1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል

ዓርብ፣ ጥቅምት 10 2010

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፡፡ ዛሬ ከሰዓት የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለሰዓታት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደነበር የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ወደ ከተማ ወጥተው ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ የነበሩት ወጣቶች በአገር ሽማግሌዎች ልመና ሀሳባቸውን እንደቀየሩም ተሰምቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2mGnG
Äthiopien Oromiya MBO Universität
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለሰዓታት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ተቃውሞዎች  ቀጥለዋል፡፡ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ በመፈክሮች የታገዙ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ እንደነበር የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ትናንትም ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲያካሂዱ ነበር። ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራቸውን የሚናገረው ስሙ እንዳይገለጽ የሚፈልግ አንድ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ለመውጣት ያደረጉትን ሙከራ በሽማግሌዎች ልመና መተዋቸውን ያስረዳል፡፡ ተቃውሟቸውን ግን በግቢያቸው ውስጥ ሆነው ለሁለት ሰዓታት ያህል ያለማቋረጥ ተቃውሟቸው በጩኸት አጅበው መቀጠላቸውን ይገልጻል፡፡ 

“የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የሚደረገውን የጅምላ ጭፍጨፋ ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበው፣ ተነሳስተው ነበር፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀገር አዛውንቶች ወጥተው ከግቢ እንዳይወጡ እና ያላቸው ጥያቄ ግቢ ውስጥ ሆነው እንዲመለስላቸው ተማሪዎቹን አስተባብረው ወደ ግቢ እንደሚለሱ ነው ያደረጉት፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ብቻ፣ ያላቸውን ጥያቄ የመንግስት አካላት መጥተው እዚያው በግቢ ውስጥ እንደሚመልሱላቸው እና እዚያው ጥያቄያቸውን እንዲያደርጉ ተብሎ ነው፡፡ በተለያየ ቦታ ህዝባችን በጥይት እየተመታ ስለሆነ፣ ያ ነገር እንዳይከሰት፣ ልጆች መሞት የለባቸውም በማለት የሀገር ሽማግሌዎች ወጥተው ተማሪዎችን እዚያው በግቢው ውስጥ እንደያዟቸው ነው”ይላል ነዋሪው፡፡ 

Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የሀገር ሽማግሌዎቹ  የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መጥተው ጥያቄዎቻችሁን እንዲመልሱ እናደርጋለን ብለው ተማሪዎቹን ማረጋጋታቸውን ነዋሪው ይናገራል፡፡ የተማሪዎቹን ጥያቄ በተመለከተ ደግሞ ተከታዩን ተናግሯል፡፡ “ጥያቄያቸው የተለያየ ነገር ነው፡፡ በድንበር ላይ የሚያልቀው የኦሮሞ ህዝብ እርሱ ይብቃ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ መፈናቀል የለበትም ነው፡፡ ተመልሶ ደግሞ የወያኔ መንግስት አመራሮች አፈና እና የኦሮሞን ህዝብ የሚያቀጭጭ የሚያደርጉትን ነገር ያቁሙ ነው፡፡ የወያኔ መንግስት ከዚህ በኋላ የኦሮሞን ህዝብ መወከል፣ ማስተዳደር አይችልም ነው” ሲል የሰማቸውን ተቃውሞዎች ጥቅል ሀሳብ ዘርዝሯል፡፡ 

እንደ አምቦ ሁሉ በሆሮ ጉድሩም ትላንት እና ከትላንት በስቲያ ለሁለት ቀናት ተቃውሞ እንደነበር ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካበቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ ቢጠናቀቅም የአካባቢው ባለስልጣናት ሰልፉን ያቀነባበሩትን ግለሰቦች ለመያዝ ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡  

“ከትላንት እና ወዲያ በሆሮ ጎድሩ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ ትላንትና ደግሞ በሆሮ ጎድሮ በአጫኖ ትምህርት ቤት እዚያ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር፡፡ ሰልፉ ይሄ ‘የወያኔ መንግስት ይወረድልን፣ የእኛ ባንዲራ ይሰቀልልን’ የሚል ነበር ፡፡ በላይኛው ፊንጫ አጫኖ ትምህርት ቤት የሚባል አለ፡፡ እነርሱም ትላንትና ‘የወያኔ ይወረድና ባንዲራችን ይሰቀልልን፣ ይሄን መንግስትም አንፈልግም፣ በቃ ይወረድልን’ በሚል ነበር” ብለዋል፡፡     

ከትላንት በስቲያ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናገዱት ፍቼ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ጫንጮ እና ሙከጡሪ ዛሬ የመረጋጋት ሁኔታ እንደሚታይባቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ ገልጸዋል፡፡ “በፍቼ ከሶስት ቀናት በፊት ተቃውሞ ነበር፡፡ ዛሬም ትላንትም አልነበረም፡፡ ገብረ ጉራቻ፣ ሙከጡሪ እና ጫንጮ አካባቢ ብዙ ጊዜ ተደርጓል፡፡ ዛሬ ሁሉም ቦታ ሰላም ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

ዛሬ ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከትላንት ወዲያ የተቃጠሉት ስድስት መኪኖችን ጫንጮ መግቢያ  ላይ መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የደህንነት እና ጸጥታ ክፍል ዛሬ ለሰራተኞች ባሰራጨው የደህንነት ማሳሰቢያ መልዕክቱ በፊንፊኔ ልዩ ዞን በጫንጮ ያለው የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለስልጣን ንብረት እና መኪኖች መውደማቸውን የደረሰውን ዘገባ ጠቅሶ ጠቁሟል፡፡ በደምቢ ዶሎ እና ጊምቢ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እና በገብረ ጉራቻም በርካታ መኪኖች መቃጠላቸውን ገልጿል፡፡ ከጥቀምት 3 እስከ ትላንት ጥቅምት 9 ባሉት ጊዜያት በምዕራብ አርሲ፣ አሩሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እንደዚሁም በፊንፊኔ ልዩ ወረዳዎች መንግስትን የሚቃወሙ ሰልፎች መካሄዳቸውን አትቷል፡፡   

Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

በሰልፎቹ ላይ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳይሳተፉ ተደጋጋሚ ተማጽኖ ሲያቀርብ የቆየው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰልፎቹን ወደ ብጥብጥ ለመቀየር ሞክረዋል የተባሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ትላንት በግል ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው “ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ የተካሄደውን ሰልፍ ወደ ረብሻና ነውጥ በመቀየር የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የኦሮሚያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እያዋላቸው ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ኃላፊው በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን በእጅ ስልካቸው ላይ ተደጋጋሚ ጥሪ ብናደርግም ምላሽ አልሰጡንም፡፡ የኦሮሚያ ጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ ደግሞ ጥያቄያችንን ካደመጡ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ