1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮንጎ የተካሄደዉ ምርጫና የአዉሮፓ ሚና

ሰኞ፣ ሐምሌ 24 1998

የተባበሩት መንግስታት ባሰፈረዉ መረጃ መሰረት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ40 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያዉ በርካታ ፓርቲዎችን ያሳተፈዉ ምርጫ ትናንት ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/E0iK
ለምርጫ ከወጣዉ ህዝብ ከፊሉ
ለምርጫ ከወጣዉ ህዝብ ከፊሉምስል picture-alliance/dpa

የመንስግታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪዎችም ምርጫዉ በሰላም እንዲከናወን የበኩላቸዉን ሃፊነት ተወጥተዋል።

በኪንሻሳ የሚገኙት 280ዎቹ የፌደራል ጀርመን ወታደሮች ካምፓቸዉ ዉስጥ መዋላቸዉ ነዉ የተነገረዉ። ለምርጫ የወጣዉ ህዝብም ቀደም ብሎ ከተገመተዉ በላይ ነበር።

የአዉሮፓ ህብረት በኮንጎ ምርጫ የወሰደዉ የሰላም ማስከበር ኃላፊነት ከታሰበዉ የጊዜ ገደብ በላይ ሳይራዘም እንደማይቀር ታዛቢዎች ይገልፃሉ።

እንግዲህ መላዉ የኮንጎ ዜጎች በምርጫዉ ከረኩ ነዉ ምርጫዉ የተረጋገጠ ነበር ማለት የሚቻለዉ። ያ ደግሞ አገሪቱ ወደዲሞክራሲ ጎዳና መግባቷንና በግዛቷ ነግሶ የከረመዉን ጦርነት ለማቆም ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

የምርጫ ኮሚሽኑ የበላይ ይህንኑ ጉዳይ ደግመዉ ደጋግመዉ ሲናገሩት ተደምጧል። አስቸጋሪዉ ነገርም እዚህ ጋ ነዉ ያለዉ።

ከምርጫዉ በፊት ግዙፎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫዉ አንሳተፍም ብለዋል። ይህም የምርጫዉ ዉጤት የተጭበረበረና ተቀባይነት የሌለዉ ነዉ እንዲሉ መንገድ ይከፍታል።

ይህ ደግሞ ይበልጥ የከፋ የሚሆነዉ ድምፅ የሰጡት ዜጎች የተቃዋሚዎቹን ፓርቲዎች ጥያቄና ተቃዉሞ ከደገፉ ነዉ።

የኮንጎ ዜጎች ፍፁም የድህነት ኑሮ የሚገፉ ወገኖች ናቸዉ። ልጆቻቸዉን የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት፤ ቢታመሙ የህክምና እርዳታ የሚያገኙባቸዉ ሃኪም ቤቶችም ሆኑ መድሃኒቶች የላቸዉም።

አሁን ሁሉም ተስፋቸዉን በምርጫዉና ዉጤቱ ላይ አድርገዉ እየተጠባበቁ ነዉ።

ጦርነት ያዳከማት አገራቸዉ ሰላም አግኝታ ማየት ይፈልጋሉ። አገራቸዉ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገች መሆኗን አሁን አዉቀዋል።

የዚህ ሃብት ሽያጭ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎቹ በሙስና የተሳሰሩት የአገራቸዉ ምሁራንና ባለነፍጥ ባለስልጣናቶቻቸዉ መሆናቸዉንም ተረድተዋል። በአጭር ጊዜ ዉስጥ ግን እንዲህ ካለዉ ተፅዕኖ ለመላቀቅ የሚቻል አይመስልም።

ይልቁንም 500 መቀመጫ ላለዉ ምክር ቤት 10,000 እንዲሁም ለአንድ ፕሬዝደንት 32 እጩ ተወዳዳሪዎች መቅረባቸዉ በኮንጎ የፖለቲካ ስልጣን መጨበጥ ማለት የጣፈጠ የንግድ ዓለም ዉስጥ መግባት እንደሆነ ተደርጎ እንደተወሰደ ነዉ የሚያመላክተዉ።

ከኪንሻሳ የሚወጣዉ የምርጫ ዉጤት ብቻ አይደለም ለዉጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀዉ በተለይ የምስራቅ ዉጤት ወሳኝ ነዉ። ባለፉት ጊዜያት በኮንጎ ሲካሄዱ ለነበሩት ጦርነቶች መነሻዉ አካባቢ ምስራቁ ነበርና።

በዚያም ላይ ጎረቤት ሀገራት እነሩዋንዳ፤ ዑጋንዳ፤ አንጎላን ጨምሮ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገችዉ ኮንጎ የተስተካከለ መንግስት ኖሯት ለማየት አይፈልጉም።

ምክንያቱም በሙስና ከተሳሰሩት ወገኖችና በነፃነት ታጋይነት ስም ከተሰማሩት ጎን በመሆን ከጥሬ ሃብቷ በመቋደስ ልማድ ከዘረጉ ቆይተዋልና በግጭቱ አትራፊዎች ናቸዉ።

ያም ሆኖ ግን ምርጫዉ ያለምንም አማራጭ ተካሂዷል። ዕለቱም ቢሆን UDPS የተባለዉ ተቃዋሚ ቡድን ከሚንቀሳቀስባት ምቡጂ-ማይ ከተማ በቀር በአብዛኛዉ በሰላም ነበር የተካሄደዉ።

ለዚህ ምርጫም አዉሮፓ ወታደሮችን ጨምሮ በርካታ ገንዘብ መድባ መሰለፏ ግልፅ ነዉ። የተባበሩት መንግስታትና የአዉሮፓ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል እዚያ መገኘት የጦር አበጋዞቹ እንዳሻቸዉ ህዝቡን ወደብጥብጥና ዉዝግብ እንዳይገፉት ይረዳል።

በቀጣዮቹ ሳምንታትና ወራትም ኮንጎ ችግር ዉስጥ እንደምትቆይ ይጠበቃል፤ የምርጫዉ ዉጤት ተጣርቶ አሸናፊዉ በዉል ፀድቆ እስኪለይ። በስፍራዉ የሚገኘዉን የሰላም አስከባሪ ኃይል ስራም ያበዛል።

30ሚሊዮን ኗሪዎች ያሏት የኮንጎ ሰላም ማለት የአንድ አገር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሰላም ነዉ ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ከአዉሮፓዉያኑ 1996 እስከ 1997ዓ.ም ድረስ በኮንጎ የተካሄደዉ ጦርነት አገራዊ ሳይሆን ግማሽ የሚሆኑትን የአህጉሪቱን ሀገራት ያሳተፈ ነበርና።

በወቅቱም 4ሚሊዮን ሰዎች የጦርነቱ ሰለባ ሆነዋል። ኮንጎ በስፋት ጀርመንን ስድስት ጊዜ እጥፍ ትሆናለች። ሰላም ቢኖራት ኖሮ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ብቻ ህዝቦቿ በብልፅግና ሊኖሩ ይችሉ ነበር።