1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮንሶ የቀጠለዉ ዉጥረት

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2008

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የኮንሶን ማኅበረሰብ ራሱን ችሎ በዞን እንዲተዳደር ያቀረበው ጥያቄ ተከትሎ የተቀሰቀሰዉ ዉጥረት አልሰከነም። ባለፈዉ እሁድ ሁለት ሰዎች በልዩ ኃይል ፖሊሶች መገደላቸዉን፤ ሌሎች ሁለት ሰዎች ክፉኛ መቁሰላቸዉና በርካቶች ለእስር መዳረጋቸዉን የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1IEae
Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson


እነዚሁ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ባደረሱን መረጃ መሠረት ነዋሪዉ ወደ መንገድ መዉጣት አልቻለም ፣ መሥርያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።
ባለፈዉ እሁድ በኮንሶ ዴበና በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ዉስጥ ሁለት ሰዎች መገደላቸዉንና በርካቶች መታሠራቸዉን የሚናገሩት የአካባቢዉ ነዋሪ መምህር ጌታቸዉ ሶካ እንደሚሉት ሰዉ ከቤቱ እንዳይወጣ እየተደረገ ነዉ።
« ባለፈዉ እሁድ ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢዉ ላይ ዘጠኝ መኪና የሚሆን ልዩ ኃይል መጥቶ ነበር። በዝያን እለት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ከዚያ በኋላ እስከዛሬ ጦር ሠራዊቱ ድረስ አካባቢዉን ቀበሌዉን እንደከበበ ነዉ። ከሰፈር ማንም እንዳይወጣ ሁሉ እየተደረገ ነዉ። ከተማም ሰዉ እንደፈለገ እንዳይንቀሳቀስ እየተደረገ ነዉ። አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነዉ ያለነዉ።»

የዛሬዉ ሁኔታ እንዴት ነዉ?
« ዛሬም አስፈሪ ነዉ በኛ አካባቢ ገበያ ቀን ነዉ። ከዚህ በፊት በዚህ ቀን በጣም ይንቀሳቀስ የነበረዉ ሕዝብ አይንቀሳቀስም። ሰዉ ፈርቶአል። ሰራዊቱ አካባቢዉን ስለከበበ እንዴት ብሎ ይወጣል?»
ሌላዉ የአካባቢዉ ነዋሪ አቶ ዴኖቴ ላለፉት ከአስር ቀናት የኮንሶ ማኅበረሰብ ባህላዊ መሪ ባልታወቀ ምክንያት እስር ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
« የኮንሶ ባህላዊ ወይም የጎሳ መሪዉ አሁን የተሾመ አይደለም። የኮንሶ ባህላዊ መሪዎች ስልጣናቸዉን የዘር ሃረግ ጉዳይ የሆነ ከአባት ወደ ልጅ ነዉ የሚቀባበሉት ነዉ። እናም ባህላዊ መሪዉ ማኅበረሰቡ ባቀረበዉ ጥያቄ መሠረት ሕዝብ ከወከላቸዉ አንዱ አባል እንደሆነ ነበር የሚታወቀዉ። የፖለቲካ ሰዉ አይደለም፤ ይህንን ደግሞ ከክልል እስከ ፊደራል ያለዉ ሰዉ ሁሉ ያዉቃል ባልታወቀ ምክንያት ወስደዉ አፍነዉ ወህኒ ጨምረዉታል። አርባ ምንጭ ወህኒ ቤት ነዉ ያለዉ። ባህላዊ ጌጡንም ባህላዊ ቱማዉንም በዉርስ የሚተላለፈዉንም የጎሳ መሪነት መለያዉን ወስደዉበታል።»

Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson


ሌላ በኩል ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያስረዱ የተላኩት የአካባቢዉ ሽማግሌዎች የእስር ማዘዣ ስለተላለፈባቸዉ ግማሾቹ ታስረዋል ፤ ገሚሱ ደግሞ ተሸሽገዉ ያሉበት ቦታ አይታወቅም። « እነሱማ ፊደራል ሄደዋል ክልል ሄደዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሄደዋል፤ የሚመለከታቸዉ ጋር ሁሉ ሄደዉ ደብዳቤዉን በግልጽ ሰጥተዉ ነዉ ያነጋገሩዋቸዉ። በአሁኑ ሰአት እንዲያዙ የሚል ትዕዛዝ በመተላለፉ ግማሾቹ ታስረዋል ግማሾቹ አምልጠዉ ተደብቀዋል። »


አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ