በኢንጋቢሬ ላይ የተላለፈው ብይን
ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2005
እአአ በ1994 ዓም የተካሄደውን የጎሣ ጭፍጨፋ ክደዋል በሚል በተመሠረቱባቸው ሁለት ክሶች ጥፋተኛ ሆነው አግኝቶዋቸዋል።
በርዋንዳ የተቃዋሚው የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ኢንኪንጊ መሪ ወይዘሮ ቪክቷር ኢንጋቢሬን የመጨረሻ ብይን ለማስማት የመጣው ሰው ፍርድ ቤቱን አጣቦ ነበር። በእሥር ላይ የሚገኙት ኢንጋቢሬ ስድስት የተለያዩ ክሶች ቢመሠረቱባቸውም፡ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽዋን በሁለቱ፡ ማለትም፡ ርዋንዳን በሽብር ተግባር ለመጉዳት አሢረዋል፡ እንዲሁም፡ እአአ ከ1994 ዓም በብዛት የቱትሲ ጎሳ የተገደሉበትን የጎሳ ጭፍጨፋ ክደዋል በተሰኙት ክሶች ጥፋተኛ ሆነው እንዳገኛቸው አስታውቋል።
ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሕግጋት መሠረት፡ በዚህ ዓይነቱ ክስ ፍርድ ፊት ሲቀርቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዚያቸው በመሆኑና፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሽብር ተግባር ለመጉዳት ማሤራቸው ከባድ ተፅዕኖ ባለማሳረፉ፡ ቅጣታቸው ተቀንሶዋል። በሁለት ክሶች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ስምንት ዓመት እሥራት ተበይኖባቸዋል።
ኢንጋቢሬ በሌሎች አራት ክሶች፡ አንድ የአሸባሪዎች ድርጅት ለማቋቋም እና የሀገሪቱን ሥነ ሥርዓት የሚያውኩ ጭምጭምታዎች ለመንዛት አሢረዋል በተባሉባቸው ክሶች ጭምር ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ዳኛው አስታውቀዋል። ብይኑን በተሰጠበት ጊዜ ኢንጋቢሬ በፍርድ ቤቱ አልተገኙም፤ ኢንጋቢሬ በርዋንዳ የፍትሕ አውታር ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለፅ ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ ጉዳያቸውን ከተመለከተው ችሎት ርቀዋል።
ብይኑን እንደማይቀበሉት ያስታወቁት የኢንጋቢሬ ጠበቃ ያን ኤድዋርድስ በብይኑ አንፃር የሚወስዱትን ርምጃ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል።
« ቀጣዩ ርምጃችን ይግባኝ ማለት ነው። ዛሬ በተላለፈው ብይን አንፃር የይግባኝ ማመልከቻ እናስገባለን። በተቻለ ፍጥነት ወደ ላዕላዩ ፍርድ ቤት እንሄዳለን። »
ልክ እንደ ኢንጋቢሬ ጠበቃ ብዙዎቹ በፍርድ ቤት ችሎቱን የተከታተሉት የኢንጋቢሬ ፓርቲ ደጋፊዎች በብይኑ መገረማቸውን ገልጸዋል። የተቃዋሚው የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ኢንኪንጊ መሪ ኢንጋቢሬ ምክትል ቦኒፋስ ቱዋጊሪማና ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው የስምንት ዓመት እሥራት ቅጣት በፍፁም ትክክል እንዳልሆነ አመልክተዋል።
« በጣም ነው የተገረምነው። መሪያችን መፈታት ነበረባቸው። ምንም ዓይነት ስህተት አልሰሩምና። ጥፋተኛ አይደሉም። »
በኢንጋቢሬ ላይ እአአ ከ1994 ዓም የጎሣ ጭፍጨፋ ጋ በተያያዘ ለተመሠረተባቸው ክስ መነሻ የሆነው ኢንጋቢሬ እአአ ጥር፡ 2010 ዓም በርዋንዳ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለመወዳደር በስደት ከነበሩባት ኔዘርላንድስ ወደ ሀገራቸው በተመለሱበትና በመዲናይቱ ኪጋሊ የሚገኘውን እአአ ለ1994 ዓም የጎሣ ጭፍጨፋ የተሰራውን መታሰቢያ በጎበኙበት ጊዜ የሰጡት አስተያየት ነበር። ኢንጋቢሬ በጎሣ ጭፍጨፋው ወቅት ለተገደሉት ለዘብተኛ የሁቱ ጎሣ አባላት ሞት ተጠያቂዎቹ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ሲሉ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።
በኢንጋቢሬ ችሎት ወቅት ዓቃብያነ ሕግ የኢንጋቢሬን በሽብር ተግባር ተሳትፎ ያሳያል ያሉዋቸውን ማስረጃዎች፡ እንዲሁም፣ ኤፍ ዲ ኤል አር ኤ ለተባለው እና በጎረቤት ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለሚገኘው የሁቱ ዓማፂ ቡድን ገንዘብ አስተላልፈዋል ያሉበትን ማስረጃ ጭምር አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ የኤፍ ዲ ኤል አር ኤ አባል መሆናቸውን ባመኑ እና በርዋንዳ ላይ ጥቃት የሚሰነዝር አንድ ቡድን እንዲያቋቁሙ ከኢንጋቢሬ ገንዘብ እንደተቀበሉ በመሰከሩ ሌሎች አራት ተከሳሾች ላይ ከሁለት እስከ አራት ዓመት እሥራት በይኖዋል።
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ