1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጥቂት ገንዘብ ኤሌክትሪክ ለአፍሪቃ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9 2006

በአፍሪቃ እስካሁን 3000 ቤቶች ሌት ብርኃን እንዲያገኙ አስችሏል። ኤሌክትሪክ ፈፅሞ ባልነበረበት ቦታ የኤሌክትሪክ ኃይል ይዘን እንመጣለን ይላል። ሞቢሶል የተሰኘው ከፀሀይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሣሪያ የሚፈበርከው ድርጅት።

https://p.dw.com/p/1BjCu
ምስል Mobisol

ሞቢሶል ድርጅት በበርሊን ከተማ ውስጥ ከአንድ ዕድሜ-ጠገብ ፋብሪካ ሁለት ሕንፃዎች ባሻገር አራተኛ ፎቅ ላይ ይገኛል። የመገጣጠሚያ ክፍሉ አነስተኛ ነው። ሠራተኞቹ ኮምፒውተሮቻቸው ላይ በሥራ ተጠምደዋል። ግድግዳው በአራቱም አቅጣጫ የተለያዩ ሰዎች አፍሪቃ ውስጥ ሆነው የተነሱት ፎቶግራፎችን ይዟል። ፎቶዎቹ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው አፍሪቃውያን ይታያሉ። በሌላኛው ፎቶ ላይ ደግሞ የኃይል ማመንጫ መሳሪያውን የቆርቆሮ ጣሪያዎች ላይ የሚገጥሙ ሰዎች ይታያሉ። በሌላኛው ግድግዳ ላይ፤ ቴሌቪዥን የሚመለከቱ፣ ራዲዮ የሚያዳምጡ አለያም ላፕቶፕ የያዙ ሰዎች አሉ። የሞቢሶል ድርጅት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ከሆኑ ሠራተኞች መካከል አንዱ የሆኑት ቶማ ዲቮው።

የሞቢሶል ድርጅት ባልደረባ ቶማ ዲቮው
የሞቢሶል ድርጅት ባልደረባ ቶማ ዲቮውምስል privat

«እዚህ 30 ሰዎች ነው ያለነው። ከቴክኒክ አንስቶ መሣሪያውን እስከማንቀሳቀስ የሚደርስ ምሉዕ አገልግሎት እንሰጣለን።»

መሣሪያው የሚገጠምላቸው የአፍሪቃ ሃገራት ደንበኞች በቋንቋቸው የስልክ አገልግሎት ያገኛሉ። የኃይል ማመንጫ መሣሪያው ችግር ከገጠመው በ72 ሠዓታት ውስጥ በድጋሚ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ዋስትና ይሰጣቸዋል። አንድ ደንበኛ የኃይል ማመንጫ መሣሪያውን ሲገዛ ክፍያውን በ3 ዓመታት ውስጥ ማጠናቀቅ ይችላል። ከእዚያም መሣሪያውን የግሉ ያደርገዋል። እንደ ኃይል ማመንጫ መሣሪያው መጠን ዋጋው ከሰባት እስከ 35 ዩሮ በወር ያስከፍላል።

ከፀሀይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው መሣሪያ
ከፀሀይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው መሣሪያምስል Mobisol

«አገልግሎቱን እየሰጠንባቸው በሚገኙት ሃገራት ማለትም፤ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ በሄድንባቸው አካባቢዎች ነዋሪው 85 በመቶ የኃይል አቅርቦት የለውም። ኃይል እንኳን ቢኖር ከጄነሬተር የሚገኝ ነው። እኛ ጣራ ላይ የሚቀመጥ ከፀሐይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ መሣሪያ ነው የፈበረክነው። አንድ ባትሪ ባለው፣ በርካታ የጀርመን መሐንዲሶች በተጠበቡበት በእዚህ መሣሪያ በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እቤታቸው ኃይል ማመንጨት ችለዋል።»

በፀሐይ ብርሃን የምትሰራው አነስተኛዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ30 ዋት ኃይል ማመንጨት ትችላለች። ሦስት አምፑሎችን የማብራት፣ አንድ ሬዲዮ የማጫወትና ሞባይል ስልክ ባትሪ ሲያልቅ ኃይል የመሙላት አቅም አላት። ትልቁ ማመንጫ ደግሞ እስከ 200 ዋት ድረስ ያመነጫል። አንድ የማቀዝቀዣ መሣሪያ አገልግሎት ላይ እንዲውል፣ በርካታ ክፍሎች እንዲያበሩ፣ የሙዚቃ ማጫወቻና ቴሌቪዥን ያለምንም ችግር እንዲሰሩ ኃይል ማመንጨት ይችላል።

ከፀሀይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው መሣሪያ ጣራ ላይ
ከፀሀይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው መሣሪያ ጣራ ላይምስል Mobisol

ሞቢሶል የኃይል ማመንጫ መሣሪያውን ለመፈብረክ ሦስት መሐንዲሶቹ ሀሳቡን ከፀነሱ ገና ሦስት ዓመትም አላለፋቸው። ድርጅቱ ታንዛኒያና ኬንያ ውስጥ የሙከራ ስራ ከጀመረም ሁለት ዓመቱ ነው። ሙሉ በሙሉ ሥራ በጀመረ በአንድ ዓመት ውስጥ ግን ደምበኞቹ 3000 ደርሰዋል።

እጎአ በ2020 የአፍሪቃ ዋነኛ የኃይል አቅራቢ የመሆን ዐሳብ አለን ሲሉ ቶማ ዱቮ ገልጠዋል። ድርጅታቸው እስከ 2017 ድረስ ከአጠቃላዩ የሩዋንዳ ነዋሪ 70 በመቶው የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ከሩዋንዳ መንግሥት ጋ እየተደራደረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የሩዋንዳ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በአሁኑ ወቅት ድርሻው 17 በመቶ ብቻ ነው።

መቀመጫውን በርሊን ላደረገው ሞቢሶል አሁን የጥድፊያ ወቅት ነው። የዓለም ባንክ በበኩሉ ሞቢሶል በርካታ የኃይል ማመንጫ መሣሪያዎችን በአፋጣኝ ማምረት ይችል እንደሆን ጠይቋል። እናም በእዚህ ዓመት የሞቢሶል ደምበኞች 10,000 ይደርሳሉ ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ