1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡድን-ስምንት፤ የፊናንሱ ቀውስና ንግድ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 1 2001

ቡድን-ስምንት በመባል የሚታወቁት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታትና ሩሢያ ዛሬ ኢጣሊያ ከተማ ል-አኪላ ውስጥ ሶሥት ቀናት የሚፈጅ ጉባዔያቸውን ከፍተዋል።

https://p.dw.com/p/IjnD
አስተናጋጁ ሢልቪዮ ቤርሉስኮኒ
አስተናጋጁ ሢልቪዮ ቤርሉስኮኒምስል AP

ጉባዔው ከሚያተኩርባቸው ዓበይት አርዕስት አንዱ ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሲሆን ከነገ ጀምሮ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሕንድንና ብራዚልን የመሳሰሉት መንግሥታት መሪዎችም በንግግሩ ይሳተፋሉ። ከቀውሱ አኳያ ዓለምአቀፉን ኤኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃር እስካሁን የተወሰዱትን ዕርምጃዎች መከለሱ ዋነኛው ተግባር ነው። በሌላ በኩል የቡድን-ስምንትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቡድን-አምሥት ሃገራት መሪዎች የዓለም ንግድ ድርጅትን የዶሃ ድርድር ዙር እስከሚቀጥለው 2010 ዓ.ም ከግቡ ለማድረስ ሊስማሙ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

የሶሥት ቀናቱ ጉባዔ ለቡድን-ስምንት መሪዎች ቀውስ የተጠናወተውን የዓለም ኤኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ነው የሚታመነው። እርግጥ አንዴ የዓለምን ዕርምጃ ለብቻቸው ይዘውሩ የነበሩት ሃያላን መንግሥታት ዛሬ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናን የመሳሰሉ መንግሥታት የሚገኙበት የቡድን-ሃያ ስብስብ ጥላ ጋርዷቸው ነው የሚገኙት። የዓለምን ችግር ለብቻቸው ሊወጡት እንደማይችሉ ግልጽ ከሆነ ውሎ አድሯል። እናም በዓለም ላይ የሃይል ሚዛን መለወጡን በማጤን ቻይና፣ ሕንድና ብራዚል በጉባዔው እንዲሳተፉ መጋበዛቸውም ለዚህ ነው። ቀውሱ በታዳጊ አገሮች ላይ ያስከተለው ቀውስ ደግሞ የመጨረሻው ቀን የውይይት ርዕስ ሲሆን ቡድኑ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎችን መጋበዙም አልቀረም።

እርግጥ የበለጸጉት መንግሥታት ቀውሱን ለመታገል ካፈሰሱት ግዙፍ በጀት አንጻር ለታዳጊ አገሮች ጠብ የሚል ነገር መኖሩ ብዙዎችን እያጠራጠረ ያለ ጉዳይ ነው። ከመቼውም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የልማት ዕርዳታ እንዳይቀነስ ከሚሰጉት መካከል አንዱ የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ጀርመናዊው የርን ካሊንስኪ ናቸው።

“ፈተናው ትልቅ እንደመሆኑ መጠን ከጉባዔው የምንጠብቀው ብዙ ነው። ፍላጎታችን ይሟላ-አይሟላ ግን አጠራጣሪ ሆኖ ይቀጥላል። ለዚህም ምክንያት አይታጣም። ለምሳሌ ኢጣሊያ የልማት ዕርዳታውን ለመቀነስና ይሄው የሚቀርብበትን ሁኔታም ለማጥበብ እንደምትፈልግ እያየን ነው። ይህ ደግሞ ጎጂ ሂደት ነው። በሌላ በኩል በፕሬዚደንት ኦባማ መሪነት አሜሪካ በዚህም ዘርፍ አንቀሳቃሽ ሞተር የመሆኗ ተሥፋ አለ። ከዚሁ በተጨማሪ የጀርመን መንግሥትም የልማት ዕርዳታውን ከፍ ለማድረግ በገባው ቃል እንደምትጸና ተሥፋ እናደርጋለን”

የዕርዳታው ተሥፋ በቀውሱ ማገገም ላይ ጥገና ይሆናል ማለት ነው። የማገገም ሂደት አለ መባሉም አልቀረም። የበለጸገው ዓለም የፊናንስ ገበዮችን ለማረጋጋትና ቀውሱን ለማታገል ያፈሰሰው በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ ችግሩን ማለዘብ እንደጀመረና አዝማሚያው አበረታች እንደሆነ በተደጋጋሚ መነገር የያዘ ጉዳይ ነው። የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክልም በቡድን-ስምንት ጉባዔ ዋዜማ ባለፈው ሣምንት በአገሪቱ ፌደራል ም/ቤት በሰጡት መንግሥታዊ መግለጫቸው ይሄው መሻሻል እንደሚታያቸው ሲናገሩ ባለፈው ሚያዚያ ወር የቡድን-ሃያ የለንደን የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ላይ የተደረገው ስምምነት በፍጥነት ገቢር እንዲሆን ነበር ያሳሰቡት።

“በወቅቱ ባንኮች በተወሰነ የማገገም ሂደት ላይ እንዳሉ፤ ተጨማሪ ዕርምጃዎች ለመውሰድ ቅልጥፍና ማሣየት እንደያዙ ነው የምንታዘበው። በጉባዔው ላይ፤ ከወዲሁ ሰፊ የሃሣብ አንድነትም አለ፤ ይህን መሰሉ ቀውስ እንዳይደገም አዲስ ዓለምአቀፍ የገበዮች ሕግ መርህ በማስፈኑ ላይ ነው የምንጸናው”

ጉባዔው ጭብጥና ተግባራዊ ውጤት ላይ መድረሱን መጨረሻውን ጠብቆ መታዘቡ ለጊዜው ግድ ነው። በሌላ በኩል የቡድን-ስምንት መሪዎችና ቡድን-አምሥት፤ ማለት ብራዚል፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ሜክሢኮና ደቡብ አፍሪቃ ለዓመታት ሲጓተት ቆይቶ የከሸፈውን የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር በሚቀጥለው 2010 ዓ.ም. በስኬት ከግቡ ለማድረስ ከወዲሁ ሳይስማሙ አልቀሩም። የመንግሥታቱ መሪዎች በጉዳዩ በተሰናዳ ረቂቅ መግለጫ ላይ ነገ በሚያካሂዱት ንግግር ስምምነቱን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ፍትሃዊ ንግድን በማስፈን የታዳጊውን ዓለም ዕድገት ለማራመድ በሚል የዶሃው ድርድር የተጀመረው እ.ጎ.አ. በ 2001 ዓ.ም. ነበር። ይሁንና የበለጸገው ዓለምና የታዳጊ አገሮች ቅራኔ ሊወገድ ባለመቻሉ ባለበት ሲጎተት ስምንት ዓመት ገደማ አልፎታል። እርግጥ የዓለም ንግድ ድርጅት ሃላፊ ፓስካል ላሚይም በመጪው ዓመት ስምምነነቱ ሊሰፍን እንደሚችል ትናንት ጀኔቫ ላይ ጠቁመዋል። ለዚሁ ምክንያትም ሕንድና አሜሪካ አዳዲስ የንግድ ተጠሪዎች ከሰየሙ ወዲህ የድርድሩ መንፈስ መሻሻሉ ነው።

በአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ስብሰባ አኳያ ባለፈው ሰኔ ወር የተገናኙት የንግድ ሚኒስትሮችም ቡድን ስምንትና ቡድን-አምሥት በመስከረም ወር የፒትስበርግ የቡድን-ሃያ መንግሥታት ጉባዔ ላይ በሚቀርብ ድርድሩን ለማጠቃለል በሚያስችል ዝርዝር መርህ እንደሚስማሙ ተሥፋቸውን ገልጸው ነበር። ይህ ቢሳካ በዓመቱ መጨረሻ በሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጉባዔ አኳያ ተከታይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ተካሂዶ በ 2010 መጀመሪያ የድርድሩን ዙር እንዲያጠናቅቅ ነው የታሰበው። ሆኖም ይህ ለጊዜው ተሥፋ ብቻ ነው።

በነገራችን ላይ ውሉን ለማስፈን የሚታሰበው እስካሁን በድርድሩ ተገኝቷል በተባለ ዕርምጃ ላይ በመመስረት ነው። በሌላ በኩል የዶሃው ድርድር መሰናከል ምክንያት በተለይ የበለጸጉት መንግሥታት የታዳጊውን ዓለም ገበሬ የገበያ ተፎካካሪነት ብቃት አስሮ የያዘ የእርሻ ድጎማቸውን በሚገባ ለመቀነስ ዝግጁ አለመሆናቸው እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ በኩል ለውጥ ካልተደረገ ታዲያ ወደፊት መራመድ መቻሉ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው።

የእርሻ ድጎማ ነገር ከተነሣ ተጎጂዎቹ መጠኑና መልኩ ይለያይ እንጂ የአፍሪቃ ብቻ ሣይሆን የበለጸገው ዓለም አነስተኛ ገበሬዎችም ጭምር ናቸው። ለምሳሌ በዚህ በጀርመን ከብት አርቢዎች ከገበያ በሚያገኙት የወተት ዋጋ መኖር አልቻልንም ሲሉ ያማርራሉ። በአፍሪቃም ይበልጥ ጥጥ አምራች ገበሬዎች ከገበያ ተጠቃሚ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ለድህነት እየተጋለጡ ነው። የእነዚህ የሁለቱም ችግሮች መንስዔ ደግሞ የደጎማው ፖሊሲ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም።

ለምሳሌ ያህል በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ለአንዲት ላም የቀን ግጦሽ ግብር ከፋዩ ነዋሪ 2,50 ኤውሮ ያወጣል። ከጠቅላላው የሕብረቱ በጀት ግማሹ የሚፈሰውም ለእርሻ ልማት ድጎማ ነው፤ ምንም እንኳ በግብርና የሚተዳደረው ነዋሪ ከሶሥት በመቶ ያነሰ ቢሆንም! በአንጻሩ በአብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች እስከ 80 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በእርሻ ተዳዳሪ ነው። ታዲያ በዚህ መስፈርት በመሠረቱ የአውሮፓ ገበሬዎች ከሁሉም በላይ ጥሩ ኑሮ መግፋት ነበረባቸው። ተጠቃሚውም እንዲሁ መርካት በተገባው ነበር። ምክንያቱም ዜጎች ከሚከፍሉት ግብር የሚፈሰው ድጎማ ዓላማ ለሁሉም በቂና ጤናማ ምግብ ማቅረብ ማስቻል ነው።

ግን ሃቁ ሌላ ነው። ድጎማውን የሚያገኙት ትናንሾቹ ገበሬዎች ሣይሆኑ ታላላቆቹ ምግብ አምራች ፋብሪካዎችና ኩባንያዎች ናቸው። ይህም በመሆኑ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ 60 በመቶው ትናንሽ ገበሬዎች ከጠቅላላው ድጎማ የሚያገኙት ድርሻ ከአሥር በመቶ አይበልጥም። በአንጻሩ ሁለት በመቶው ግዙፎቹ ሩቡን ያገኛሉ። በአሜሪካም ቢሆን 60 በመቶው ገበሬ ከመንግሥት የሚያገኘው አንዳች ድጎማ የለም። ከጠቅላላው የመንግሥት ድጎማ 72 በመቶውን የሚውጡት አሥር ከመቶው ሃብታሞች ናቸው። እንግዲህ በአውሮፓና በአሜሪካ ምን ያህል ይመረት ብዙም ክብደት የለውም። ገንዘብ የሚገኘው በምርት ሣይሆን በድጎማ ነው። ይሁን እንጂ የተትረፈረፈ ምርት በዓለም ገበዮች ላይ ዋጋን በመጫን ለምሳሌ የአፍሪቃውን ጥጥ አምራች ገበሬ ሊጎዳ ይችላል።

አሜሪካ ከ 2001 እስከ 2002 ማለት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጥጥ አምራች ገበሬዎቿ ያፈሰሰችው ድጎማ አራት ሚሊያርድ ዶላር ይደርስ ነበር። ይህም ጠቅላላው ምርት በዓለም ገበያ ካስገኘው የበለጠ መሆኑ ነው። ባለሙያዎች እንደሚገምቱት ይሄው ድጎማ የአፍሪቃን ጥጥ አምራች ገበሬ በዓመት ከ 250 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያሳጣ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ለውድቀት የሚዳርግም ነው። ድጎማው ቢቀር አፍሪቃ ከአሁኑ 75 በመቶ የበለጥ ጥጥ ወደ ውጭ ለመሸጥ በቻለች ነበር። የዶሃውን ድርድር በዕውነት በስኬት ለማጠቃለል ከተፈለገ ከሁሉም በላይ ይህ የእርሻ ድጎማ ፖሊሲ በአግባብ መቀየሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው የሚሆነው።

MM/DW/AFP