1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሉዋቲ ቤራዎ የአንጎላ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ

Eshete Bekeleዓርብ፣ መስከረም 6 2009

በእሥር ላይ ለ36 ቀናት ያካሔደው የረሐብ አድማ ሉዋቲ ቤራዎ በአንጎላ ለእሥር ከታደረጉ 17 የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች መካከል ዝነኛ አድርጎታል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ግድም በምህረት የተፈታው ወጣት የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ግን ለዶይቼ ቬለ በአንጎላ ነፃነት እንደማይሰማው ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/1K3ql
Afrika Luaty Beirao Rapper und Aktivist in Angola
ምስል Privat

''በአንጎላ ማንም ነፃ አይደለም'' ሉዋቲ ቤራዎ

ሉዋቲ ቤራዎ ከሌሎች አስራ ስድስት የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ጋር ከአንድ አመት በላይ በአንጎላ በእሥር አሳልፏል። አስራ ሰባቱ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ለእሥር የተዳረጉት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመገልበጥ አሲረዋል በሚል ተጠርጥረው ነበር። እነርሱ ግን የአሜሪካዊውን የፖለቲካ ሳይንቲስት ጌኔ ሻርፕ አምባገነናዊ ሥርዓተ-መንግስት በነገሰባቸው አገራት ትጥቅ አልባት ትግል እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል የሚል መፅሐፍ ብቻ ነበር ያነበቡት።
የአንጎላው ፕሬዝዳንት ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ በሰጡት ምህረት ሉዋቲ ቤራዎ ካለፈው ሰኔ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ነፃ ነው። ከዳጎ ኒቬል በሥተቀር ሁሉም የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ከእሥር ተለቀዋል። ሁሉም አንጎላን ለቀው መውጣት ከመከልከላቸውም ባሻገር በወር አንድ ጊዜ ከፍርድ ቤት መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ሉዋቲ ቤራዎ የተወለደው እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1981 ዓ.ም. ከአንጎላ የተማሩ ቤተሰቦች በሉዋንዳ ነበር። አባቱ ጆዓ ቤራዎ የገዢው የአንጎላ ነፃ አውጪ ንቅናቄ (MPLA) አባል እና የፕሬዝዳንት ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ የግል ፋውንዴሽን ኃላፊ ነበሩ። የአንጎላ እና የፖርቱጋል ጥምር ዜግነት ያለው ሉዋቲ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ከእሥር በኋላ በሚኖርባት አገሩ ነፃነት እንደማይሰማው ተናግሯል።
«በፍፁም! ከመታሰሬ በፊትም ነፃነት አይሰማኝም ነበር። በዚህች አገር ማንም ሰው ነፃ አይደለም። እዚህ ሰዎች የሚኖሩት በፍርኃት ውስጥ ነው። እና ፍርኃት የሚሰማው ሰው ነፃ አይደለም። ይህ በእኔ እና የሰብዓዊ መብት አራማጅ ጓደኞቼ ላይ በተጨባጭ ይታያል። በፍፁም ነፃነት አይሰማኝም። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደልቤ መዘዋወር በቻልኩ ነበር።»
ባለፈው ነሐሴ ወር የምህረት አዋጁ ሥራ ላይ ውሏል። በጉዳዩ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
«በራሴ እና በሌሎችም ላይ እንዳስተዋልኩት ምህረት ትልቅ ትርጉም የለውም። ጉዳዩ ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ ጥፋተኛ አለመሆናችን ሊከበር ይገባ ነበር። የተፈጠረው ነገር ግን ይህ አይደለም። በስልጣን ላይ ያለውም መንግስት ይግባኝ ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም። ላላጠፋንው ጥፋት በሚሰጥ ምህረት ላይ በፍፁም አልስማማም። ስለዚህ በፍጹም ይቅርታ አልፈልግም። ምህረቱን ውድቅ የሚቻልበት መንገድ ካለ ያንን ለማድረግ እሞክራለሁ። አስቸጋሪም እንኳ ቢሆን! ምህረት አልፈልግም። ችሎቱ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ። እስከ መጨረሻው የአንጎላ የፍትኅ አካል! ተቋሞቻችን ምን ያክል ጠንካራ እንደሆኑ መፈተሽ እፈልጋለሁ። ለነገሩ ተቋሞቻችን እጅጉን ደካማ እና በሥራ አስፈጻሚው ላይ ጥገኛ የሆኑ ናቸው። ተቋሞቻችን ለዴሞክራሲ እና በሕግ የበላይነት ለሚመራ መንግስት የሚመጥኑም አይደሉም። እኛ ደግሞ ያንን ነው መመስረት የምንሻው። ዴሞክራሲያዊ እና በሕግ የበላይነት የሚመራ አገር!»
Angola befreite Aktivisten - Luaty Beirão
ምስል DW/P. Borralho
እና ችሎቱ እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል ትሻለህ?
«አዎ! የሚከፈለው ዋጋ ምንም ይሁን ምን እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል እፈልጋለሁ። ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አፅድቆ የተበየነብኝን የአምስት አመት ከስድስት ወራት የእሥር ጊዜ ለማጠናቀቅ ወደ እሥር ቤት ለመመለስ ብገደድም እንኳ።»
የአንጎላ አጠቃላይ ምርጫ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ሊካሔድ እቅድ ተይዟል። የሰብዓዊ መብት አራማጆች ምን አቅደዋል?
«ብዙዎቻችን በምርጫው ሒደት አናምንበትም። ምርጫው በራሱ አምባገነንነት ለመደበቅ የሚደረግ ጥረት ነው ብለን እናስባለን። አምባገነኖች ምርጫን ለመሸነፍ አያካሂዱም። ይህንን በአንጎላ የ1992፤2008 እና 2012 ምርጫዎች ታዝበናል። ብዙዎቻችን የምርጫ ሒደቱ ግልፅ እና ተዓማኒ እንዳልሆኑ ይሰማናል። እኛ እንደ ዜጋ የምርጫ ማጭበርበሮቹን ለመቀነስ እና ለማጋለጥ እንዲሁም አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ኃሳቦች አሉን። ሌሎች አራማጆች በምርጫው ድምፅ ላለመስጠት እና ተዓቅቦ ለማድረግ ተስማምተዋል። ይህ ግን ሁላችንም ተግባራዊ የምናደርገው አይደለም።»
ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ ከጎርጎሮሳዊው 1979 ዓ.ም. ጀምሮ አንጎላን ላለፉት 36 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ሰውየው በተደጋጋሚ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ቃል ቢገቡም አንዱንም ተግባራዊ ማድረግ አልፈለጉም። አሁንም በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ.ም. ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ተናግረዋል። በተፈጥሮ ኃብት የበለጸገችው አንጎላ ዜጎች መካከል 70 በመቶው የቀን ገቢያቸው ከአንድ ዶላር ያነሰ ቢሆንም የኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ መንግስት ግን በሙሥና ይታማል። አንጎላውያንም በአንድ ሰው ለ36 ዓመታት በሚዘወረው ፖለቲካቸው የተሰላቹ ይመስላል። ሉዋቲን ጨምሮ። ሉዋቲ ግን አሁም አንድን የፖለቲካ ፓርቲ ለመቀላቀል ዝግጁ አይመስልም።
«ይህ የማይታሰብ ጥያቄ ነው። ፖለቲካ ፓርቲዎቹም አባላቸው እንድሆን መጠየቅ ስላቆሙ አቋሜን የተረዱት ይመስለኛል። ብዙም አሳስቦኝ አያውቅም። ወደ ፊትም እንደዚሁ የሚቀጥል ይመስለኛል።»
የራስህን የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት አስበህ ታውቃለህ?
«እንደዚያ አስቤ አላውቅም። ሰዎችም እንደዚያ እንዲያደርጉ ግፊት አሳድሬ አላውቅም። እኔ ሰዎች አምባገነንነትን ለመታገል የሚያምኑበትን ሒደት እንዲከተሉ ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ። እኔን መሰል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ወጣት አንጎላውያን ያንን የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት እናሳካዋለን ብለው ካመኑ አልቃወማቸውም። ነገር ግን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በጓደኞቼ አሊያም ወይም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስለተመሰረተ ብቻ ድጋፍ ስለማድረጌ ግን እርግጠኛ አይደለሁም።»
Angola Aktivisten Protest Central Angola 7311 Luaty Beirao
ምስል Central Angola 7311
እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ አትፈልግም ማለት ነው?
«ሙሉ በሙሉ አይሆንም ማለት አልችልም። ለጊዜው ግን የእኔ የማይታመን ኃሳብ ነው።»
የአንጎላ ተቃዋሚዎችን ሥራ እንዴት ትገመግመዋለህ?
«በመጀመሪያ የአንጎላ ሙሉ ነፃነት አብሔራዊ ኅብረት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትልቁን መሳሪያ የጨበጠ በመሆኑ ትኩረት ልናደርግበት ይገባል። ይሁንና የአባላቱን እና ተከታዮቹን እምቅ አቅም ከመጠቀም አኳያ የሰራው ነገር በጣም ትንሽ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ በጣም ደካማ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነው ያለን።»
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ለየት ያለ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር?
«አገዛዙ ነፃ ሊሆን የሚገባውን ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን በቁጥጥሩ ስር አድርጎታል። አገዛዙ የምርጫ ሒደቱ እንዴት ሊከወን እንደሚገባ ይወስናል። ተቃዋሚዎች ደግሞ እያማረሩ መግለጫ ያወጣሉ። ይህ ለእኔ በፍፁም በቂ አይደለም።»
ወደ አንጎላ የሲቪክ ማሕበረሰብ እንመለስ። ከማሕበረሰቡ ምን ትጠብቃለህ?
«ብዙ ነገር አልጠብቅም። ምክንያቱም ስያሜውን የሚመጥን የሲቪክ ማሕበረሰብ አለን ብዬ አላስብም። መልካም ፈቃድ ያላቸው ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ግለሰቦች አሉ። ይሁንና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ከሚችሉበት ቦታ ላይ አይደለም ያሉት። የሲቪክ ማሕረሰባችን ትብብር የለውም። ያ ደግሞ በቂ አይደለም። ይሁንና ከሲቪክ ማሕበረሰቡ ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው መንግስትን የሚቃወሙ ግለሰቦችን ብተች እመርጣለሁ።»
ክሪስቲያነ ቬይራ ቴሼራ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ