1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዚምባብዌ ተቃዋሚ ቡድን አንፃር የቀጠለው የእሥራት ርምጃ

ዓርብ፣ ኅዳር 11 1996
https://p.dw.com/p/E0lG
የጀርመን ጋዜጦችና መጽሔቶች በዚህ ሣምንት ከተመለከቱዋቸው አፍሪቃ ነክ ጉዳዮች መካከል የዛሬው አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች ዝግጅታችን በመጀመሪያ በዚምባብዌ ተቃዋሚ ቡድን አንፃር ለቀጠለው የእሥራት ርምጃ ትኩረት ሰጥቶዋል። ዚምባብዌን እከፋው ምሥቅልቅል ሁኔታ ላይ ጥለዋል በሚል በሀገሪቱ ገዢ መደብ አንፃር ሒስ ከመሰንዘር ወደ ኋላ የማይሉት የዚምባብዌ ፕሮፌሰሮች አሁን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ባጠናከሩት ድንገተኛ አሠሣ ሥጋት እንደተደቀነባቸው የግራ ክንፉ ዕለታዊ ዚውድዶቸ ጋዜጣ አስታውቋል። የሀራሬ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆን ማኩሜ ሙጋቤ በሚከተሉትና እርሳቸውም አጥፊ በሚሉት የሀገሪቱ ነጮች የእርሻ ቦታዎችን በወረሱበት ፖሊሲ አንፃር ግልፁን ወቀሳ በማሰማታቸውና በሀገሪቱም የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ በመጠየቃቸው አሁን እንደ ወንጀለኛ ወህኒ ወርደዋል። ከማኩምቤ ጎን ሌሎች የመንግሥቱን ፖሊሲ በመቃወም አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎች፡ ከፍተኛ የሙያ ማኅበራት መሪዎችም ጭምር የእሥራት እጣ ገጥሟቸዋል። ይኸው የዚምባቤ መንግሥት ርምጃ ባንድ በኩል፡ እንዲሁም፡ ምንም እንኳን የኮመኔልዝ ድርጅት የዚምባብዌ መንግሥት በሚከተለው የጭቆና አሠራር የተነሣ ሀገሪቱን እአአ እስከተያዘው አውሮጳዊ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከማኅበሩ ቢያግድም፡ ሙጋቤ የፊታችን ታኅሳስ ወር በናይጀሪያ በሚደረገው የኮመኔልዝ ድርጅት ዓቢይ ጉባዔ ላይ እንደሚካፈሉ ያስታወቁበት ድርጊት ዓለም አቀፉን ኅብረተ ሰብ አብዝቶ ነው ያስቆጣው። ሙጋቤ በዚሁ አነጋገራቸው በነጮቹና በጥቁሮቹ የኮመንዌልዝ አባል ሀገራት መካከል ልዩነት ለመፍጠር ነው የፈለጉት። የዓቢዩ ጉባዔ አስተናጋጅ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንዦ፡ በደቡብ አፍሪቃ አቻቸው ታቦ ምቤኪ አንፃር፡ ብሪታንያና አውስትሬሊያ ዚምባብዌ ትገለል ዘንድ የያዙትን አቋም ሲደግፉ ከቆዩ በኋላ አሁን የሮበርት ሙጋቤ በዓቢዩ ጉባዔ ተሳትፎን በተመለከተ የአቋም ለውጥ በማድረግ፡ ሰሞኑን ሙጋቤን የጎበኙበት ሁኔታ በኮመንዌልዝ አባል መንግሥታት መካከል ልዩነቱን ይበልጡን እንዳይገዝፈው አሥግቶዋል። ሙጋቤ በጉባዔው የማይሳተፉበት ሁኔታ ኦባሳንዦን አጣብቂኝ ሁኔታ ላይ ሊጥላቸው ይችላል፤ ምክንያቱም መጋቤ ከስብሰባው ከተገለሉ፡ ሌሎቹ የኮመንዌልዝ አባል አፍሪቃውያት ሀገሮች መሪዎችም ከዓቢዩ ጉባዔ ሊርቁ ይችላልና።