1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዊ የሀገር ጎብኚዎች ሹፌር ተገድሏል

ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 2009

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የሄዱ 10 አውሮጳውያን ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ኢትዮጵያዊ ሹፌር ሲገደል አንዲት ጎብኚ መቁሰሏ ተነገረ፡፡ ሚዛን ተፈሪ ከተማ አቅራቢያ እንደተፈጸመ በተነገረለት በዚህ ጥቃት የጎብኚዎቹ ንብረትም ተዘርፏል፡፡ ከጎብኚዎቹ ውስጥ ስድስቱ የስሎቫክ ተወላጅ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የቼክ ሪፐብሊክ ዜጎች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/2SkDj
Äthiopien Omo Fluss Tal Landschaft
ምስል JENNY VAUGHAN/AFP/GettyImages

European Tourists Attacked in Ethiiopia FINAL - MP3-Stereo

ስድስት ስሎቫኮችን እና አራት የቼክ ሪፐብሊክ ተወላጆች የነበሩበት የጎብኚዎች ቡድን ጥቃቱ የደረሰበት ባለፈው ሳምንት ሰኞ ነበር፡፡ ጎብኚዎቹ በአራት ላንድ ክሩዘር መኪኖች ሆነው ወደ ደቡብ ክልል ሲጓዙ ሱርማ ወረዳ ላይ ነበር ጥቃት የደረሰባቸው፡፡ በጥቃቱ  ለምለሟ ሀገሬ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ለተባለ ድርጅት ይሰራ የነበረ ኢትዮጵያዊ ሹፌር ሲገደል አንዲት የስሎቫክ ጎብኚ ቆስለዋል፡፡ 

መቀመጫውን በስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራቲስላቫ ያደረገው  የጉዞ ወኪል ዋና ዳይሬክተር ሎቦሾ ፌልነር ጥቃቱ የተፈጸመው ጎብኚዎቹ በሚዛን ተፈሪ የነበራቸውን የምሳ ቆይታ አጠናቅቀው ወደ ሱርማ ወረዳ በገቡበት ወቅት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ከተጓዦቹ ያገኙትን መረጃ ተንተርሰው ጥቃቱን ያደረሱት የሱርማ የጎሳ አባላት እንደሆነ ይወነጅላሉ፡፡

“ከምሳ በኋላ ወደ ሱርማ ጎሳዎች ነበር የሄዱት፡፡ ጠመንጃ የታጠቁ የተወሰኑ ሱርማዎች ከጫካ ወጡና አስቆሟቸው፡፡ ከዚያም ዘረፏቸው፡፡ ከመካከላቸው ወጣቱ ሁለት ደንበኞቼ ወደነበሩበት የመጀመሪያ መኪና ድንጋይ መወርወር ጀመረ፡፡ አንዷን ዶክተር ጭንቅላቷን በድንጋይ መታት፡፡ ከዚያ በኋላ አንደኛው ሹፌር ከመኪናው ሲወርድ በጥይት ተመታ፡፡ ከዶክተሮቹ አንዷ እንደነገረችኝ ወዲያውኑ በጥይት ወደተመታው ሹፌር ስትሄድ ሜዳ ላይ ተዘርግቶ እና በደም ተሸፍኖ ነበር፡፡ ወዲያውኑ ህይወቱ ያለፈች ይመስላል፡፡” 

እንደ የጉዞ ወኪሉ አባባል ከሆነ በድንጋይ የተመታችው ሶሎቫካዊት ያጋጠማት ቀላል ጉዳት በመሆኑ በኢትዮጵያ ባለ ሆስፒታል ውስጥ መቆየት አላስፈለጋትም፡፡ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ እና ሶስት ዶክተሮች የተካተቱበት የጎብኚዎች ቡድን ከጥቃቱ በኋላ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን በማምጣት ወደ ኦስትሪያ ቬይና እንዲበረርሩ ተደርጓል፡፡ 

በቼክ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ የሆኑት ኢሪና ቫላንቶቫ በጉዞ ወኪሉ የተገለጸውን የጥቃቱን ዝርዝር ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል፡፡ በጎብኚዎች ቡድን ውስጥ የነበሩ የቼክ ተወላጆች ውስጥ የተጎዳ ባለመኖሩ ዜጎቻቸው ጉዳዩን በአዲስ አበባ ለሚገኘው ኤምባሲያቸው እንኳ አለማሳወቃቸውን እና የጉዳቱን ዝርዝር መረጃ ያገኙት በአዲስ አበባ ከሚገኘው የስሎቫኪያ ኤምባሲ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቡድኙ ውስጥ የነበሩ የቼክ ተወላጆች በሙሉ ወደ ሀገራቸው በሰላም ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ 

Omo Dam Projekt in Äthiopien
ምስል Survival International

ጥቃቱን የፈጸሙት ስድስት የታጠቁ ግለሰቦች እንደሆነ የሚያስረዱት ቃል አቃባይዋ ጉዳዩ ተራ ዝርፊያ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ፡፡ 

“ስድስት ዘራፊዎች የነበሩበት ቡድን ከጎብኚዎቹ ገንዘብ እና የክሬዲት ካርድ ወስደውባቸዋል፡፡ ምናልባትም ጎብኚዎቹ የያዟዋቸውን ዋጋ የሚያወጡ ነገሮች መዝረፍ አስበው ይሆናል፡፡ ገንዝብ እና ክሬዲት ካርድ በእጃቸው ነበር፡፡ የዝርፊያው ዋና ዓላማ ምን ነበር የሚለውን ግን በመላምት መናገር አንፈልግም፡፡” 

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች አራት እንደሆኑ እና ሽፍቶች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው በጥቃቱ የኢትዮጵያ ሹፌር መገደሉን ይቀበላሉ ሆኖም መንስኤው ከዝርፊያ የዘለለ አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ከጎብኚዎቹ ላይ ገንዝብ እና እቃ መወሰዱን ነው፡፡ እስካሁንም ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች የሱርማ ጎሳ አባላት ለመሆናቸው መረጃ አለመገኙትንም ያስረዳሉ፡፡  

“በአካባቢው ላይ የነበሩ ሽፍቶች ናቸው ነው የሚባለው፡፡ ሹፌሩ ሞቷል፡፡ ሬሳውም ለምርመራ ወደ [አዲስ አበባ] መጥቷል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ደርሶ ሰዎችን አረጋጋቸው፡፡ ይህንን ተግባር ያደረጉትን ሰዎች ለመያዝ ፍለጋው እንደቀጠለ ነው ያለው፡፡ አካባቢው የሱርማዎች መኖሪያ ነው፡፡ ሱርማዎች ሊሆኑ ይችላሉ ሌላም ሊሆን ይችላል፡፡ ባልተያዙበት ጉዳይ ላይ ይሄ ነው ብሎ መናገር የሚከብድ ይመስለኛል፡፡”

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች እንዲሰርዙ አልያም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲወስዱ ማስጠንቀቂያ ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡ ቼክ ሪፐብሊክም ከሁለት ሳምንት በፊት ተመሳሳይ መልዕክት ለዜጎቿ አስተላልፋለች፡፡ ሀገሪቱ ያለፈውን ሳምንት ጥቃት ተከትሎ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ እንደማታወጣ የቼክ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡ አሁን ያለው በራሱ “ጥብቅ ማስጠንቀቂያ” ነው ይላሉ የመስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ፡፡  
 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ