1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡድን 20 ምጣኔ ሐብታዊ ወይስ ፖለቲካዊ?

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2007

አንዱ ቡድን በ15ለ 1 ተፃራሪ ሐይላት የተወጠረ፤ በ4መሐል ሰፋሪዎች የተትመከመከ መሆኑን መስካሪ ነዉ።ለዘንድሮዉ ጉባኤ የመነጋገሪያ ርዕስ፤ የአቋም መግለጫምከቡድኑ ይፋዊ አላማ ጋር የሚጣጠም ነዉ።ምጣኔ ሐብት።

https://p.dw.com/p/1Dor3
ምስል Andrew Taylor/G20 Australia via Getty Images

የቡድን ዉስጥ ተፃራሪ ቡድናት የፈጠሩት ሐይላት 15ለ1 እንድተ ወጋገዙ፤ እንደ ተዛዛቱ፤ መሐል ሰፋሪዎቹ እንዳደፈጡ ጉባኤያቸዉ አበቃ ፣ እንደ ስማቸዉ ሁሉ ቡድናቸዉ አንድ፤ ቁጥራቸዉ 20 ነዉ።ጉባኤያቸዉ የጋራ ርዕሳቸዉ የወል-አስተናጋቸዉም አንድ ነዉ።ብሪስበን-አዉስትሬሊያ።ባንድ የተቧደኑት ወይም መቧደናቸዉን ላለፉት ሰባት ዓመታት የነገሩን መሪዎች-ላንድ ጉባኤ በታደሙበት ያሉ፤ ያደረጉት ግን አንዱ ቡድን በ15ለ 1 ተፃራሪ ሐይላት የተወጠረ፤በአራት መሐል ሰፋሪዎች የተትመከመከ መሆኑን መስካሪ ነዉ።ለዘንድሮዉ ጉባኤ በይፋ የተዘጋጀዉ የመነጋገሪያ ርዕስ፤ ይፋዊዉ የአቋም መግለጫም ከቡድኑ ይፋዊ አላማ ጋር የሚጣጠም ነዉ።ምጣኔ ሐብት።የቡድን ዉስጥ ተፃራሪ ቡድናት የፈጠሩት ሐይላት 15ለ1 እንድተ ወጋገዙ፤ እንደ ተዛዛቱ፤ መሐል ሰፋሪዎቹ እንዳደፈጡ ጉባኤያቸዉ አበቃ። ትናንት።ጉባኤ መነሻ፤ ዓላማዉ ማጣቀሻ የጉባኤተኞቹ ልዩነት፤ የዓለም ዕዉነትመድረሻኝን ነው።

ዓለምን ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ለማስወገድ በጋራ እንዲመክር-እንዲጥር ጥር በ1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በተሰየመዉ ሥብስብ ዉስጥ ሁለቱም የሰሜን አሜሪካ ሐገራት አባል ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ።ከመካከለኛዉና ደቡብ አሜሪካ ሰወስት ሐገራት አሉ- ሜክሲኮ፤አርጀቲና እና ብራዚል።

እስያን-ሩቅም፤ደቡብ ምሥራቅም፤ መካከለኛዉ ምሥራቅም ተብሎ ቻይና፤ጃፓን፤ሕንድ፤ኢንዶኔዢያ፤ሳዑዲ አረቢያ፤ ደቡብ ኮሪያ እና ግሚስ አዉሮጳዊቱ ቱርክ ወክለዋታል።ድምር-ሰባት።ከኦሺኒያ-ያዉ አዉስትሬሊያ አለች።አዉሮጳ ከምዕራብ፤ ብሪታኒያ፤ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤ኢጣሊያ አሉ፤ የአዉሮጳ ሕብረትም እንደ ሐገር ሙሉ አባል ነዉ።አራት ሲደመር አንድ-አምስት።ከምሥራቅ አዉሮጳ-ሩሲያ ናት።ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ችግር ካለባት ከደሐይቱ አፍሪቃ ሥለ ምጣኔ ሐብት ችግር ለሚመክር-ለሚወስነዉ ቡድን አባልነት የበቃችዉ ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ናት።

የ19ኙ ሐገራትና የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች የሞሪታንያ፤የሴኔጋል፤ የስፓኝ፤ የምያንማር፤ የኒዉዚላንድ እና የሲንጋፑር አቻዎቸዉን በንግድነት፤ ከሰወስት ሺሕ ዘጠኝ መቶ በላይ ባለሥልጣኖቻቸዉንና አማካሪዎቻቸዉን እና የድርጅት መሪዎችን እስከትለዉ ብርስበን-አዉስትሬሊያን አጨናንቀዋት ሰነበቱ።

የጉባኤዉ እስተናጋጅ የአዉስትሬሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒይ አቦት እንዳሉት የጉባኤዉ ትኩረት እንደ ስብስቡ የጋራ-አላማ ሁሉ ምጣኔ ሐብትን ማሳደግ ነዉ።«የላቀ (ምጣኔ ሐብታዊ) ዕድገትና ተጨማሪ ሥራ።በነዚሕ ሁለት ቀናት ትኩረት እንዲሰጣቸዉ የምፈልጋቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።ዓለም ከኛ የሚጠብቀዉም ይሕንን ነዉ።ተጨማሪ ዕድገትና የሥራ ቦታ ይፈልጋሉ።ይሕን ማድረግ የኛ ፈንታ ነዉ።»

BRICS am Rande des G20-Gipfel in Brisbane 15.11.2014 Dilma Rousseff
ምስል picture-alliance/dpa/Druzhinin Alexei

እንደተባለዉ የዓለም ምጣኔ ሐብት በጉባኤዉ ላይ ተነስቷል።ጉባኤተኞች ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫም እስከ 2018 ድረስ የ2.1 ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ለማስዝገብ ቃል ገብተዋል።የቃሉ-እዉነት ሐሰትነት የሚለየዉ በርግጥ ከሰወስት ዓመት በኋላ ነዉ።ጉባኤዉ ግን ለአዉስትሬሊያ በታሪኳ የመጀመሪያዉ ታላቅ ድግስ ነበር።

ብሪስበን ካለፈዉ አርብ እስከትናንት መሪዎቹን ጨምሮ በአራት ሺሕ ጉባኤተኞች፤ ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ በሚበልጡ ጋዜጠኞች ተጥለቅልቃ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ አቦትም በመሩት ጉባኤዉ ሒደትና ዉጤት ረክተዋል።«ዘንድሮ ቡድን 20 ተጨባጭና ገቢራዊ ዉጤት አሳይቷል።ቡድን 20 ባለፉት 48 ሰዓታት በተደረገዉ ጉባኤዉ ባሳረገዉ የአንድ ዓመት ጥረቱ፤ የዓለም ሕዝብ መብት የተሻለ ይሆናል።ይሕ ነዉ ቁም ነገሩ።»

ይበሉ እንጂ ከጉባኤዉ ዋዜማ እስከ ፍፃሜዉ ጉባኤተኞች ከምጣኔ ሐብቱ ይልቅ በፖለቲካዉ፤ከዓለም ይልቅ በአንዲት ዩክሬን ሰበብ ጎራ ለይተዉ ሲወጋገዙ፤ ሲነታረኩ ነዉ የሰነበቱት።የቃላቱን ጦርነት ከመሪዎቹ ቀድመዉ የከፈቱት መገናኛ ዘዴዎች ነበሩ።

የአዉስትሬሊያ መገናኛ ዘዴዎች «ዩክሬንን የወረሩ» ያሏቸዉ የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት በጉባኤ ቢገኙ «ትደግፋላችሁ-ትቃወማላችዉ» የሚል ይዘት ያለዉ መጠይቅ ለሕዝብ በተኑ።ከተጠየቀዉ አርባ ዘጠኝ በመቶዉ ፑቲን ለጉባኤዉ መጋበዝ የለባቸዉም አለ።መገናኛ ዘዴዎቹ «ንቃተ-ሕሊናቸዉን ካዳበሩላቸዉ» እንዷ እንዲሕ አሉ።«ለቡድን 20 ጉባኤ እዚሕ የሚሰበሰቡት መሪዎች የሚስተር ፑቲንን እና የሩሲያ ፌደሬሽንን ወራሪነት አምነዉ፤ዩክሬንን ለበርካታ ዓመታት በምታሸማቅቀዉ ሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ እንፈልጋለን።»

የሩሲያ መገናኛ ዘዴዎች አጻፋ ቀላል አልነበረም«አፍቃኒስታንን፤ ኢራቅን፤ ሊቢያን ሌላም ጨማምረዉ «የወረረዉ ማነዉ?» የሚሉ ቃላት ተኮሱ።ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሞስኮ ከመነሳታቸዉ በፊት የሩሲያ የጦር መርከቦች አዉስትሬሊያ ወደምታዋስነዉ ዓለም አቀፍ ባሕር ቀዘፉ።የአዉስትሬሊያ የጦር ጄቶችና መርከቦች ባንጻሩ የሩሲያ መርከቦችን እንቅስቃሴ ይቆጣጠሩ ገቡ።

Symbolbild G20-Gipfel in Brisbane Putin verlässt Gipfel vorzeitig
ምስል Alain Jocard/AFP/Getty Images

የመሪዎቹ ዛቻ-ማስፈራራት ቀጠለ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ገና ጉባኤዉ ሳይጀመር ሩሲያን አስጠነቀቁ።«ሩሲያ ነገሩን ካባባሰች ተጨማሪ ማዕቀብ እንጥላለን።ይሕን ያሕል ቀላል ነዉ።»የካናዳዉ ጠቅላይ ሚንስትር ስቴፋን ሐርፐር «ሩሲያ ከዩክሬን መዉጣት አለባት» አሉ።

የጉባኤዉ አስተናጋጅ የአዉስትሬሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ አቦት ፑቲንን ለማዉገዝ ያሳበቡት ባለፈዉ ሐምሌ ከኔዘርላንድስ ወደ አዉስትሬሊያ ሲበር ዩክሬን አየር ክልል ተምትቶ የጋየዉን የመንገደኞች አዉሮፕላን ነዉ።«በአደጋዉ ለሞቱት አዉስቴሬሊያዌዉያን ፑቲን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸዉ»

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜልክም ፑቲን የዩክሬን አማፂይንን መርዳታቸዉን ካላቆሙ ምዕራባዉያን መንግሥታት በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠነቀቁ።«(ማዕቀብ የሚጣልባቸዉ) የተጨማሪ ሰዎች ሥም ዝርዝር ካጀንዳችን ዉስጥ መኖሩን አስታዉቃለሁ። ግጭቱ ከቀጠለ ይሕ ፖለቲካዊ-መልከዓምድራዊ ጠብ ቢባባስ በኛ በአዉሮጳዉያን በኩል ሊገርመን አይገባም።አሁንም የሻከረዉ ከሩሲያ ጋር ያለን ግንኙነትን ይበልጥ ማወኩ የማይቀር ነዉ።»

የፕሬዝዳንት ፑቲን አፀፋ የተጣለዉም ሆነ የሚጣለዉ መዕቀብ ጉዳት መንታ የሚል ነበር።ማዕቀብ የጣሉና የሚጥሉትንም ሩሲያንም የሚጎዳ።«ማዕቀቦቹ የሚጎዱት፤ የተጣለባቸዉንም፤የሚጣልባቸዉንም ነዉ።»

G20 Gipfel Angela Merkel 15.11.2014
ምስል picture-alliance/RIA Novosti/S. Guneev

የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።የአዉሮጳ ሕብረትን ጨምሮ የምዕራባዉያን ሐገራት መሪዎች በየተራ ያወገዛቸዉን ፕሩዝዳንት ፑቲንን፤ የምዕራባዉያኑ ደጋፊ ሐገራት መሪዎችም ሸሸት-እራቅ እይሏቸዉ ያዙ።በፕሬዝዳንት ፑቲንን የማዉገዝ፤ ማስፈራራት የመነጠሉ ዘመቻ በዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ማስጠንቀቂያ አሳረገ።

ኦባማ-የሐገራቸዉን ብቸኛ ልዕለ-ሐያልነት ረገጥ-አድርገዉ በመናገር ሩሲያ እንደማትመጥናት በሾርኒ አስታወቁ። «ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር በደስታ የምንቀበለዉ ልዩ ሐላፊነት ዓለብን።አሸባሪዉን ISILን ለመደምሰስ በሚደረገዉ ዉጊያ ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ እየመራን ነዉ።ኢቦላን ለመከላከል የሚደረገዉን ጥረት እመራን ነዉ።ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን በመቃወምም ዓለምን እየመራን ነዉ።የበረራ ቁጥር MH17 አዉሮፕላን በመታቱ እንደታየዉ ወረራዉ ለዓለም ሥጋት ነዉ።»

የምዕራባዉያኑ መንግሥታት ማሕበር መሪዎች-ከተከታዮቻቸዉ ጋር አንዱን ፑቲንን ሲያወግዙ-ሲያስፈራሩ፤ ሲያገልሉ፤ ፑቲን ሲከላከሉ የተቀሩት አራቱ በገለልተኛነት መቆየቱን ነዉ የመረጡት።ወይም የመሰሉት።አራቱ BRICSየተሰኘዉ ማሕበር ከሩሲያ ጋር የሚያስተሳስራቸዉ፤ አነሰም በዛ የምዕራቡን ዓለም ጫና ለመቀበል የሚያንገራግሩ ናቸዉ።ብራዚል፤ቻይና፤ሕንድ እና ደቡብ አፍሪቃ።

G20-Gipfel in Brisbane Deutschland Russland 15.11.2014
ምስል picture-alliance/dpa/Nietfeld

ወቀሳ ትችቱ ያየለባቸዉ ፕሬዝዳንት ፑቲን እስከ ጉባኤዉ መዝጊያ አልጠበቁም ወደ ሐገራቸዉ ተመለሱ።ፕሬዝዳንት ኦባማ ግን የሩሲያን ያክል አይሁን እንጂ ለቻይናም አልተመለሱ።

«ቻይና ም በንግድ፤ ይሁን በባሕር ሌሎቹ ሐገራት የሚያከብሩትን ሕግ እንድታከብር እናበረታታለን።በዚሕ ጉዳይ የልዩነታችንን ምክንያት ግልፅ ማድረግ አለብን።»

የብሪስተኑ ጉባኤ የተጠናቀቀዉ የበርሊን ግንብ መናድ የጀመረበት 25ኛ ዓመት በተከበረ በሳምንቱ ነዉ።ግንቡ ሲናድ በዉጤቱም የኮሚንስት-ካፒታሊስቱ ዓለም የጦር ፍጥጫ ሲያበቃ፤ ብዙ ታዛቢዎች እንደሚስማሙበት፤ የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብ በያለበት የፈነደቀ-ጮቤ የረገጠዉ ዓለም ሠላም ትሆናለች በሚል ትልቅ ተስፋ ነበር።

ግንቡ የተናደበት 25ኛ ዓመት ከመከሩ ከጥቂት ወራት በፊት ባለፈዉ መስከረም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ግን ዓለም ከሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በማታዉቀዉ ጦርነት፤ግጭት፤በሽታ፤ በሕዝቦች ሞትና ስደት ተመሰቃቅላላች።

የበርሊን ግንብ እንዲናድ ከፍተኛዉን አስተዋፅኦ ያደረጉት፤ የቀድሞዋን ኮሚንስታዊት ልዕለ ሐያል ሐገር ሶቭየት ሕብረትን ካናቷ ቀጥቅጠዉ የፈረካከሷት የመጨረሻ መሪዋ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ መሆናቸዉ ብዙ አያከራክርም።ጎርቫቾቭ የበርሊን ግንብ መናድ የጀመረበት ሃያ-አምስተኛ ዓመት በዓል ሲከበር እንዳሉት የዛሬ-ሐያአምስት ዓመቱ ተስፋ-ዛሬ የለም።

በጦርነት፤ በሽታ፤ በሕዝብ ስደት የተመሰቃቀለችዉ ዓለም ወደ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን እንዳትዘቅጥ ያሰጋል። ከስጋት ያዉጣን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ