1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓል እና አዲስ አበባ

ሰኞ፣ መስከረም 1 2010

አዲስ አበባ ገና ከዋዜማው ጀምሮ ለበዓሉ ዝግጅት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሞልታ ነበር፡፡ የበግ፣ የዶሮ እንዲሁም የመሰረታዊ ሸቀጦች አይቀመሴነት እንደተጠበቀ ሆኖ የመብራት መቆራረጥ በበዓሉ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ነበረው፡፡

https://p.dw.com/p/2jjAg
Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien
ምስል Yohannes Geberegziabeher

በዓል እና አዲስ አበባ

መዲናይቱ አዲስ አበባ ዋዜማን ደመቅ ባለ ድባብ አሳልፋለች፡፡ በየቦታው ከነበሩ የሙዚቃ ድግሶች ጀምሮ እሰከ የመጨረሻ ሰዓት የበዓል ግብይት ድረስ ነዋሪዎቿ በዓሉን ለመቀበል ሽር ጉድ ሲሉ ነበር የዋሉ ያመሹት፡፡ ለበዓሉ ማድመቂያ እኩለ ለሊት ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ርችት ተተኩሷል፡፡ ዛሬ ንጋት ላይ መድፍ ተተኩሷል፡

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ደግሞ ለ10 ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው የአዲስ ዓመት አቀባበል ማሳረጊያ ትላንት ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሄዷል፡፡ ሀገሪቱ በድርቅ እና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለችበት ሁኔታ እንዲህ አይነት በርካታ ብር የፈሰሰበት ዝግጅት መደረጉ ትችቶች አስከትሏል፡፡ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዩሃንስ ገብረእግዚያብሔር ያነጋገራቸው የከተማይቱ ነዋሪዎችም ይህንኑ ሀሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ በዓሉን አስመልከተን የተለያዩ ሰዎችን ሀሳብ ተቀብለናል፡፡ በተለይ ለበዓሉ አቀባበል ተብሎ መጀመሪያ 20 ሚሊዮን ከዚያ ወደ አራት ሚሊዮን ብር ዝቅ አለ ተብሎ የተነገረው የበዓሉ ዝግጅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ በሚሰቃዩበት ጊዜ እንዲህ አይነት ዳንኪራ መዘጋጀቱ ብዙም አልተወደደም፡፡ 

ለበዓሉ ዝግጅት ወጣ የተባለውን ብር እና ሁለቱ ያለጨረታ ዝግጅቱን ያዘጋጁ ድርጅቶች ተከፈለን ያሉት የሰማይ እና የምድር ርቀት ያለው በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ለማካተት ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን አዘጋጆቹ ስልካችንን ባለማንሳታቸው ለጊዜው አልተሳካልንም፡፡ ትላንት ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ የቀረበው ዝግጅት ከመዝናኛ ይልቅ ስብሰባ ይመስል ነበር፡፡ ደረቅ እና ፈጠራ ባልታከለበት መልኩ ስለሀገሪቱ ሰላም፣ ልማት፣ ወዘተ…ሙዚቃዊ ድራማ በሚል ሽፋን ሲቀርብ በዝግጅቱ የተሰላቹ ታዳሚዎች በፉጨት ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡   

 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ሂሩት መለሰ