1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ዓለም አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ተሸላሚ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 13 2009

የኮንጎ ተወላጁ ደራሲና የአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ መምሕር ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ ስድስት የዓለም ቋንቋዎችን አጣርቶ ይናገራል። ኑሮዉና ሥራዉ ደግሞ ከሁለት አህጉሮች ጋር ቀቆራኝቶታል። የትዉልድ ሃገሩ ከሚገኝበት ከአፍሪቃ እና አሁን ከሚኖርበት ከአዉሮጳዊትዋ ኦስትርያ  ከተማ ግራዝ ጋር።

https://p.dw.com/p/2gu49
Frankreich Fiston Mwanza Mujila in Paris
ምስል picture-alliance/Leemage/F. Gattoni

በጀርመን ዓለም አቀፍ የስነጽሑፍ ተሸላሚ

የኮንጎ ተወላጁ ደራሲና የአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ መምሕር ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ ስድስት የዓለም ቋንቋዎችን አጣርቶ ይናገራል። ኑሮዉና ሥራዉ ደግሞ ከሁለት አህጉሮች ጋር ቀቆራኝቶታል። የትዉልድ ሃገሩ ከሚገኝበት ከአፍሪቃ እና አሁን ከሚኖርበት ከአዉሮጳዊትዋ ኦስትርያ  ከተማ ግራዝ ጋር። በአለፈዉ ሰሞን በጀርመን የዓለም ቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማትን ስላገኘዉ የአፍሪቃ የሥነ-ጽሑፍ አስተማሪ እና ደራሲ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ መሰናዶ ይዘናል።

«Tram 83» ለተሰኘዉ ልብ-ወለድ መጽሐፉ ባለፈዉ ሰምወን በርሊን ላይ የዓለም አቀፉን የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት ያገኘዉ የኮንጎ ተወላጅ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ የቋንቋ ተሰጥኦ እንዳለዉ ተነግሮለታል። ቋንቋ ለኔ ሙዚቃ ነዉ ሲልም ነዉ የሚገልፀዉ። የዶቼ ቬለዋ ሳቢነ ኪስልባህ ኮንጎዋዊዉን ደራሲ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላን ያገኘችዉ በሚኖርበት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአፍሪቃ ሥነ ጽሑፍ ትምህርትን በሚሰጥበት በኦስትርያዋ አነስተና ግራስ ከተማ ነዉ። «Tram 83» ማለት ባቡር ቁጥር 83 የተሰኘዉና ኮንጎ ከቅኝ ግዛት በኋላ ቅኝ ግዛት ዉስጥ እንደምትገኝ የሚተርከብት ይህ መጽሐፍ ከፈረንሳይና ቋንቋ ወደ ጀርመንኛም በተርጎሙ ለተርጉዋሚዎቹ ሁለት ጀርመናዉያንም ሽልማቱ መሰጠቱ ነዉ የተነገረዉ። የ46 ዓመቱ ኮንጉዋዊዉ ደራሲ የደረሰዉ በልብወለድ መጽሐፉ የሚተርከዉዉ ኮንጎ ከቅኝ ግዛት በኋላ ስፍር ቁጥር የተፈጥሮ ማዕድን በሚዛቅበት በቦታ በማሳየቱ « ይህ ሽልማት እንደተበረከተለት ለሽልማት የመረጡት ዳኞች በሽልማት አሰጣጡ ሥነ-ስርዓት ላይ ተናግረዋል። በዚህም የደራሲዉ 20 ሺህ ይሮ ለተርጓሚዎቹ ሁለት ሴቶች ለእያንዳንዳቸዉ 15 ሺህ ይሮ እንደተሰጣቸዉ « በርሊን ሃዉስ ዴር ኩልቱርን » የተሰኘዉ በርሊን የሚገኘዉ ዓለም አቀፉ ሸላሚ የባህል ተቋም አስታዉቋል።

ኮንጎዋዊዉ ደራሲ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ  ባቡር ቁጥር 83፤ Tram 83» የተሰኘዉ ድርሰት እና ዓለም አቀፍ ሽልማትን ያገኘበት መጽሐፉ በኦስትርያ የሚገኙ አሳታሚ ድርጅቶች አናትምም ማለታቸዉ እና ደራሲዎ ተቸግሮ እንደነበር ተሰምቶአል። በርግጥ ድርሰቱ አፍሪቃዊ በመሆኑ ይሆን እንዴ አሳታሚ ድርጅቶች ላለማተም የወሰኑት ለተባለዉ ጥያቄ  ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ በቀጥታ አናትምም እንዳላሉ ይናገራል።  

« የልብ ወለድ መጽሐፍ አሳታሚ ድርጅቶች በቀጥታ መጽሐፉን አናትምም ብለዉ መልስ አልሰጡም። ድርሰቱ በጣም አፍሪቃዊ ይዘት አፍሪቃዊ ቃና ያለዉ ነዉ፤ ሲሉ መግለፃቸዉን የብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል። የምኖረዉ ኦስትርያ ግራዝ የሚባል ከተማ ዉስጥ ነዉ። የምጽፈዉ ግን በፈረንሳይኛ ነዉ። የጀርመንና ቋንቋ በሚናገሩ ሃገራት ዉስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋን የሚያትም አሳታሚ ድርጅት የለም ማለት ይቻላል። ግራዝ ዉስጥ ሆኖ ታድያ  ፓሪስ ከሚገኝ የመጽሐፍ አሳታሚ ድርጅት ጋር ተነጋግሮ መጽሐፍን ለሕትመት ማብቃት ቀላል አይሆንም ብዙ ጊዜን ይወስዳል።» 

Buchcover Tram 83 von Fiston Mwanza Mujila
ምስል Paul Zsolnay Verlag

በድርሰቱ ዉስጥ ሉሙባሺ የተባለች የኮንጎ ከተማን ይጠቀሳል። ደራሲዉ ምናልባት ይህች ከተማ ከኦስትርያዋ ስትሪያ አመሳስለዉ ይሆን?

 « ጽሑፊን የጀመርኩት ጀርመን ሳለሁ ነዉ። ሃይንሪሽ ቦል ከተሰኘ ተቋም ባገኘሁት የነጻ ትምህርት እድል ለአንድ ዓመት በኮለኝ እና በአኸን ከተማ መካከል በምትገኘዉ ላንገንብሮይሽ በተሰኘች ትንሽ ከተማ ኖርያለሁ። እዝያ ሳለሁ ነዉ። የድርሰቴን መሰረት የጀመርኩት፤ ከዝያ እዚህ አሁን ባለሁበት በኦስትርያዋ ግራዝ ከተማ ዉስጥ ጽፊ ጨረስኩ። በአንድ ጊዜ ሦስት፤ አምስት ምዕራፎችን እጽፋለሁ።  ስለዚህም እኔ አንድ ሰፊ ልብ ወለድ ከመጻፍ ይልቅ፤ አነስ አነስ ያሉ ትያትሮችን ግጥሞችን መነባንቦችን መጻፉን እመርጣለሁ። እንዲህ ያለን አጠር ያለ ጽሑፍን ስጽፍ ነዉ ፍርያማ የምሆነዉ። »  

ኦስትርያ ከተማ ግራዝ ላይ እየተኖረ ስለአፍሪቃዊ ከተማ ጉዳይ መጻፍ አይከብድ ይሆን? ምናልባት በአዉሮጳና  በአፍሪቃዊትዋ ከተማ ያለዉ ርቀት ሃሳብን ለማፍለቅ ረድቶስ ይሆን?  ኮንጎ ሲኖር ሳይታይ ሳይያዝ የሚያመልጠ  ነገር ብዙ ነዉ ሲል ደራሲዉ ይቀጥላል።

« ኮንጎ ዉስጥ ስትኖር ሁሉ ነገር እጅግ በፍጥነት ነዉ ፍዉ ብሎ የሚያልፈዉ። እንዲያ ሲሆን ታድያ ሳታየዉ የሚያልፍህና ሳትደርስበት የሚያመልጥህም ነገር በዝያዉ መጠን እጅግ ብዙ ነዉ። ስለ ኮንጎ ጉዳይ ለመጻፍ በኩንጎ ዉስጥ ሳለህ ሳይሆን በዉጭ ሃገር ሆኖ ይቀላል። ማለት አሁን እኔ እንዳደረኩት በፈረንሳይ አልያም እዚህ በኦስትርያ እየኖርክ ስጽፍ ቀለል ይለኛል። ከዉጭ መጻፍ የሚቀለዉ በርቀት ማየት ስለሚቻል፤ ጊዜም ስለሚኖር ነዉ። በዉጭ ሃገር ስኖር ድርሰቴን ስጽፍ ታሪኩን ከየትኛዉ ወገን በኩል ቁጭ ብዬ በየትኛዉ መነጽር ኮንጎን አይቼ ስለኮንጎ እንደምጽፍ በግልፅ በምናቤ ማየት እችላለሁ። ይህን ስል ልክ እንደ አዉሮጳዊ በአዉሮጳዊ መንጽር እያየሁ አልያም ልክ እንደ ኮንጎ ዜጋ ወይም ደግሞ በፈረንሳዊ ወይም ደግሞ በቤልጂግ ዉስጥ እንደሚኖር ጸሐፊ ምናብ ማለቴ ነዉ። የኮንጎ ዜጋ ሆነህ በቤልጂየም ስትኖር ስለኮንጎ ስትፅፍ  በኮንጎ ዉስጥ ሆኖ እንደሚጽፍ ደራሲ አይደለም የድርሰትህ ይዘት የሚሆነዉ ። በኦስትርያ ዉስጥ ሆነህ ስለ ኮንጎ ስትጽፍ የኮንጎ የቅኝ ግዛት ታሪክ በቀጥታ ስለማይሰማህ የድርሰትህ ይዘት ትንሽ ለየት ማለቱ አይቀርም፤ ምክንያቱም ኮንጎ በኦስትርያ ቅኝ ስላልነበረች ነዉ። ይህ የተለያየ የምናብ መነጽር የትዉልድ ሃገሪን ብሎም አፍሪቃን በአዲስ  እንዳይና በአዲስ አንድጽፍ ይረዳኛል።»

የዶይቼ ቬለዋ ሳቢነ ኪስልባህ ለኮንጎዋዊዉ  ደራሲ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ ቃለ-መጠይቅ ባደረገችለት ወቅት በኦስትርያ ስኖር ስለትዉልድ ሃገሩ ኮንጎ ገልፆ ለመፃፍ በአዕምሮዉ ብዥ ያለ ሃሳብ እንዳለዉ ተናግሮ ነበር። ምክንያቱም ኦስትርያ ተቀምጦ በምናቡ ኮንጎን እንደአዉሮጳዊ አልያም እንደ ኮንጎ ተወላጅ በተለያየ መነጽር ስለሚያይ  እንደሆነ ገልጾ ነበር። 

 « አዎ አሁን አሁን ኦስትርያዊ ደራሲ ነኝ ብዬ እራሴን ማስተዋወቅ እችላለሁ። ግራዝ ሁለተኛ የትዉልድ ከተማዬ ናት። ይህ ማለት አፍሪቃን እንደ አዉሮጳዊም አልያም እንደ አፍሪቃዊም በምናቤ ማየት እችላለሁ። ሁለት የተለያዩ የምናብ መንገዶች ናቸዉ። አንደኛዉ እንደ አፍሪቃዊ ተስፈኛ ሁለተኛዉ ድፍን ያለ አፍሪቃዊ ምናብ ማለት ነዉ። አፍሪቃ ማለት ተዝቆ የማያልቅ የተለያየ ነገርን ነገርን ያቀፈች ሰፊ የሆነች አህጉር ማለት ናት። በአዉሮጳ ዉስጥ ሆኖ ስለ አፍሪቃ ሲወራ ምናልባት የአዕምሮ ሕመም ሊያስይዝ ይችላል። ለዚህም ነዉ ምናልባት ይህን ምናብ ለማስቀየርያ እና ስለአፍሪቃ ለመፃፍ አዲስ መነጽር ያስፈልጋል ያልኩት። ስለአፍሪቃ ለመጻፍ አፍሪቃን በቅርበት ማወቅ ያስፈልጋል፤ ለዚህም በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ኮንጎ እየሄድኩ ሃገሪን እጎበኛለሁ።» ኮንጎ ማለት ለአንተ ምንድ ናት?

«ኮንጎ ለኔ እናቴም አባቴም ቤተሰቤን ናት። ጥሩም መጥፎም ያየሁባት የማይባት ሃገሪ ናት። ከአለፉት 20 ዓመታት ወዲህ በምስራቃዊዉ የሃገሪቱ ክፍል በሚገኘዉ የተፈጥሮ ጥሪ ኃብት የተነሳ የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቶአል። እንዲም ሆኖ እዝያ ቦታ ላይ የእርስ በርስ ጦርነት ቢታይም አካባቢዉ ላይ የሚኖረዉ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ቀና፤ ተስፈኛ ነዉ። ኮንጎ ከዓመታትት ጀምሮ የስልጣን መንበሩን ከተቆናጠጠዉ አምባገነን ጋር እየታገለች ነዉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ተስፋችንን አላጣንም። ኮንጎ ለኔ ምንግዜም የምወዳት ሃገሪ ናት። ሃገሪን እና ቤተሰቦቼን ሁልግዜም በልቤ ይዤ በጀርባዩ አዝዬ ነዉ ሁሉ ቦታ የምዞረዉ።»

Österreich Kongolesische Autor Fiston Mwanza Mujila in Graz
ምስል DW/S. Kieselbach

ኮንጎዋዊዉ  ደራሲ ፊስቶን ሙዋንዛ ሙጂላ ባቡር ቁጥር 83 ሲል የሰየመዉ ልብወለድ መጽሐፍ ለሱ ልክ እንደ ጃዝ ሙዚቃ መሆኑን ነዉ የሚናገረዉ። በአሁኑ ወቅት በአዉሮጳ ስለ አፍሪቃ የስደተኞች ችግር በተደጋጋሚ የሚነገርበት እና አፍሪቃ ዉስጥ ስለሚታየዉ ችግር በተደጋጋሚ የሚነሳበት  ወቅት ነዉ። ደራሲዉ ይህን  በተደጋጋሚ የሚሰማ አባባልን  በከፊል በድርሰቱ ጠቅሶታል። ስለአፍሪቃ በተደጋጋሚ የሚነገረዉን ነገር ተከትሎ አፍሪቃ ምናባዊ ነዉ ሲልም ነዉ የገለፀዉ።  

 «አፍሪቃ ምናባዊ ነዉ። አፍሪቃ የሚባል ነገር የለም። ይህ የአዉሮጳዉያን ፍልስፍና ነዉ። ስለ አፍሪቃ የሚጻፈዉ ነገር ሁሉ አሰቃቂ አይነት ነገር ነዉ። ስለአፍሪቃ ለመጻፍ አፍሪቃ መኖር እና ከዝያ በመጀመርያ አፍሪቃ ማነዉ አፍሪቃ ምንድን ነዉ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ስለአፍሪቃ ታሪክ መጠየቅ ይኖርበታል፤ በአፍሪቃ ስላለዉ አመለካከት ብሎም ስለአዉሮጳ አመለካከት ሁሉ መጠየቅ ይኖርበታል። አዉሮጳ ዉስጥ ስለአፍሪቃ የምንሰማዉ በመገናኛ ብዙኃን ነዉ። ብዙኃን መገናኛዎች የሚዘግቡት ደግሞ በአፍሪቃ የተከሰተዉን አዲሱን የተጋነነዉን ወይም ትልቅ የተባለዉን ወቅታዊዉን ዜና ነዉ። እንደኔ እምነት አዉሮጳ ዉስጥ ስለአፍሪቃ ያለዉ እምነት እና ግንዛቤ እጅግ የተሳሳተ ነዉ።»    

በዚህም ይላል ደራሲዉና የአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ መምህሩ ሙዋንዛ ሙጂላ በሚኖርበት በኦስትርያ ስለአፍሪቃ ምንነት ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ይናገራል።

«የማስተምረዉ ስለአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ ነዉ ። ስለአፍሪቃ ሳስተምር ከተማሪዎቼ ጋር ስለአፍሪቃ አወራለሁ እወያያለሁ። አፍሪቃ ጦርነት ረሃብና ችግር ብቻ እንዳልሆነችም እናገራለሁ። ስለ አፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ ስለ አፍሪቃ ኪነ-ጥበብ እና ስለአፍሪቃዉያን ማንነትና ምንነት ለማስተማር መንገዱ ይህ ዘዴ ብቻ ይመስለኛል እጅግ ጡሩ መንገድ ነዉ። ምክንያቱም በብዙኃን መገናኛ ስለአፍሪቃ የሚነገረዉ ስለአፍሪቃ የሚሳለዉ ስዕል ብሎም ስለአፍሪቃ የሚያሰጠዉ ግንዛቤ ሌላ ይዘት አልያም ሌላ አይነት አቅጣጫን የያዘ ነዉ።»

በአፍሪቃ የነበረዉን የቅኝ ግዛትን ታሪክ ተከትሎ አዉሮጳ ከአፍሪቃ ጋር ከመቶ ዓመት የዘለቀ ግንኙነት አለ ። በአሁኑ ወቅት ይህ ቁርኝት ከኮንጎ ምን ያህል ይታይ ይሆን? ለሚለዉ ሙዋንዛ ሙጂላ በመቀጠል  

 «አፍሪቃ 54 አልያም 55 ሃገሮችን ያቀፈች አህጉር  ናት። በአፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ ሃገራት መካከል ስምንት ሃገራት ብቻ ናቸዉ የፖለቲካ ሁኔታቸዉ እጅግ የተበላሸ ሆኖ የምናገኘዉ። ለምሳሌ ሶማልያን ኮንጎን ደቡብ ሱዳንን መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ደቡብ አፍሪቃዊ ወደ አዉሮጳ ተሰዶ መኖርን አይሻም። አንጎላዊም ቢሆን፤ ከሞዛንቢክ፤ ከቦትስዋና ከሴኔጋል እና ከቱኒዚያ የመጣም ዜጋ መሰደድን የሚሻ አይደለም። አዉሮጳ ዉስጥ የሚታመነዉ ግን ሁሉ አፍሪቃዉያን ወደ አዉሮጳ ተሰደዉ መኖርን ይሻሉ የሚለዉን ነዉ። ችግር በሚታይባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት የሚኖሩ አፍሪቃዉያንም ቢሆኑ ወደ አዉሮጳ መምጣት የለባቸዉም። እና አሁን የሚያስፈልገን አፍሪቃዊ ችግር መፍቻን ዘዴን መቀየስ ነዉ»  

እንድያም ሆኖ ይላል ደራሲዉ ሙዋንዛ ሙጂላ በመቀጠል  ኮንጎ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላም ዛሬም ቅኝ ግዛት ዉስጥ ናት። 

Österreich Kongolesische Autor Fiston Mwanza Mujila in Graz
ምስል DW/S. Kieselbach

«የአፍሪቃን ችግር ለመፍታት አዉሮጳ ዉስጥ ዘዴ መግኘት አለበት ተብሎ ይታመናል። ነገር ግን ችግሩን መፍቻዉ ከሁሉ በቅድምያ መምጣት ያለበት ከራስዋ ከአፍሪቃ ነዉ። ኮንጎ ከቅኝ ግዛት ተላቃ ዳግም ቅኝ ግዛት ዉስጥ ተዘፍቃ የምገኝ ሃገር  ናት። 70 አልያም 80 በመቶ የሆነዉ በዓለማችን ልዩ የሆነዉ ማዕድን በኩንጎ ዉስጥ ነዉ የሚገኘዉ ። ይህ ማዕድን  ለተንቀሳቃሽ ማለት ለሞባይል ስልክ መስርያ የሚያገለግል ማዕድን ነዉ። በዚህም ምክንያት ይህን ማዕድን ለመቀራመት ሃገሪቱን በቁጥጥሩ አድርጎ ማስተዳደር የሚፈልገዉ ወገን እጅግ ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ኮንጎ ዉስጥ በማዕድንኑ ቦታ ላይ ፈረንሳይ ትልቅ ሚና አላት። ቤልጂየም እና ዩናይትድ ስቴትስም እንዲሁ ሌሎቹ የኮንጎ ተቀራማቾች ናቸዉ። በዚህም ምክንያት ኮንጎ የፈለገዉ መቶ የሚዘልባት ልክ የሕጻናት መጫወቻ ሜዳ ዓይነት ሆናለች። ኮንጎ በራስዋ ቆማ ራስዋን የምትመራ ሃገር አይደለችም፤ እስካሁን የምትገኘዉ ቅኝ ግዛት ዉስጥ ነዉ።»   

ኮንግዋዊዉ ደራሲ ሥለ አፍሪቃን ሥነ-ጽሑፍ በማስተማሩ የአፍሪቃ አምባሳደር ነህ ማለት ይቻላልን?«የማስተምረዉ ሥነ-ጽሑፍን ነዉ። ሥነ-ጽሑፍ ደግሞ ይህ ነዉ የሚባል የሚገለጽ ነገር ነዉ። ልክ እንደ ደራሲ ስራዬ  የቃላት ተምኔትን ፤ ምኞትን እና ፈጠራን ይዤ ስለአፍሪቃ አንድ ስዕልን አንድ ነገርን ማስጨበጥ ነዉ። ልክ እንደ አንድ የአፍሪቃ የሥነ-ጽሑፍ አስተማሪ ስለልብ ወለድ ምንነት ከተማሪዎቼ ጋር እወያያለሁ፤ ፈጠራዩንም አሳያለሁ። ልክ አንደ አንድ ደራሴ ስለአፍሪቃ የተለያዩ ነገሮች መጻፍ እችላለሁ። ልክ እንደ አንድ የሥነ-ጽሑፍ አስተማሪ ግን እዉነታዉን ቁልጭ አድርጌ አሳያለሁ። »

በኮንጎ ዉስጥ በሚገኝ አንድ ማዕድን ማዉጫ ቦታ የሚታየዉን የተለያየ ጉዳይ "Tram 83" በተሰኘዉ ልብወልድ መጽሐፉ ያስቀመጠዉ ኮንጎዋዊዉ ደራሲ በተለይ አካባቢዉ ላይ ራሳቸዉን እየሸጡ ስለሚተዳደሩ ሴቶች ጉዳይ በመጻፉ ፀረ ሴት የሚል የተለያየ ትችትም ደርሶበታል። ስለዚህስ ትችት ምን አስተያየት ይኖረዉ ይሆን?

« በእኔ ሥነ-ጽሑፍ ዉስጥ ማለትም በመጽሐፊ ዉስጥ የሚገኙት ገፀ-ባህርያት ማለትም ወንዶቹም ሴቶቹም  ጥሩ ዓይነት እይታ የላቸዉም። ስለሴት መጥፎ አይነት ነገር ሲሰማ ሲነገር ግን የሰዉ አመለካከት ትንሽ ቁጣን ያዘለ ሆኖ ይታያል። በምንኖርበት ዓለም በሴቶች ላይ ስለሚደርሰዉ ጥላቻ መወራት አለበት የሚል እምነት አለኝ። በምጽፈዉ ልብወለድ ትረካ ዉስጥም የሚታዩት ገፀ-ባሕራያት በኮንጎ በአንድ የማዕድን ማዉጫ ቦታ ላይ የሚሆነዉን ነገር የሚገልጽ ነዉ። ታሪኩ በዚህ ማዕድን ማዉጫ ቦታ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለሚፈፀምባቸዉ በሴተኛ አዳሪነት በሚተዳደሩ ሴቶች ላይ ነዉ። ስለዚህም የኔ ልብ ወለድ የእነዚህን ሰዎች የእለት ሕይወት የሚያሳይ ነዉ ። ልክ እንደ አንድ ደራሲ ይህን ገሃድ ለማሳየት ስለእነዚህ  ሰዎች ኑሮና ሕይወት መጻፍ ነበረብኝ።»

Österreich Kongolesische Autor Fiston Mwanza Mujila in Graz
ምስል DW/S. Kieselbach

ፈረንሳይኛና ጀርመንናን ጨምሮ ስድስት ቋንቋዎችን የሚናገረዉ ኮንግዋዊዉ ደራሲ ደራሲዉ ሙዋንዛ ሙጂላ ቋንቋን ለሱ።  

 « አንድ ቋንቋ ለኔ ልክ እንደ አንድ ማሽን ነዉ። ይህን ማሽን እገነባለሁ። ቋንቋ ለኔ ልክ እንደ አንድ ቦክስ ግጥምያ ነዉ።  እኔ ከቃላት ጋር የምገጥም ቦክሰኛ ነኝ። ቋንቋ ለኔ እንደ ሙዚቃም ነዉ ። ሳክስፎን የሙዚቃ መሳርያን የመጫወት ምኞት ነበረኝ ፤ ነገር ግን ባደኩበት የኮንጎ ከተማ ዉስጥ የሳክስፎን ሙዚቃ መሳር ያ አስተማሪ አልነበረም። ስለዚህ ለኔ ቋንቋ ልክ እንደ አንድ የሙዚቃ መጫወቻ መሳርያ ነዉ። ሙዚቃን እደርሳለሁ ሙዚቃን እጫወታለሁ። በቋንቋም አዲስ ድምፀትን አዲስ ቃላትን እየደረስኩ አዲስ ቋንቋን ለመፍጠር እሞክራለሁ። ይህ የየምፈጥረዉ አዲስ ቋንቋ ደግሞ ድንበር የሌለዉ ልክ እንደ አንድ ወንዝ የሚፈስ ነዉ። በዚህም ምክንያት ያለምንም ገደብ ልክ እንደ አንድ ወንዝ ያለማቋረጥ አነባለሁ።» 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሠ