1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለቤት ያላገኙት የ40/60 የቁጠባ ቤቶች

ሰኞ፣ ሰኔ 12 2009

40/60 በመባል የሚታወቁትና ግንባታቸው ተጠናቆ በመጋቢት ወር የተመረቁት 1292፤ የቁጠባ ቤቶች እስካሁን ለባለ እድለኞች አልተላለፉም። ዛሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጸው የቤቶቹን ርክክብ በያዝነዉ ሰኔ ወር ውስጥ ይጨርሳል። እጣ የሚወጣው ደግሞ ከርክክቡ በኋላ ይባል እንጂ መቼ እንደሚካሄድ ቀነ ሰሌዳዉ አልተቀመጠለትም።

https://p.dw.com/p/2eovg
Äthiopien Sozialwohnungen in Addis Abeba
ምስል Y. G/Egziabher

40/60 Sozialbau Projekt in Addis - MP3-Stereo

የ40/60 የቁጠባ ቤቶች መርኃ ግብር ምዝገባ ከተካሄደ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። በወቅቱ ከ 164,000 በላይ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበዋል። ከነዚህ ተመዝጋቢዎች አንዷ መኖርያ ቤት ለማግኘት እስካሁን በቁጠባ ላይ ብትሆንም ይደርሰኛል የሚል ተስፋ እንደሌላት የዶይቸ ቬለ ገልጻለች። ይህም ቁጠባውን ስላላጠናቀቀች ነው። ሌላው በዚህ የቁጠባ መርኃ ግብር ፈፅሞ እምነት አጥቶ ጭራሽ መቆጠቡን ያቋረጠው ግለሰብ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ጥያቄ  ውስጥ ይከታል። ለምሳሌ ለምን 40 በመቶ የቆጠቡ የእጣው ተሳታፊ እንደማይሆኑ እና ግንባታው ለምን እጅግ አዝጋሚ እንደሆነ ነው።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በልሁ ታከለ እንደገለፁልን ባንኩ የቤቶቹን ርክክብ በያዝነዉ ሰኔ ወር ውስጥ ይጨርሳል። ከዛም እጣው ይወጣል። በቤቶቹ ላይም የዋጋ ማሻሻያ ይደረጋል። አቶ በልሁ የዋጋው ልዩነት ወይም የሚደረገው ማሻሻያ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለጊዜው መረጃ የለኝም ብለዋል። አቶ በልሁ የቤቱ ግንባታ እና ርክክብ ለምን እስካሁን ዘገየ ለሚለው ጥያቄ ይህን የባንኩ የሥራ ድርሻ አድርገዉ አይመለከቱትም።

በንግድ ባንኩ መረጃ መሰረት ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ከ 164,000 በላይ ሰዎች በቤት ቁጠባው መርኃ ግብር ቢመዘገቡም በተግባር አሁን ድረስ እየቆጠቡ የሚገኙት 142,000 ገደማ ናቸው።  ከነዚህም መካከል መቆጠብ የሚገባቸውን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁት 17,000 ገደማ ደርሰዋል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ