1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 2007

« የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ በጣም እወዳለሁ። እንጀራ በዶሮ ወጥ መብላት ለምጃለሁ። ጥብስም በጣም እወዳለሁ። የዶም በየአይነቱ የማዘወትረዉና የምወደዉ ምግቤ ነበር። በኢትዮጵያ የገና፤ የፋሲካ በዓል አከባበር እጅግ ዉብ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/1GMst
Äthiopien Constanze Prehl
አማርኛ ተናጋሪዋ ጀርመናዊት ኮንስታንሰ ፕሬልምስል Constanze Prehl

ጀርመናዊትዋ « ወደ ሐገሬ ስመለስ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዉያን ይዤ የምሄደዉ የበማኅበረሰቡ የሚታየዉን ሞቅ ያለ ቅርርብ ማኅበራዊ የአኗኗር ዘዴዉን ነዉ»
«ኢትዮጵያ ዉስጥ ስኖር 23 ዓመቴ ነዉ። ግማሽ እድሜዬን ያሳለፍኩትም እዚሁ ነዉ። አሁን ግን አዛዉንቶቹ ቤተሰቦቼ ጋር መሆን ስለምፈልግ ወደ ሀገሬ ወደ ጀርመን መመለስ እፈልጋለሁ። ወዲህም ልጆቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በጀርመን እንዲያጠናቅቁ፤ በዛዉም የጀርመንን ባህል እንዲማሩ በጀርመን ያለዉን አኗኗርም እንዲተዋወቁ እፈልጋለሁ።» ያሉን ጀርመናዊትዋ ኮንስታንሰ ፕሪል ናቸዉ፤ ኮንስታንተ ፕሪል አጠር ባለ ስማቸዉ «ኮኒ» ሲባሉ ነዉ የሚታወቁት። በዚህ ዝግጅታችን አማርኛ ተናጋሪዋን ጀርመናዊት በእንግድነት ይዘናል።

Äthiopien Constanze Prehl
በጎአ 1999ዓ,ም ኮንስታንተ ፕሬል ከካርል ሃይንዝ በም ጋር በዓለም ከተማምስል Constanze Prehl


አማርኛ ቋንቋን የተማሩት በጀርመን በላይፕሲግ ከተማ ነዉ። በርግጥ አማርኛ ቋንቋ የየትሀገር ቋንቋ እንኳ እንደሆነ አያዉቁም ነበር ትምህርቱን ለመከታተል ዩንቨርስቲ ሲመዘገቡ። እንደ ኮኒ ወደዚህ ዩንቨርስቲ ያቀኑት የአፍሪቃ ጥናት «African Studies» ለመከታተል ነበር ። ከዚያም ቋንቋ መማር ስለነበረባቸዉ አማርኛን መማር ይፈልጋሉን ተብለዉ ሲጠየቁ፤ መልሳቸዉ አዎን ነበር። ስሞን ማን ልበል አልኳቸዉ፤ አይ አንቺ ብትይኝ እወዳለሁ ስላሉኝ በሃሳባቸዉ ተስማምቼ ቃለ-ምልልሳችን ጀመርን፤ በነገራችን ላይ በጀርመን ባህል ከ 15 ዓመት ጀምሮ ማንኛዉም ሰዉ በቅጡ የማይተዋወቅ ከሆነ በአንቱታ ነዉ ንግግር የሚለዋወጠዉ፤ የሰዉየዉ ፈቃድ ሆኖ አይ አንተ በለኝ አንቺ በለኝ ካልተባባለ በስተቀር፤
« ስሜ ኮንስታንሰ ፕሪል ይባላል በአጭሩ ኮኒ እባላለሁ። በኢትዮጵያ 23 ዓመት ነዉ የኖርኩት፤ ማለት ግማሽ ሕይወቴን ያሳለፍኩት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።»

ግማሽ ሕይወትሽን ኢትዮጵያ ነዉ ያሳለፍሽዉ፤ አማርኛ እንዴት ተማርሽ?
«አማርኛ የተማርኩት በዩንቨርስቲ ነዉ። በጀርመንዋ ከተማ በላይፕዚግ ዩንቨርስቲ ሁለት ኢትዮጵያዉያንና አንድ ጀርመናዊ ነበሩ አስተማሪዎቼ። ጥናቱን በአምስት ዓመት ነበር የጨረስኩት፤ የተማረኩት የአማርኛና የእንጊሊዘኛ አስተርጓሚ ሆኜ ነዉ። ትምህርቱ ከአፍሪቃ የቋንቋ ሳይንስ ጋር የተያያዘ ነበር። በዚህ ጥናቴ ላይ ለግማሽ ዓመት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ገብቼም ተምሪአለሁ» ማለት በኢትዮጵያ ቋንቋ ላይ ማለት በአማርኛ ቋንቋ ላይ ነዉ ጥናት ያደረግሽዉ የጻፍሽዉም?

Äthiopien Constanze Prehl
ምስል Constanze Prehl


«ጥናት ከመጀመሪ በፊት በላይፕዚግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃን የቋንቋ ሳይንስን መማር ፈልጌ ማመልከቻ ካስገባሁ በኋላ በዝያን ጊዜ የተሰጠኝን ፈተና አለፍኩ። ለተወሰነ ጥናት የአማርኛ የእንጊሊዘኛ አስተርጓሚ መማር ትፈልጊያለሽ ዉይ? ብለዉ ሲጠይቁኝ፤ አዎ! እሺ! አልኳቸዉ። በዝያን ጊዜ አማርኛ ቋንቋ ምን እንደነበር፤ የየት ሀገር ቋንቋ እንደነበረ እንኳ አላዉቅም።» «ስለኢትዮጵያ የማዉቀዉ ነገር አልነበረኝም ግን ትምህርቴን ጀመርኩ ፤ የኢትዮጵያ ቋንቋ አማርኛን ማጥናት ጀመርኩ» «ኦሮምኛ ከአንዳንድ ቃላት በስተቀር አልችልም ፤ አዝናለሁ። »


በኢትዮጵያ 23 ዓመት ኖረሻል? ጣልያናዊዉን ባለቤትሽን የተዋወቅሽዉም እዝያዉ ኢትዮጵያ እንደሆን አጫዉተሽኛል? እና ሁለቱም ልጆችሽ የተወለዱትም እዝያዉ ኢትዮጵያ ነዉ ማለት ነዉ?
«ልጆቼን የወለድኩት ከኢትዮጵያ ወደ ጀርመን ተመልሼ መጥቼ ነዉ። ቤተሰቦቼ ጋር ብሆን ይሻላል ጥሩ ነዉ ብዬ ነዉ፤ የተመለስኩት። ልጆቹ ሶስት ወር ከሞላቸዉ በኋላ ግን ወደ ኢትዮጵያ ይዤአቸዉ ሄጂ እዝያዉ ኑሮዬን ቀጠልኩ። ልጆቼ ወንዶች ናቸዉ። ትልቁ ልጄ 14 ዓመቱ ነዉ። ሁለተኛዉ ወንዱ ልጄ 12 ዓመት ሞልቶታል። እና እዚሁ ኢትዮጵያ ነዉ ያደጉት አራት ቋንቋዎችን አጣርተዉ መናገር ይችላሉ።»


ታድያ ለምን ኢትዮጵያን ትለቅያለሽ። አንቺን ያስተዋወቁኝ ሰዎች እንደነገሩኝ ኢትዮጵያን በጣም ትወዳለች ብለዉ ነዉ ታድያ ለምን ትሄጃለሽ? «ምን መሰለሽ አንዳንዴ በእድሜ የሀገር ናፍቆት ይመጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን አዛዉንቶቹን ወላጆቼን ማለት እናንትና አባቴ ጋር አብሪ መሆን እፈልጋለሁ። ልጆቼም ከፍተኛ ተቋም ለመግባት እንዲያስችላቸዉ በጀርመን ሀገር ጥሩ ትምህርትን ማግኘት ይችላሉ ብዬ በማሰብ ነዉ። ለዝያ ነዉ ወደ ትዉልድ ሀገሪ ወደ ጀርመን ለመመለስ የወሰንኩት። »
እና ታድያ አይከብድሽም? የእድሜሽን ግማሽ የኖርሽዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ፤ እንደገና ወደ ጀርመን መጥቶ አዲስ አካባቢ አዲስ መኖርያ ከነበረዉ የተለየ የኑሮ ዘዴና ባህል ዳግም መላመዱ አይከብድም?

Äthiopien Constanze Prehl
ኮንስታንተ ፕሬል ታሳትመዉ የነበረዉ «ኢትዮጵያዊት» መጽሔትምስል Constanze Prehl


«የኔ ግማሽ መንፈስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቀሪ ነዉ። ግማሹ መንፈሴ ብቻ ነዉ ወደ ጀርመን የሚመጣዉ ማለት ይቻላል። እና ኑሮን ጀርመን ዉስጥ እንደ አዲስ ነዉ የምጀምርዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ጀርመን የማላገኛቸዉን ነገሮች ስለለመድኩ ጀርመን ዉስጥ መኖር ስጀምር ሁሉን ነገር እንደ አዲስ መጀመር ይኖርብኛል፤ የሚከብደኝም ይመስለኛል። ቢሆንም ኑሮ እንደዚህ በመሆኑ፤ አንዳንዴ አዲስ ህይወት መጀመር መቀየር ጥሩ ነዉ። አሁን ወደ ጀርመን ብመለስም ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝን ግንኙነት አላቋርጥም። ስራ ለመስራት እቅድ አለኝ። ለምሳሌ በፊት ለሴቶች የማዘጋጅ የነበረዉ መጽሔት ወደፊትም እደገና ሌላ እትም ለማዉጣት ነዉ። መጽሔቱ ማንበብና መፃፍ ለሚጀመሩ ኢትዮጵያዉያ ሴቶች የሚሆን ነዉ።»
እንግዲህ ጀርመን ሀገር 23 ዓመት ኖረሻል፤ እና ይሄን ነገር ከኢትዮጵያ ይዤ ወደ ጀርመን ብሄድ ይጠቅመኛል የምትይዉ ነገር አለሽ?


« ወደ ሐገሪ ስመለስ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዉያን ይዤ የምሄደዉ የበማኅበረሰቡ የሚታየዉን ሞቅ ያለ ቅርርብ ማኅበራዊ የአኗኗር ዘዴዉን ነዉ» ሞቅ ያለዉን የማሕበራዊ ኑሮ ማለትሽ ነዉ! የኢትዮጵያን ምግብስ ትወጃለሽ?!
« ምግብ በጣም እወዳለሁ። እንጀራ በዶሮ ወጥ መብላት ለምጃለሁ። ጥብስም በጣም እወዳለሁ። የዶም በየአይነቱ የማዘወትረዉ የምወደዉ ምግቤ ነበር፤ እና የኢትዮጵያ ባህላዊ ነገሮችን በሚመለከት የገና በዓል የፋሲካ በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ዉስጥ በልዩ ሁኔታ ነዉ።» እና ልጆችሽ ከዚህ ባህል ጋር ተቆራኝተዋል እንጀራ ይወዳሉ?
« አዎ ይወዳሉ። እና ወደ ጀርመን መመለስ ለእነሱ አዲስ ነገር ነዉ። ከጀርመን ይልቅ የኢትዮጵያን ባህል ነዉ፤ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ያደጉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ ። በዚህም ምን ይገጥመናል የሚል ትንሽ የፍርሃት ስሜት ያላቸዉ ይመስለኛል»


መቼም የኢትዮጵያ ባህል አልባሳት ፤ የተለያዩ አይነት ምግቦችን እንደምትወጂ ነገርሽኝ ። በርካታ ባልንጀሮችም አፍርተሻል። ግን ነገር ባይሆiን ጥሩ ነበር ይህ አጉል ነገር ነዉ ደስ አይለኝም የምትይዉስ ነገር አለ?
« አዎ ይወዳሉ። እና ወደ ጀርመን መመለስ ለእነሱ አዲስ ነገር ነዉ። ከጀርመን ይልቅ የኢትዮጵያን ባህል ነዉ፤ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ያደጉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ ። በዚህም ምን ይገጥመናል የሚል ትንሽ የፍርሃት ስሜት ያላቸዉ ይመስለኛል» በኢትዮጵያ በየትኛዉ አካባቢዎች ሄደሽ የሴቶች ግርዛት፤ በሕፃንነት ማግባት የመሳሰሉትን አጉል ልምዶችን አይተሻል? «እኔ በተለይ ሰዎች ለሰዎች በተባለዉ የግብረሰናይ ድርጅት 10 ዓመት ሰርቻለሁ። በድርጅት ዉስጥ የሴቶች ፕሮግራም አስተናባሪ ነበርኩ። ባህላዊ ልምዶችን በሚመለከት፤ ፕሮግራም አዘጋጅ ነበር። አንዳንድ መጥፎ ልምዶችም አሉ። ለምሳሌ የሴቶች መገረዝ በልጅነት ጋብቻ የመሳሰሉ በጣም መቀየር መቅረት ያለበት ጉዳይ ነዉ። ይህን ጉዳይ በሚመለከት መጽሔት ላይ መጻፍ ቃለ- መጠይቅ ምናምን በማድረግ በማሳወቅ እንዲቀየር እፈልጋለሁ። »

Äthiopien Constanze Prehl
ምስል Constanze Prehl


ትምህርትን ባህልን በተመለከተ ይምትነግሪኝ ሌላስ ነገር አለ? « ብዙ ክፍለ ሀገሮችን ተዘዋዉሪ አይቻለሁ ወደ ሰሜን ወደ ደቡብ ፤ ምስራቅ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሁሉ ሄጃለሁ። ለምሳሌ ወደ ኢሊባቡር ወደ ሰሜን ሸዋ በጣም የምወደዉ አካባቢ ነዉ። ወደ ትግራይ ወደ ሀረር አካባቢ፤ ማለት ሀረር ሸለቆ ሁሉ ነበርኩ። እዝያ እንሰራ ነበር። አካባቢ የግርዛት ችግር በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ይታይ ነበር። በሰሜን ሸዋ አካባቢ ደግሞ ከጋብቻ ጋር በተያያዙ ችግሮች በጣም ከፍተኛ ችግር ነበር። ጋብቻ የፈፀሙ የዘጠኝ የአስር ዓመት ልጆች ጋር ተገናኝቼም ነበር። ይህ ነገር ማየት ለኔ በጣም ከባድ ነበር። እነዚህ ህጻናት ኑሮአቸዉ እንዲቀየር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።»


በኢትዮጵያ ለ 23 ዓመታት የኖረችዉና በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ በሚገኘዉ ጀርመን ትምህርት ቤትና በኢትዮጵያ በሚገኙ ድርጅቶች ዉስጥ ካገለገለችዉ አማረኛ ተናጋሪ ጀርመናዊት ጋር ያደረግነዉ ቃለ ምልልሥ እስከዚሁ ነበር። ኮንስታንሰ ፕሪል በኢትዮጵያ የ 23 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ትዉልድ ሃገርዋ ተመልሳለች ፤ ያልምድሽ እያልን ፤ ሙሉ ቃለ- ምልልሱ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን መከታተል እንደሚችሉ እንገልፃለን።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ