1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዩጋንዳ ሕ/መንግሥት ላይ የታሰበ ለውጥ የቀሰቀሰው ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 15 2009

የዩጋንዳ ፖሊስ ከመዲናይቱ ካምፓላ በስተሰሜን ወጣ ባለ አንድ አካባቢ በሕግ ያልተፈቀደ ስብሰባ አካሂደዋል ያላቸውን ከ50 የሚበልጡ ሰዎች ሰሞኑን አሰሯል። ይሁንና፣የተቃዋሚው ወገን የፖሊስ ርምጃ የዩጋንዳ ገዢ ፓርቲ የፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን የስልጣን ዘመን ለማራዘም በወጠነው እቅድ አንጻር የተነሳውን ተቃውሞ ለማፈን ያደረገው ነው ሲል ወቅሷል። 

https://p.dw.com/p/2gz6Y
WM Anschlag Uganda Parlament Flaggen Halbmast Terrorismus
ምስል AP

በዩጋንዳ ሕ/መንግሥት ላይ የታሰበው ለውጥ እና ተቃውሞ

የዩጋንዳ ገዢ የብሔራዊ ተከላከይ ንቅናቄ ፣ በምህጻሩ «ኤንአርኤም» ፓርቲ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈረውን፣ ማለትም ፣ ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ የሚወዳደሩትን ግለሰቦች ዕድሜ የሚገድበውን «አንቀጽ 102 ለ» ን  ከሕገ መንግሥቱ ለማውጣት መፈለጉን ባለፈው ሳምንት  ካስታወቀ ወዲህ የሕዝብ ተቃውሞ ቀጥሏል። እንደ ተቃዋሚ ቡድኖች ግምት፣ ይህ ገዢው ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ ላይ እንዲደረግ የፈለገው  ለውጥ ፣ የ73 ዓመቱን ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ከጎርጎሪዮሳዊው 2021 ዓም በኋላም በስልጣን እንዲቆዩ ለማስቻል የታቀደ ነው። 
በመንግሥቱ እቅድ አንጻር ተቃውሞ በመውጣታቸው ከታሰሩት መካከል የተቃዋሚው የዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ኖርቤት ማው፣ የፓርቲው ዋና ጸሀፊ ጀራልድ ሲሪንዳ እና «ስራ አጥ ወንድማማችነት» በሚል ቡድን ስር የሚጠቃለሉ ብዙ ወጣቶች ይገኙባቸዋል። 
ከሶስት ቀናት በፊት በፖሊስ በቁጥጥር የዋሉት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ኖርበርት ማው  እና በዕድሜው ገደብ መሰረዝ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡትን ታሳሪዎች ከተፈቱ በኋላ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ  ኖርበርት ማው አስታውቀዋል።«ለሙሴቬኒ መልሴ ግልጽ ነው። ሰዎችን ለምንድን ነው ክትባት የምንሰጠው? የታመሙ ሰዎችን አትከትብም። ክትባት የምትሰጠው ለጤነኞች ነው፣ ድንገት በሽታው ቢከሰት በሚል።»

Uganda Wahlen Proteste der Opposition
ምስል Reuters/G. Tomasevic


በመንግሥቱ እቅድ አንጻር የተቃዋሚው ወገን በዕድሜ ልክ ፕሬዚደንትነት ስልጣን አንጻር ለመታገል   «ቱጂኳታኮ»  የተባለውን  ዘመቻ አጠናክሮ በማካሄድ ላይ ነው። «ቱጂኳታኮ»  በዘረፋ ትርጉሙ እጆችህን ከ«ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ለ» አንሳ ማለት ነው። የፕሬዚደንታዊ እጩዎች የዕድሜ ገደብ መቀየር የለበትም በሚል ተቃውሞው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም እየተካሄደ ይገኛል። 
ከ1986 ዓም ወዲህ በስልጣን ላይ የሚገኙት እና የስልጣን ዘመናቸው ከአራት ዓመት በኋላ በሚያበቃበት ጊዜ የመውረድ  ሀሳብ እንዳላቸው ያልጠቆሙት ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ  በቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በእጩ ተወዳዳሪነ ት መቅረብ አይችሉም፣ ምክንያቱም፣  የዩጋንዳ «ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102  ለ »ከ75 ዓመት በላይ የሆነ ግለሰብ ለፕሬዚደንትነቱ ስልጣን በእጩነት እንዳይወዳደር ይከለክላል። 
«ቱጂኳታኮ»  የተባለው  የተቃዋሚው ወገን ያነቃቃው ዘመቻ ግን ዩጋንዳዊቷ ዣክሊን ካኩንዚ እንደሚሉት በመዲናይቱ ካምፓላ ያን ያህል ድጋፍ የለውም።
« ዴሞክራሲያችን የተጠናከረ አይደለም። ከ75 ከመቶ በላይ ከ35 ዓመት በታች የሆነ ሕዝብ በሚኖርባት ዩጋንዳ ውስጥ ፣ ወጣቱ  የራሱ መሪ ለመሆን የሚያስችለውን  ሁኔታ ይፈጥራል ብዬ  እኔ በግሌ አላስብም። »
በዩጋንዳ ለመብት የሚሟገተው የሂውማን ራይትስ ኢንሽየቲቭ ፋውንዱሽን ዋና ዳይሬክተር ሊቪንግስተን ሴዋንያና ከዚሁ  ዕድሜው ገደብ በተጨማሪ የሚያሳስባቸው ሌላ ጉዳይ እንዳለ ገልጸዋል።
«ለነገሩ፣ የዕድሜ ጉዳይ ማነጋገርም አልነበረበትም። ምክንያቱም ፣ ያ የተወሰነ ጉዳይ ነው፣ እርግጥ፣ ገና አልተሞከረም። እኔን የሚያሳስበኝ የፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን ላይ ያረፈውን ገደብ እንደገና ስራ ላይ የማዋሉ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም፣  ይህ ለኛ ዋና ዋስትናችን  ነው። የስልጣን ዘመኑ ገደብ ጥያቄ፣  በተለይ የዩጋንዳ መንግሥት እንደሚፈለገው አለመጠናከሩን እና ደካማነቱን  ስናይ፣ እንዲሁም፣ የህብረተሰቡን ሁኔታ  ስንመለከት ይህ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነው። »
በካምፓላ የማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የሕገ ፕሮፌሰር ዳንየል ሩሄዛ የዩጋንዳን ሕገ መንግሥት የጻፉት አባቶች በፕሬዚደንታዊ እጩዎች ዕድሜ ላይ ገደብ ሲያሳርፉ ካለ ምክንያት እንዳልሆነ ይናገራሉ። እና የሕገ መንግሥቱ ጸሀፍት ምክንያቶች ትክክለኛ ናቸው አይደሉም ሕዝቡrሊወያይ እና ውሳኔ ላይ ሊደርስ ይገባል ባይ ናቸው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ «አንቀጽ 102 ለ»  ን ከሕገ መንግሥቱ መሰረዝ  ትልቅ ጥፋት ያስከትላል ሲሉ ሩሄዛ አስጠንቅቀዋል። 
« ሀገራችን የምትከተለው  ስርዓተ ዴሞክራሲ ገና ወጣት ነው።  እና አሁን በሕገ መንግሥቱ ዙርያ የተጀመረውን ውይይት በትክክል ለማካሄድ ከተፈለገ  የበሰለ እና የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖረን ያስፈልጋል። »
« አንቀጽ 102 ለ»ን ከሕገ መንግሥቱ ለማውጣት የሚጠይቅ የህግ ረቂቅ እስካሁን ለዩጋንዳ ምክር ቤት እንዳልደረሰ የተናገሩት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሬቤካ ካዳጋ ሕገ መንግሥቱን እንዳቀይሩ የሚያስፈራሩ ዛቻዎች እንደደረሱዋቸው ገልጸዋል።
« የምክር ቤት እንደራሴዎች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል። ሕይወታቸው ስጋት ላይ መሆኗን የሚገልጹ ዛቻ የያዙ መልዕክቶች ደርሰዋቸዋል።  ግን ለሀገሪቱ ሕዝብ ላረጋግጥ የምፈልገው እስካሁን ለፕሬዚደንትነት በሚወዳደረው ግለሰብ ዕድሜ  ላይ ያረፈውን ገደብ የማንሳቱ ጥያቄ የሰፈረበት አንድም የሕግ ረቂቅ አላየሁም። የቀረበ የሕግ ረቂቅም የለም። ይሁንና ፣ ቁጣ ይታያል፣  እንቅስቃሴም አለ። የተሟጋቾች እንቅስቃሴም አለ። »
በዩጋንዳ ባለፉት አራት ፕሬዚደንታዊ ምርጫዎች በፕሬዚደንት ሙሴቬኒ አንጻር ተወዳደረው የተሸነፉት «ፎረም ፎር ዴሞክራቲክ ቸንጅ» የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኪዛ ቢሲጄይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ለ ለመሰረዝ የሚደረገውን ጥረት አውግዘው፣ ዩጋንዳን ወደፊት ሊያራምድ የሚችለው መፍቀሬ ዴሞክራሲ ኃይላኅ የሙሴቬኒ የብሔራዊ ተከላካይ ንቅናቄ ፓርቲ አገዛዝን ለማብቃት በሚቻልበት ዘዴ ላይ እንዲያተኩሩ ሀሳብ አቅርበዋል። 
ፖሊስ ሰሞኑን ያሰራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና ሌሎች የመንግሥቱ እቅድ ተቺዎች ከጠበቆችም ጋር ሆነ ከዘመዶቻቸው ጋር የመገናኘት መብት እንደተነፈጋቸው የተቃዋሚ ቡድን አባላት አስታውቀዋል።

Uganda Kizza Bezigye Opposition
ኪዛ ቢሲጄይምስል DW/E. Lubega
Uganda - Präsident Yoweri Museveni
ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒምስል dpa

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ