በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባሕል ድግስ
«13ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባሕል ፌስቲቫል» በጀርመን ፍራንክፉርት ከተማ ተጠናቋል። በዝግጅቱ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።
ኢትዮ-ፍራንስ ቡድን፦ ከ14 ዓመት በታች
በፈረንሣይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ይኽ ቡድን ከ10 ዓመት እና ከ14 ዓመት በታች እንዲሁም የአዋቂዎች በሚል በሦስት የተከፋፈለ ነው። የፍራንክፉርቱን የስፖርት እና ባሕል ድግስ ካደመቁት ቡድኖች አንዱ ኢትዮ-ፍራንስ ይገኝበታል።
ዋንጫዎቹን ለማንሳት ፍልሚያው ከባድ ነበር
በአውሮጳ የሚገኙ 30 ቡድኖች የተጋበዙበት ይኽ የስፖርት ውድድር ሕፃናቱን ጨምሮ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል።
የወደፊት ተስፋዎች፦ ብቃታቸውን ለማሳየት ተሰልፈው
ጀርመንን ጨምሮ ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ከተሞች የተውጣጡ የሕፃናት እና የታዳጊዎች ቡድኖች በውድድሩ ተሳታፊ ነበሩ። አንዳንዶቹ በሚኖሩበት ከተማ በኮከብነት የተመረጡ ተጨዋቾች ይገኙባቸዋል። በሕፃናት እና ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ ለስኬት መሠረት መሆኑ ይታመንበታል።
የዋንጫው ባለቤት፦የኢትዮ ለንደን ቡድን
የኢትዮ ለንደን ቡድን ለእረፍት የወጣው በኢትዮ ኖርዌይ 1 ለ0 እየተመራ ነበር። አሠልጣኙ ተጨዋቾቹን ሲያበረታቱ። «ጠንክራችሁ ተጫወቱ፣ ብትሸነፉም ምንም አይደለም፣ ግን ጠንክራችሁ ተጫወቱ» በማለት በተደጋጋሚ ሲያበረታቷቸው ነበር። የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ እውነትም ማበረታቻው ሥራውን ሠርቷል።
ኢትዮ ለንደኖች አቻ የምታደርጋቸውን ግብ አስቆጥረው
በእርግጥም የአሠልጣኙ ምክር እጅግ ጠቃሚ ነበር። ኢትዮ ኖርዌዮች እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ነበሩ። አንድ ተቀያሪ ቦታ ላይ የተቀመጠ ተጨዋች «ማሸነፋችን አይቀርም» ሲል በእርግጠኝነት ተናግሮ ነበር። ሆኖም ኢትዮ ለንደኖች አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥረው የኢትዮ ኖርዌዮችን ሕልም አምክነዋል።
ግብ ተቆጠረ፦ ደጋፊዎች ቆመው ፈነጠዙ
ፉክክሩ ከባድ ነበር። ኢትዮ ለንደን እና ኢትዮ ኖርዌይ ቡድኖች አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተለያዩ። እናም በፍፁም ቅጣት ምት መለያ ተፋጠጡ። በፍፁም ቅጣት ምቱ መለያም ኢትዮ ለንደን ኢትዮ ኖርዌይን 6 ለ5 አሸንፏል። ዋንጫው ዘንድሮም ወደ ለንደን።
ዓሊ ረዲ በክብር እንግድነት
አረንጓዴ የለበሱት አቶ ግርማ ሣኅሌ በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባሕል ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት የክብር እንግዳው ዓሊ ረዲን ሲያስተዋውቁ። የሕፃናቱን እና የታዳጊዎችቹን ውድድር የከፈተው የክብር እንግዳው ዓሊ ረዲ ነበር። ዓሊ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የረዥም ጊዜ ግብ ጠባቂ እና የቡና ቡድን ተሰላፊ ነበረ ። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ነው።
ታዳሚያን በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ሲከታተሉ
ከአውሮጳ፣ ከአሜሪካ እና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከአምስት ሺህ ያላነሰ ታዳሚ በድግሱ ላይ እንደተገኘ ተገልጧል። ታዳሚያኑ ወደ ስታዲየሙ የገቡት ለዓርብ እና ለቅዳሜ መግቢያ 5 ዩሮ ከፍለው ነበር። አንዳንዶች መግቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠየቁ ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር።
ታዳሚያኑ ውድድሩን በንቃት ሲከታተሉ
ከታዳሚያኑ መካከል አንዳንዶች ከረቡዕ አንስቶ እስከ ቅዳሜ ከስታድየም አልተለዩም። ብዙዎች ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ነበር የመጡት።
ሕፃናት የፀሐዩን ንዳድ በውኃ ለመቋቋም ሲጥሩ
በወቅቱ ፍራንክፉርት እጅግ ሞቃት ነበረች። ሙቀቱ አዋቂዎች በየአጋጣሚው የተለያዩ መጠጦችን ደጋግመው ለመጠጣት ሲገፋፋቸው ነበር። ሕፃናቱ ደግሞ በሜዳው ዙሪያ ከተዘጋጁ ቧንቧዎች በሚፈልቅ ውኃ በሙቀት የነደደ ገላቸውን ለማቀዝቀዝ መጣራቸው አልቀረም።
የሙዚቃ ዝግጅት በዲጄ
በዲጄ የሙዚቃ ዝግጅት ታዳሚያኑ ሲዝናኑ። ስፖርታዊ ውድድሩ የጎላ ነበር። ሆኖም የባሕል ዝግጅቶች ብዙ ሊሠራባቸው ይገባል።
ከሜዳው በስተጀርባ የምግብ መሸጫ ዳሶች
ከፆም ምግብ አንስቶ እስከክትፎ ብሎም ጎረድ ጎረድ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች በነጫጮቹ ዳሶች ውስጥ ሲሸጡ ነበር። የምግብ ገበያው እጅግ የደራ ነበር ማለት ይቻላል።
የነገ ተስፋዎች ነገም በውድድር ለማሸነፍ ብቅ ይላሉ
የስፖርት እና የባሕል ድግሱ ብዙዎችን ከማገናኘቱም ባሻገር ሕፃናት እና ታዳጊዎችንም አሰባስቧል። የ10 ዓመቱ ብሩክ ሲሳይ ይኽ ድግስ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍራንክፉርት ከተማ ላይ ከተኪያሄደ ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው የተወለደው። የስፖርት እና የባሕል ድግሱ 13ኛ ዓመቱን ሲያስቆጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ ሆኖ ብቅ ብሏል። ምናልባት የዛሬ 13 አለያም 26 ዓመት ደግሞ ምን ይከሰት ይኾን?