1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዋሚዎች «አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም» ብለዋል

ዓርብ፣ ኅዳር 1 2010

በተቃውሞ ላይ የሰነበቱት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአረርቲ ከተማ ነዋሪዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ዛሬ ተነጋግረዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ከህዝቡ የተውጣጣ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከስምምነት ላይ ቢደርሱም ለችግሮቻቸው አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2nQya
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ተቃዋሚዎች «አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም» ብለዋል

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ መቀመጫ የሆነችው የአረርቲ ከተማ ካለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 28 ጀምሮ መረጋጋት ርቋታል፡፡ በከተማይቱ ለሁለት ሳምንት የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች እስካሁንም ከብርሃን ጋር ሳይገናኙ በጨለማ የተዋጡ ምሽቶችን እየገፉ ነው፡፡ በመብራት መጥፋት ሰበብ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች ታክለውበት ፋብሪካ እስከማቃጠል የደረሰ ጥፋት አስከትሏል፡፡

ከመብራት አገልግሎት፣ ከዘይትና ስኳር አቅርቦት፣ ከግብር አከፋፋል፣ ከወጣቶች ስራ ዕድል እና ከኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በተቃውሟቸው ላይ ያነሱት ነዋሪዎች ዛሬ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ሲነጋገሩ ውለዋል፡፡ በፊታውራሪ ጌታብቻ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሰባሰቡት ነዋሪዎች ከቀኑ አራት ሰዓት ጀምሮ ለአምስት ሰዓታት ያህል የቆየ ውይይት ከባለስልጣናቱ ጋር ማካሄዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ 

Licht Lampen
ምስል picture-alliance / Helga Lade Fotoagentur GmbH, Ger

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የከተማዋ ነዋሪ በስብሰባው ላይ የተነሱ የነዋሪዎች ጥያቄዎችን ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል፡፡ “ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ይበልጥ ደግሞ ይህን ግጭት ያስነሳው የመብራት ጉዳይ ስለነበረ መብራት በተከታታ 13 ቀን ጠፍቶ ህዝቡ ሰልፍ በወጣበት አጋጣሚ እያለ መንገድ ላይ እያለ ነበር መብራት የመጣው፡፡ የጀመሩትን ስራ ሳይጨርሱ መልሶ ተቋረጠ መብራት፡፡ ከዚያ በኋላ በማግስቱ ጠዋትም ሊመጣ ስላልቻለ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ‘እንዴት እንታለላለን’ በሚል ነበረ ቁጣውን ሲያሰማ የነበረው፡፡ ይሄ ነው ይበልጥ ገዝፎ የወጣው ጥያቄ፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ የስኳር እና የዘይት ጉዳይ ነው፡፡ በስኳር እና ዘይት እዚህ የገዘፈ በሚባል መልኩ ችግር ስላለ ህዝቡ አምርሮ ሲናገር የነበረው በዚህ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የተነሱት ደግሞ ለወጣቱ ታስቦ የተገዙ ትራክተሮች ነበሩ፡፡ እነርሱን ትራክተሮች ጎማጣ ጣቢያ የሚባል ግቢ ውስጥ ቆመው እየበሰበሱ ነው ያሉት፡፡ ወጣቱን ተጠቃሚ ካላደረጉ ለምንድነው የሚለው ሌላው ጎልቶ የወጣው ጥያቄ ነበር፡፡ በተጨማሪነትም ለቻይናዎች የተሰጠው የኢንዱስትሪ ዞን መሬት ከገበሬው ላይ ሲወሰድ በካሬ ሜትር ካሳ ሲሰጥ የነበረው 49 ብር ገደማ ነበር፡፡ ያ ነገር ግን ህዝቡ አልተዋጠለትም ነበር፡፡ ከአንድ ጥማድ ላይ ከእያንዳንዱ አርሶ አደር ላይ ቢያንስ 56 ሺህ ብር ተወስዶበታል፡፡ ይህ ብር የት ነው ያለው? የሚለው ላይ ‘በቀጣይ ሌሎች ስብሰባዎችን እያደረግን፣ ብሩም የት እንደገባ ከህዝቡ ጋር የምናጣራ ይሆናል’ ብለው ነው ዛሬ ወደማጠናቀቂያ የተደረሰበት፡፡”     

ሌላ የከተማይቱ ነዋሪ ከእነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ በነጋዴዎች ላይ አላግባብ ተጭኗል በተባለው ግብር ላይ የተቃውሞ ድምጾች መሰማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ስብሰባውን ሲመሩ የነበሩት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ እና ሌሎች የአካባቢው ባለስልጣናት ለነዋሪዎቹ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸውን የስብሰባው ታዳሚዎች ገልጸዋል፡፡ ባለስልጣናቱ በችግሮቹ ላይ ተከታታይ ውይይት ለማካሄድ ቃል መግባታቸውን እና ከህዝቡ የተውጣጣ 20 አባላት ያሉበት መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

ላለፉት ሶስት ቀናት እንቅስቃሴ ቆሙባት የነበረችው የአረርቲ ዛሬ በአንጻራዊነት መረጋጋት እንደሰፈነባት ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ወደ ከተማይቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ ኃይሎች መግባታቸውን ተከትሎ አሁንም ውጥረት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አባላት በከተማው አስተዳደር ጽህፈት ቤት መስፈራቸውን እና የክልሉ ልዩ ኃይል ደግሞ በብአዴን ጽህፈት ቤት እንዳሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ 

የአረርቲው ነዋሪ ዛሬ በከተማይቱ የነበረውን ድባብ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ “ምንም የተከፈተ ነገር የለም፡፡ መስሪያ ቤቶች  አልተከፈቱም፡፡ ሆቴሎችም ተከፍተው አይታዩም፡፡ ባጃጆችም አንዳንዶች ብቻ ናቸው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ ፀጥ ያለ ድባብ ነው ያለው፡፡  በተለይ ልዩ ኃይሎች በብዛት ነው ያሉት፡፡ የተወሰኑ ፌደራል ፖሊሶችም አሉ፡፡ የፌደራሉ ፖሊሶቹ ወጥተው አይታዩም፡፡ አንዳንዴ ምግብ ወደተዘጋጀበት ቦታ ሲሄዱ ብቻ ነው የሚታዩት፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይሎች ግን በግልጽ ይታያሉ፡፡ ወዲያ እና ወዲህ ይንቀሳቀሳሉ፡፡”  ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የከተማው ነዋሪ ከዛሬው ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ አንዳንድ ሱቆች መከፈታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ጥቅምት 29 በከተማው በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ሱቆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ በከተማይቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ መኪኖች መስታወቶች እንደተሰባበሩም ገልጸዋል፡፡ በፓርኩ ያለ አንድ ጄኔሬተርም መቃጠሉ ተነግሯል፡፡

Zucker
ምስል bit24 - Fotolia

የአማራ ክልላዊ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዳስታወቁት በዕለቱ በነበረው ተቃውሞ በ70 ሚሊዮን ብር የተቋቋመ እና ባለፈው ዓመት ስራውን የጀመረ የችቡድ ፋብሪካ “የቃጠሎ እና የንብረት ውድመት” ደርሶበታል፡፡ በጊዜው ሁለት ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳቱ የደረሰው በፋብሪካው ጠባቂዎች በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡

የአረርቲው ነዋሪ ህዝቡ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ተመሳሳይ ተቃውሞች ይቀጥላሉ ባይ ናቸው፡፡ “ዛሬ ከክልል ተወካዮች፣ ከዞኑ አስተዳደሮች መጥተዋል፡፡ ወጣቱ በመድረክ ላይ፣ እነርሱ ፊትም ቃል ገብቶ ነው የተለያየው፡፡ ይሄ ችግር ካልተፈታ እስከሞት ፍጻሜ ድረስ ህይወታችንን እንሰጣለን እያለ ነው ወጣቱ፡፡”   

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ