1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግብጽ መንግስት አንጻር የቀጠለው ተቃውሞ

እሑድ፣ ጥር 22 2003

በአሌግዛንድርያ ፡ በካይሮ እና በኢዝማየልያ ከተሞች በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ መቶ ሀምሳ ሰዎች እንደተገደሉ እና በርካቶችም እንደቆሰሉ ተዘገቦዋል። ፖሊስ በካይሮ በሀገር አስተዳደሩ አካባቢ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን በጎማ ጥይቶች እና በሚያስለቅስ ጢስ ተጠቅሞዋል።

https://p.dw.com/p/Qwip
ምስል AP

የጦር ኃይሉ ግን ጣልቃ እንዳልገባ ነው የተገለጸው። መንግስት የሰዓት እላፊ ቢያውጅም፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ግብጻውያን በአደባባይ በመቆየት ተቃውሞአቸውን እንደቀጠሉ ነው።
የግብጽ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ በመንግስታቸው አንጻር የቀጠለውን ተቃውሞ ለማብረድ በማሰብ ካቢኔአቸውን አሰናበቱ፤ በሀገሪቱም የተሀድሶ ለውጥ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ስልጣን ከያዙ ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ አሁን ለመጀመርያ ጊዜ ምክትል ፕሬዚደንትም ሾመዋል። የምክትል ፕሬዚደንትነቱን ስልጣን የተረከቡት ካለፉት ሁለት አሰርተ ዓመታት ወዲህ የስለላ ድርጅቱ ኃላፊ የሆኑት ኦማር ሱሌይማን ናቸው።
የግብጽ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የሰሞኑ ዓይነት ትልቅ የህዝብ ተቃውሞ ተነስቶባቸው አያውቅም። ልክ በሌላዋ ዐረባዊት ሀገር ቱኒዝያ እንደታየው፡ ተቃውሞው የተነቃቃው በኢንተርኔት ታጋዮቹ ወጣት የሀገሪቱ ዜጎች ነው። በግብጽ የቀጠለው የተቃውሞ ርምጃ የሀገሪቱ መንግስት ሊወድቅ ተቃርቦ ይሆን የሚለውን ጥያቄ አስነስቶዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ የተጀመረው ትዊተር እና ፌስቡክን በመሳሰሉ የኢንተርኔት ማህበራዊ የመገናኛ መረቦች ላይ ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ ከቀረበ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ግብጻውያን አደባባይ ወጥተዋል።

አርያም ተክሌ

መስፍን መኮንን