ብራዚላዊቷ ዳኛ ሲልቪያ ሽታይነር፦ በወቅቱ ዣን ፒየር ቤምባ ለወታደሮቻቸው መመሪያ ይሰጡ የነበሩ መኾናቸው በራሱ ማስረጃ ነው ብለዋል። «በአጠቃላዩ ወታደራዊ ተልዕእኮ ወቅት ወታደራዊ አመራሩ ይሰጥ የነበረው በቤምባ ሲሆን፤ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ የነበሩ ወታደሮቻቸውም በእሳቸው ቁጥጥር ስር ነበሩ» ሲሉ አክለዋል።

«የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ ወታደሮች ኃይል በመጠቀም እያወቁ ሆን ብለው ጥቃት በመፈጸም ጸያፍ በሆነ መንገድ የሴቶችን ማንኛውንም የተከፈተ አካል ደፍረዋል። እናም ሲቪል ማኅበረሰቡ ጥቃት የደረሰበት እንደተባለው በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ ቀዳሚ ዒላማ ተደርጎ ለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ደርሷል።»

ከ14 ዓመት በፊት መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ በዋናነት በደሉ የተፈፀመው የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አንጌ ፌሊክስ ፓታሴ ላይ በተቃጣው መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ወቅት ነው። የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ መሪ፦ ወታደሮቻቸውን ወደ ጎረቤት ሀገር የላኩት ፕሬዚዳንቱን ከፍራንሷ ቦዋዚዝ መፈንቅለ-መንግሥት ጥቃት ለመታደግ ነበር። በእርግጥ ፍራንሷ ቦዋዚዝ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2003 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት አንጌ ፌሊክስ ፓታሴ ላይ የተሳካ መፈንቅለ-መንግሥት ማከናወን ችለው ነበር። እሳቸውም ታዲያ አልቀረላቸውም፤ በጉልበት ከያዙት ሥልጣን ከዐሥር ዓመት ቆይታ በኋላ በተመሳሳይ መፈንቅለ-መንግሥት ተሰናብተዋል።

የቀድሞ የኮንጎ ምክትል ፕሬዝዳንትና «የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ» መሪ ዣን ፒየር ቤምባ
የቀድሞ የኮንጎ ምክትል ፕሬዝዳንትና «የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ» መሪ ዣን ፒየር ቤምባምስል picture-alliance/dpa/P. Dejong

ባለፈው ሰኞ የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ መሪ ዣን ፒየር ቤምባ ጥፋተኛ የተባሉበት በደል ጎረቤት ሀገር የላኳቸው 1,500 ወታደሮች በክፍያ ፈንታ ወንድ፣ ሴት፤ ሕፃን፣ አዋቂ ሳይሉ አስገድደው እንዲደፍሩ ተፈቅዶላቸዋል በሚል ነው።

«ከቀረቡት ምሥክሮች እንደተሰማው እና ከአጠቃላይ የፍርድ ሒደቱ እንደተብራራው ሚስተር ዣን ፒየር ቤምባ ወታደራዊ አዛዥ በነበሩበት ወቅት የጦር ወንጀል ድርጊት በመፈፀም፤ ሰብአዊነት በመፃረር ግድያ በመፈጸማቸው በአንቀጽ 28 ሀ፤ እንዲሁም ሰብአዊነትን በመፃረር በአስገድዶ መድፈር ድርጊት በአንቀጽ 7-1 ሰ መሠረት ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው አግኝቷቸዋል።»

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ዣን ፒየር ቤምባ ላይ የጥፋተኛነት ውሳኔ ባስተላለፈበት እለት የቀድሞ የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ አባል እና የቤምባ ቀኝ እጅ ዣክ ዦሊም ተገኝተው ነበር። ንቅናቄውን የመሠረቱት እሳቸው ናቸው።

«በአጠቃላይ የፍርድ ሒደቱ ፕሬዚዳንት ቤምባ ጥፋተኛ አለመኾናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን በጥንቃቄ ቃኝቷል። ሆኖም በውጤቱ ተበሳጭተናል» ብለዋል። ብራዚላዊቷ ዳኛ ግን ቤምባ ወደ እሥር ቤት እንዲመለሱ በተጨማሪ ወስነዋል።

ዳኛ ጆይስ አሎች፤ ብራዚላዊቷ የመሀል ዳኛ ሲልቪያ ሽታይነር እና ዳኛ ኩኒኮ ኦዛኪ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ
ዳኛ ጆይስ አሎች፤ ብራዚላዊቷ የመሀል ዳኛ ሲልቪያ ሽታይነር እና ዳኛ ኩኒኮ ኦዛኪ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድምስል picture-alliance/AP Images/J. Lampen

«በማስቀጠልም ሚስተር ዣን ፒየር ቤምባ ጎምቦ እስኪበየንባቸው ድረስ በእሥር እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።»

የሰኞ እለቱ ውሳኔ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ታሪክ አራተኛው መሆኑ ነው። በአሁኑ ወቅት ከ20 የማያንሱ አፍሪቃውያን በዴን ሐጉ ፍርድ ቤት ክሳቸው እየታየ ነው። አፍሪቃውያኑ ፍርድ ቤቱ እኛ ላይ ብቻ ሲሆን ይበረታል ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ። አንዲት የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ ደጋፊ በበኩላቸው «ምንም አዲስ ነገር የለውም ሁሉንም ነገር ሆን ብለው ነው፤ ይኼ ለአፍሪቃ እጅግ የሚያሳዝን ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ማሰቃየት እና አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ቤምባን ጥፋተኛ ያደረጋቸው በመሆኑ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ የክስ ሒደት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ ነበር። ውሳኔው በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎችም መነጋገሪያ ሆኗል። አንዲት የኦንላይን ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ በአስገድዶ መድፈር የጦር ወንጀል የተከሰሱ ግለሰብ ላይ ሦስት እንስት ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ውሳኔ ሲያስተላልፉ መመልከት ያኽል ጠንካራ ነገር የለም ሲሉ አስነብበዋል።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. የዛሬ ስምንት፥ ዓመት በወርኃ ግንቦት፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ቤምባ ላይ የክስ ሒደቱ የጀመረው ከ2 ዓመታት በኋላ ኅዳር ወር ውስጥ በ2010 ዓም ነበር። ጥፋተኛ የተባሉት የኮንጎ ነጻ አውጪ ንቅናቄ መሪ ዣን ፒየር ቤምባ ላይ ብይኑ ወደፊት ይሰጣል፤ ያኔ የሚጠብቃቸው የዕድሜ ልክ እሥራት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ