1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡድን ስምንት እና የሰሞኑ ጉባኤዉ

ሰኞ፣ ግንቦት 22 2003

የስድስቱን ሐገራት መሪዎች ሻቱ ዶ ራምቡዬ ላይ ለጉባኤ ያሰባሰበዉ በ1973ቱ የአረብ-እስራኤል ጦርነት ሰበብ የአረብ ሐገራት ነዳጅ ዘይት ላለመሸጥ ማደማቸዉ፥ በኢንዱስትሪ በበለፀገዉ ዓለም ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ነበር።

https://p.dw.com/p/RQsG

30 05 11

ዶቪል ፈረንሳይ-ባለፈዉሳምንት ሐሙስና አርብ።ከ1975 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በየአመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ የቡድን ሥምንት አባል ሐገራት መሪዎች ዘንድሮም ለአንድ ቀን ተኩል ያሕል ዶቪል ተሰበሰቡ። ወሰኑ። ሔዱም።የጉባኤዉ ሒደት መነሻ፥ የቡድኑ ማንነት፥ ማጣቃሻ፥ የጥቂቶቹ ስብሰባ-ዉሳኔ ትልቅ ተስዕኖ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዝዳት ቫለሪ ዢስካር ዴ ስታንግ በ1975 የሐገራቸዉን የቅርብ ወዳጅ-እኩያ፥አምስት ሐገራት መሪዎችን ጉባኤ ሲጠሩ ከጉባኤተኞቹ ዕቅድ የወደፊት አላማ ይልቅ መከካለኛዉ ምሥራቅ ከዚያ በፊት እንደነበረበት ዘመነ-ዘመናት ሁሉ አለምን የማሳሰቡ፥ ምናልባት ዳግም የመየቀሩ እዉነት ነበር የደመቀዉ።

በርግጥም የስድስቱን ሐገራት መሪዎች ሻቱ ዶ ራምቡዬ ላይ ለጉባኤ ያሰባሰበዉ በ1973ቱ የአረብ-እስራኤል ጦርነት ሰበብ የአረብ ሐገራት ነዳጅ ዘይት ላለመሸጥ ማደማቸዉ፥ በኢንዱስትሪ በበለፀገዉ ዓለም ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ነበር።ጉባኤተኞቹ የነዳጅ እጥረቱ ያደረሰባቸዉን ኪሳራ ገምግመዉ አድማዉ እንዳይደገም አስጠንቅቀዉ፥ ቢደገም አድማኞችን የሚቀጡበትን ሥልት ነድፈዉ ነበር የተለያዩት።

በዚሕም ሰበብ ይመስላል የያኔዎቹ የፖለቲካ ታዛቢና ተንታኞች «ጉባኤዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ አለምን ሲለዉጥ የለዉጡ ሒደት የሐብታም-ሐያላኑን ሐገራት ጥቅምና ፍላጎትን በማይፃረር መንገድ ለማሾር የመከሩ-የወሰኑበት» ከማለት ባለፍ የስብስቡን የወደፊት አለማ፥ እቅድና ጉልበት ብዙም ያላተኮሩበት።

በፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ቫለሪ ዢስካር ዴ ስታን ጋባዢነት የተሰበሰቡት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ጄራልድ ፎርድ፥ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሐሮልድ ዊልሰን፥ የኢጣሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አልዶ ሞሮ፥ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ታከኦ ሚኪ እና የምዕራብ ጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ሔልሙት ሽሚት በያኔ ጉባኤቸዉ ማሳረጊያ ከዋና ዉሳኔያቸዉ ግርጌ እንደ ዘበት የጠቀሷት ሐሳብ የዛሬዉን ስብስብ፥ የስብስቡንም ጉልበት ፈጠረች።

ያ የመካከለኛዉ ምሥራቅ መዘዝ ያገናኘዉ ስብስብ በ1976 ካናዳን፥ በ1997 ሩሲያን ጨምሮ ስምንት ሆነ።ዘንድሮ ሰላሳሰባተኛ ጉባኤን አጠናቀቀ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በጉባኤዉ ላይ ለመካፈል ከዋሽንግተን ከመነሳታቸዉ በፊት ያደረጉት ንግግር-ዉይይት የዘንድሮዉም ጉባኤ ለዚያ ቡድን መመሥረት ምክንያት የሆነዉ የዚያ ሐብታም-ጉደኛ ምድር ማብቂያ የለሽ ጉድ-ሁነት እንደሚሆን አላከራከረም ነበር።አረብ፥ እስራኤል። መካከለኛዉ ምሥራቅ።

«የግጭቱ አብይ ጉዳይ ድርድር ሊደረግበት የሚገባ ሲሆን፥ የድርድሩ መሠረትም ግልፅ ነዉ።ተጨባጭ ፍልስጤም እና ደሕንነቷ የተጠበቀ እስራኤል።ዩናይትድ ስቴትስ፥-ድርድሩ ፍልስጤሞች ከእስራኤል፥ ከዮሮዳኖስ እና ከግብፅ ጋር ቋሚ ድንበር እንዲኖራቸዉ፥ እስራኤል ደግሞ ከፍልስጤሞች ጋር ቋሚ ወሰን እንዲኖራት በሚያደረግ የሁለት መንግሥታት ዉጤት ማሳረግ አለበት ብላ ታምናለች።ሁለቱ መንግሥታት አስተማማኝና እዉቅና ያለዉ ወሰን እንዲኖራቸዉ በጋራ በሚደርሱበት ስምምነት መሠረት የእስራኤልና የፍልስጤም ድንበር በ1967ቱ ወሰን ላይ የሚያርፍ ይሆናል።ፍልስጤሞች በሉላላዊና በቋሚ መንግሥት አማካይነት እራሳቸዉን የማስተዳደር፥ ሐብታቸዉን የመቆጣጠር መብት ሊኖራቸዉ ይገባል።»

የፕሬዚዳት ኦባማ ንግግር በተለይ የወደፊቱ የፍልስጤሞች ድንበር ከ1967ቱ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት በፊት በነበረዉ ወሰን ላይ መወሰን አለበት ማለታቸዉ የእስራኤሉን መንግሥት በማስከፋቱ የቡድን ስምንት ጉባኤተኞች ማብቂያ ያጣዉን የእስራኤል-ፍልስጤሞችን ግጭት-ቁርቁስ ጉባኤዉ አነሳ ለማሰኘት ያክል ከማዉሳት ባለፍ ብዙም ያሉት ነገር የለም።

አብይ ርዕሳቸዉ ግን ያን ስብስብ ለመፍጠር ሰበብ ከሆነዉ ከዚያ ምድር አዲስ ሁነት ብዙም አልዘለለም።ጉባኤተኞቹ መከካለኛዉ ምሥራቅ።በየገዢዎቹ ላይ ካመፀዉ የአረብ ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ ቃል-ገብተዋል።ቡድን ስምንት የሚያስናብራቸዉ አብዛኞቹ ሐገራት (ሁሉም ማለት ይቻላል) እስካለፈዉ ጥር ድረስ የቱኒስ-ካይሮ ገዢዎች ጥብቅ ወዳጆች፥ ተባባሪ፥ ረዳቶችም ነበሩ። የቱኒዚያና የግብፅ ሕዝብ በአደባባይ አመፅ የረጅም ጊዜ ገዢዎቹን ሲያስወግድ ትላልቁ አለም ትልቅ ጥቅሙን ባረጁ-ባፈጁት የቀድሞ ወዳጆቹ ሊለዉጥ አይፈቅድም።አልፈቀደም።

«ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም» በሚለዉ የረጅም ጊዜ በፖለቲካዊ መርሕ የሚመራዉ ሐያል ዓለም የተለወጠዉ የአረብ ፖለቲካ ዘላቂ ጥቅሙን በሚያስከብር መንገድ እንዲዘወር መከረ-ወሰነም። በዉሳኔዉ መሠረት ቡድኑ በመጪዎቹ ሁለት አመታት ዉስጥ ለቱኒዚያና ለግብፅ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ይረዳል።ዕርዳታዉ የጀርመንዋ መራሔተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ባስቸኳይ ቱኒዚያና ግብፅ መድረስ፥ ለታሰበለት አለማም መዋል አለበት።

«እንደሚመስለኝ እርዳታዉን ፈጥኖ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነዉ።ልንሰጥ የምንፈልገዉን ፈጥኖ የሚያደርስ አዲስ፥ ቀልጣፋ፥ እና ዉጤታማ መዋቅር ያለዉ ግብረ-ሐይል በአዉሮጳ ሕብረትም ዉስጥ ጭምር ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ።በተለይ ቱኒዚያ ርዳታዉን ፈጥኖ ለዉጤት የሚያበቃ ግልፅ የምጣኔ ሐብት እቅድ አላት።»

እንደ ሌሎቹ አለም አቀፍ፥ አካባቢያዊ፥ ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ ድርጅቶች፥ ማሕበራት ወይም ተቋማት ቋሚ ፅሕፈት ቤት፥ ርዕሠ-መንበንበር፥ መሪ፥ ሠራተኞችም የሉትም።ቡድን ስምንት።በሕዝብ ቁጥርም የቡድኑ አባል ሐገራት በሙሉ ያላቸዉ የሕዝብ ቁጥር ከአለም አስራ አራት በመቶዉን ብቻ ነዉ።ከዓለም ምጣኔ ሐብት ግን ከስልሳ-ከመቶ በላዩን ይቆጣጠራሉ።ከዓለም ጦር ሐይል ሰባ ሁለት ከመቶዉን ያዛሉ።

አለም ካላት የኑክሌር ቦምቦች ከ96 እስከ 99 ከመቶ የሚደርሰዉን ያጨቁት ከስምንቱ ሐገራት አራቱ ናቸዉ፥-ዩናይትድ ስቴትስ፥ ሩሲያ፥ ፈረንሳይና ብሪታንያ።በነገራችን ላይ የአዉቶሚክ ቦምብን ዘግናኝ እልቂት የቀመሰችዉ ብቸኛይቱ የዓለም ሐገርም የዚሁ ቡድን አባል ናት።ጃፓን።እና የዚያ ቡድን መሪዎች በጋራ አይደለም በተናጥል እንኳን የሚሉ-የሚያደርጉት የዓለምን ሁለንተናዊ እንዴትነት በያኝ ነዉ።

መሪዎቹ ቱኒዚያንና ግብፅን ለመርዳት መወሰናቸዉ ከዶቭሌ እንደተሰማ፥ አንደኛ፥- በልማዱ እንርዳ የሚልን የሚጠላ ባለመኖሩ፥ ሁለተኛ፥- እንርዳባዮቹ እንርዳ ብለዉ አይደለም እንምታ ቢሉም እነሱን መቃወም ከተመቺ ጋር አብሮ መጨፍለቅ በመሆኑ፥ የሚሉ-የሚያደርጉትን የሚቃወም የለም።የርዳታዉ ዜና ሲሰማም ተረጂዎች በደስታ ይቦርቃሉ ነበር የቡዝዎች እምነት።

የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ ያስወገደዉን ሕዝባዊ አብዮት ከመሩና ካስተባበሩት አንዷ ራጊያ ዑመር ግን የብዙዎቹን እምነት፥ ነባሩን ፖለቲካዊ ቀመርም አይቀበሉትም።ርዳታዉ ለማነዉ-ይጠቃሉ የሕግ ባለሙያዋ።

«እርዳታ ለመስጠት የተገባዉን ቃል የምንደግፈዉ እርዳታዉ ለተወሰኑ መስኮች የሚዉል መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነዉ።እንደ ሲቢል ማሕበረሰብ አባልና እንደ መብት ተሟጋች ይሕ ገንዘብ የሚዉልበትን መስክ አላዉቅም።እርዳታዉ ጦሩን ለመደገፍና የቀድሞዉ ሥርዓት አባላት ለተሰገሰጉበት ሐይል የሚዉል ከሆነ ገንዘቡን አንፈልገዉም።የዚሕን አብዮት መርሕና አላማ የሚቃወሙ የቀድሞዉ ሥርዓት ቅሪቶች አሁንም አሉ።ገንዘቡ ይሕን ያረጀ ሥርዓት ለመደገፍ እንደማይዉል ተስፋ አደርጋለሁ።»

ከ1990ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ የቡድን ስምንት ጉባኤ በተደረገ ቁጥር ድሕነትን፥ ረሐብ፥ በሽታን ለማስወገድ ለሚደረገዉ ጥረት በቢሊዮነ-ቢሊዮናት የሚቆጠር ዶላር ለመስጠት ጉባኤተኞች ቃል-እንደገቡ፥ የገቡትን ቃል ገቢር ሳያደርጉ ሲቀሩ፥ በሌላ ቃል እንዳደሱ ነበር።ዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደርን የማያከብሩ መንግሥታትን እንደማይረዱም በተደጋጋሚ ሲያስታዉቁ ነበር።
በአብዛኛዉ ለአፍሪቃ በጥቂቱ ለእስያ ሕዝብ የሚገባዉ ቃል-ተስፋ እስካሁን ከ«እንቁልልጮሽ» ባለፍ ብዙም ገቢር አልሆነም።አሁን ለቱኒዚያና ለግብፅ ሕዝብ የተገባዉ ቃል-ገቢራዊነትም ወደፊት የሚታይ ነዉ የሚሆነዉ።የደሐይቱ አፍሪቃ ጉዳይ ግን ዘንድሮ ለጎላ ርዕስነት እንኳን አልበቃም።

ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ፥ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ ባለፈዉ ባለፈዉ መጋቢት ሊቢያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በድል ሳያጠናቅቁ በየአመቱ የሚንከባለለዉን ድሐ-ሐገራትን የመርዳት ርዕሥ-እንደ ትልቅ ጉዳይ የሚያነሱበት ምክንያት በርግጥ አልነበራቸዉም።

እንደ ትልቅ ርዕስ ማንሳት ቀርቶ ለድሆቹ ሐገራት ሕዝብ የሚቆረቆሩ ወገኖች በየጊዜዉ የሚያሰሙትን ሰልፍና ተቃዉሞ ላለመስማት የጉባኤቸዉን ስፍራ በአስራ-ሁለት ሺሕ ሠራዊት አሳጥረዉት ነበር።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ለማስወገድ የተከፈተዉ ወታደራዊ፥ ፖለቲካዊ፥ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ደግሞ ፕሬዝዳት ኦባማ እንዳሉት በቅርቡ በድል ይጠናቀቃል።

«የሊቢያዉ ዘመቻችን ጥሩ ዉጤት ማምጣቱ አግባብቶናል።ይሁንና ቃዛፊ ሊቢያ ሆነዉ ጦራቸዉን በሊቢያ ሕዝብ ላይ እስካዘመቱ ድረስ ሰላማዊ ሰዎች ከአደጋ እንዲጠበቁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ገቢራዊ ሊሆን አይችልም።እና የጀመርነዉን ለመጨረሽ ቆርጠናል።»

26.05.2011 DW-TV JOURNAL WIRTSCHAFT ZAHL DES TAGES BIP G8 eng
የቡድን 8 ጠቅላላ ምርት
Flash-Galerie G8-Gipfel
ምስል AP

ጉባኤተኞች ተቃዋሚዎቹን በሚያገድል-በሚያስረዉ በሶሪያ መንግሥት ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ተገቢነት አድንቀዉ፥ ደማስቆዎችን በድጋሚ ሲያወግዙ አርብ፥ የየመንዋ ርዕሠ-ከተማ ሰነዓ በደም እንደጨቀየች ነበር።ፕሬዝዳት ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ እንደ ትሪፖሊ፥ እንደ ደማስቆ ገዢዎች ሕዝባቸዉን እያስገደሉ፥ ለሸምጋዮች እንቢኝ እንዳሉ ቤተ-መንግሥታቸዉ ዉስጥ እንደተቀመጡ ነዉ። ለጉባኤተኞች ግን ሳሌሕ እንደ አል-ቃዛፊ እንደ አል-አሰድ የሚታዩ አይደሉም።ዓለምም ሕዝብ በአደባባይ ሠልፍ አምባገኖች በተወገዱበት ማግሥትም እንደ ወትሮዋ እንደተዛነቀች፥ በተፃራሪ አቋም እንደተዘወረች ትቀጥላለች።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬዬ ።ገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ