1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በየመን የተባባሰዉ ጥቃት

ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2006

የመን ዉስጥ የጥቃት ርምጃዎች እየተባባሱ ነዉ። በዛሬዉ ዕለት ብቻ ቢያንስ ስምንት የመንግስት ወታደሮችና 10 የአልቃይዳ ተዋጊዎች የተባሉ ሰዎች በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ተገድለዋል። በወቅቱም ከባድ ዉጊያ መካሄዱን በግጭቱ የተሳተፉ ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1BzkH
Jemen Soldaten Kampf gegen Al Kaida 07.05.2014
ምስል REUTERS/Yemen's Defence Ministry

የወታደራዊ ሠፈሩ ከፕሬዝደንቱ መኖሪያ ፊት ለፊት በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ነዉ የሚገኘዉ በየመኗ ዋና ከተማ ሰንዓ። ሁለት ጊዜ በእሳት የመጋየት አደጋ ገጥሞታል። እሁድ ዕለት የአልቃይዳ አባላት መሆናቸዉ የተጠረጠረ ተዋጊዎች ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅትም ከአጥቂዎቹ ሶስቱ እና አንዲ ሲቪል ህይወታቸዉ አልፏል። ከሶስት ቀናት በፊትም በዚሁ ስፍራ አምስት ወታደሮች ተገድለዋል። ባለፉት በርካታ ቀናት የመን በአዳዲስ ጥቃቶች እየተናጠች ነዉ። በተለይም በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ ቦምብ 12 ወታደሮች ተገድለዋል። ባለፈዉ ዓርብ የየመን የመከላከያ ሚኒስትር ሞሐመድ ናስር አህመድ እዚያዉ ደቡብ ዉስጥ ከጥቃት ለጥቂት አምልጠዋል። እየተባባሰ በመጣዉ ጥቃትም እዚህም እዚያም የሚሞትና የሚቆስለዉ ተበራክቷል።

የመን ዉስጥ የወታደራዊ ይዞታዎችና ተቋማትን ማጥቃት ያልተለመደ አይደለም። ባለፈዉ ታህሳስ ወር ሰንዓ ዉስጥ የሚገኘዉ ወታደራዊ ሃኪም ቤት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ለ52 ሰዎች ህልፈተህይወት ምክንያት ሆኗል። ከእነሱ መካከልም የጀርመኑ ዓለም ዓቀፍ ትብብር GIZ ሠራተኞች የሆኑ ጀርመናዉያን ይገኙበታል። የመን ዉስጥ በአሁኑ ወቅት ለተባባሰዉ ጥቃት መነሻ ምክንያቱ መንግስት ለሚወስደዉ የማጥቃት ርምጃ ምላሽ መሆኑን ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነዉ ሞሐመድ ኤል ቃዲ ይገልጻል፤

Jemen Anschlag in Sanaa 05.05.2014
ምስል Mohammed Huwais/AFP/Getty Images

«ወታደራዊዉ ዘመቻ ያልተጠበቀ፣ ጠንካራና ለመጀመሪያ ጊዜ አልቃይዳን ለማጥቃት የቆረጠ ነዉ። እናም አሁን ከፍተኛ ስጋት አለ፤ ምክንያቱም የአልቃይዳ ተከታዮች ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የተበታተኑ ናቸዉ። እናም ይህ ጠንካራ ዘመቻ ከባድ ተፅዕኖና ጉዳት ካደረሰባቸዉ በኋላ እነሱም በኃይለኛ ቁጣ የአፀፋ ጥቃታቸዉን እዚህም እዚያም መቀጠላቸዉ አይቀርም። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነዉ ሃድራሞስ ዉስጥ በወታደራዊ የጦር ሠፈር ላይ ያደረሱት የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ነዉ።»

ደቡባዊ የመን ዉስጥ የመንግስት ወታደሮች ላለፉት ሶስት ሳምንታት እስላማዊ ፅንፈኞቹን ማጥቃታቸዉን ቀጥለዋል። የፅንፈኙ ጠንካራ ይዞታ በሆነዉ ሸዋብ ክፍለ ሃገርም የፀጥታ ኃይሎቹ ጥቃት አይሏል።

Jemen Großoffensive gegen mehrere Hochburgen der Al-Qaida
ምስል picture-alliance/dpa

በአረብ ባህረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሰዉ የአሸባሪዉ ድርጅት የአልቃይዳ ክንፍ የመንና በመጠኑ ደግሞ ስዑድ አረቢያ ዉስጥ መኖሩ ነዉ የሚገለጸዉ። የመን ዉስጥ የሚገኘዉ የአልቃይዳ ተዋጊ ኃይል ፓኪስታን ዉስጥ ካለዉ የቡድኑ አካል ጋ ግንኙነት ቢኖረዉም ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነዉ በርሊን የሚገኘዉ የዓለም ዓቀፉፖለቲካ ሳይንስ ተቋም የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳዮች ተንታኝ ጉዊዶ ሽታይን በርግ የሚገልጹት። ቡድኑ ትንሽ ቢሆን የሚቃወመዉ አካል ደካማነት ጠቅሞታልም ባይ ናቸዉ።

« የመን ዉስጥ የሚገኘዉ አልቃይዳ ከፓኪስታኑ አልቃይዳ ጋ ግንኙነት ቢኖረዉም በአብዛኛዉ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነዉ። ሆኖም ከቀጣይ ርምጃቸዉ አይገቱም። ዓላማቸዉም የሰንዓዉን መንግስት በማስወድ እስላማዊ መንግስት የመን ዉስጥ መመሥረት ነዉ። ከ2011 እስከ 2012 ደቡባዊ የመን ዉስጥ በአንድ አነስተኛ አካባቢ ይህን ሞክረዋል፤ ሳይሳካላቸዉ ቢቀርም ዳግም ሁኔታዎች በማመቻቸት የቀድሞዉን ስልታቸዉን ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከሩ ነዉ። በጣም ትንሽ ቡድን ነዉ ነገር ግን በሚቃወመዉ ወገን ድክመት እየተጠቀመ ይገኛል፤ ይህም በተለይ የየመን መንግስት ነዉ።»

አሸባሪዉን ቡድን ለመዋጋት የዉጭ ድጋፍ ካላገኘ በቀር የየመን መንግስት በእርግጥ ደካማ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ተጠርጣሪ የአልቃይዳ ደጋፊዎች የሚገኙበትን አካባቢ በተደጋጋሚ ደብድበዋል። ባለፈዉ ሰኞ ዕለት ባካሄዱት ድብደባ ስድስት የቡድኑ ታጣቂዎች መገደላቸዉ ተሰምቷል። በዚህ ምክንያትም እንደሽታይንበርግ የዉጭ ድጋፍ በእጥፍ ማደግ እንደሚኖርበት ይታመናል። በሌላ በኩል ግን ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖቹ የሚያደርሱት ድብደባ ሲቪሎች ላይ ጉዳት በማድረሱ በርካታ የመናዉያንን አስቆጥቷል። በዚህ መዘዝም የዉጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አደጋ ሊጣል ይችላል የሚል ስጋት አለ። ለአዉሮጳ ኅብረት ልዑካን የሚሠራ ፈረንሳዊ የጥበቃ ባልደረባ ከቀናት በፊት ሰንዓ ዉስጥ በጥይት ተገድሏል። ሁለት የጀርመን ኤምባሲ ሠራተኞች ደግሞ ቀደም ሲል ከጥቃት ለጥቂት አምልጠዋል። የየመን የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር አዲስ ጥቃት ሊከተል እንደሚችል በመግለፅ የፀጥታ ጥበቃዉን አጠናክሯል። የአሜሪካን ኤምባሲ በዚሁ ምክንያት ለጊዜዉ ተዘግቷል። የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ ሞሐመድ አል ካይድ ሁኔታዉ ሊባባስ እና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፤

Sanaa Soldaten Straßenkontrolle 20.04.2014
ምስል Mohammed Huwais/AFP/Getty Images

«በእርግጠኝነት ሁኔታዉ ሊባባስና የከፋ መሆኑ አይቀርም። በዚህ ሁኔታም መንግስት የፀጥታ ኃይሎቹን በሙሉ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ማድረግና አልቃይናድ የሚፋለሙበትን ስልት መቀየር ይኖርበታል። ከዚህም ሌላ የስለላ ሠራተኞቹን ማጠናከርና ቢያንስ አልቃይዳ በዚህ ረገድ የሚያደርገዉን እንቅስቃሴ መገደብ ይኖርበታል። የመን በተለያዩ ግንባሮች አይቃይዳን በወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ታጣቂዎችን የሚያፈራበት አመለካከቱን ራሱ ለመዋጋት የዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ያስፈልጋታል።»

እንዲያም ሆኖ በአልቃይዳ ተዋጊዎች እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ለመገንጠልና ራሳቸዉን ለመቻል የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያካሂዱት ፍልሚያም ሌላዉ የየመን ራስ ምታት ነዉ። በአሁኑ ይዞታ የመንግስት ህልዉና ከሰንዓ የሚዘል ዓይነት አይመስም።

አንድርያስ ጎርዝቭስኪ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ