1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኒዠር ደለል የቀጠለው ሁከት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 9 1996
https://p.dw.com/p/E0lC

ናይጀሪያ ውስጥ በነዳጅ ዘይት ሀብት በታደለው በኒዠር ደለል ክፍለ ሀገር ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ የቀጠለው ሁከት ባካባቢው አዲስ ምርጫ ካልተደረገ በስተቀር እየተባባሰ ሊሄድና ወደለየለት ጦርነት ሊቀየር የሚችልበት ሥጋት መኖሩን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሒውማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ያወጣው ዘገባ አስታውቋል። በውዝግቡ እስካሁን በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎቹ የሚገመቱም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የዎሪ ውዝግብና የቀሰቀሰው ሁከት የሚል መጠሪያ የያዘው ባለ ሀያ ዘጠኝ ገፁ ዘገባ እንዳስታወቀው፡ ምንም እንኳን ለውዝግቡ የግልና የተቀናቃኝ ጎሣዎች ሚሊሺያ ጦር ተጠያቂ ቢሆኑም፡ በርካታ ሲቭል ሕዝብም በመንግሥቱ ፀጥታ ኃይላት ተገድሎዋል። የኒዠር ደለል ሕዝብ በናይጀሪያ የተፈጥሮ ሀብት ምንጭ በሆነው አካባቢ በመኖሩ ብቻ ብዙ ሥቃይ ደርሶበታል። በሲቭሉ ሕዝብ ላይ ግን ወንጀል የፈፀሙት ወገኖች እስካሁን ድረስ ለፍርድ የሚቀርቡበት አንዳችም ዕድል አልታየም።
ደም አፋሳሹ ግጭት ባካባቢው ነዋሪና በጠቅላላ በናይጀሪያ ላይ ግዙፍ ክስረት አድርሶዋል። ናይጀሪያ ወደ ውጭ በንግድ ከምትልከው ምርትዋ ከምታገኘው ገቢ መካከል ከዘጠና ከመቶውን በላይ የሚሸፍነው አርባ ከመቶው የነዳጅ ዘይት ምርትዋ የሚያልፈው በዚሁ አካባቢ ባለው የዋሪ ወደብ በኩል ነው፤ ይሁንና፡ ይኸው ወደብ ባካባቢው በቀጠለው ግጭት የተነሣ ባለፈው ዓመት ብቻ በተደጋጋሚ መዘጋት ግድ ነበር የሆነበት። ነዳጅ ዘይቱ ወደ ወደቡ የሚያልፍባቸው ቧምቧዎች እየተቀደዱና ነዳጅ ዘይቱ እየተሰረቀ በሚሸጥበት ሕገ ወጡ ድርጊት የናይጀሪያ መንግሥት በያመቱ ከሰባት መቶ ሀምሣ ሚልዮን እስከ አንድ ነጥብ አምሥት ሚልያርድ ዩኤስ ዶላር ክስረት ይደርስበታል።

በኒዠር ደለል የሚታየው ግጭት የጎሣና የፖለቲካ ምክንያቶች እንዳሉት ቢታወቅም፡ ከነዳጅ ዘይቱ ምርት ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለመቆጣጠር በተለያዩ ቡድናትና በመንግሥቱ መካከል የሚደረገው ፉክክር ለውዝግቡ መባባስ ተጠያቂ መሆኑን የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ፡ በዘገባው መሠረት፡ በኒዠር ደለል የሚፋለሙት ወገኖች በሦስት ጎሣዎች የተደራጁ ሲሆኑ፡ ጥቂት መቶ ሺህ ሕዝብ ያለውና ከዮሩባ ጎሣ ጋር የሚቀራረበው የኢትሴኬሪ ጎሣ፡ እንዲሁም፡ የኡርሆቦና ከአሥር ሚልዮን የሚበልጥ ሕዝብ ያለው የኢዣው ጎሣ በኒዠር ደለል ያለችዋን ትልቋን የዋሪ ከተማ እንደ ትውልድ ሀገራቸው አድርገው ይመለከታሉ። ያካባቢው እና የፌዴራዊው መንግሥት ጽሕፈት ቤቶች በሚገኝባት የዋሪ ከተማ የባለቤትነት ጥያቄ ሰበብ ንትርኩ የተጀመረው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሳይሆን ገና በቅኝ አገዛዙ ዘመን እንደነበር የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ አሳይቶዋል። እአአ በ 1991 ዓም የኒዠር ክፍለ ሀገር በተቋቋመበት ጊዜ፡ ምንም እንኳን የኢትሴኬሪ ጎሣ በአሀዝ ንዑስ ቢሆንም፡ ሐቀኛው ያካባቢ ጥንታዊ ነዋሪነቱ ተረጋግጦለታል፤ በዚህም የተነሣ የነፃ ትምህርት ዕድል ወይም አዳዲስ የሥራ ኮንትራቶች፡ ወዘተ በማግኘቱ ረገድ ከሌሎቹ ሁለት ያካባቢው ጎሣዎች የተሻለ ዕድል ያገኘበት አሠራር በጎሣዎቹ መካከል ቅሬታ ፈጥሮ፡ ከ 1997 ዓም ወዲህ የታየውን ሁከት ቀስቅሶዋል። የተቀናቃኞቹ ጎሣዎች ሚሊሺያዎችም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ያካባቢውን መንደሮች መዝረፍ፡ ነዋሪዎቹን መግደልና ማጉላላት ብቻ ሳይሆን፡ ብሶታቸው ተሰሚነት ያገኝላቸው ዘንድ ባካባቢው የሚሠሩትን የውጭ ሀገር ዜጎች የነዳጅ ዘይት አምራችና አጣሪ ኩባንያዎችን በመያዝ ሥራቸውን አስተጓጉለውባቸዋል። የናይጀሪያ መንግሥት ግጭቱን ለማብቃት ወይም ውጥረቱን ለማርገብ እስካሁን በቂ ጥረት አላደረገም በሚል የዘገባው አዘጋጂዎች ወቅሰዋል። በሀገሪቱ የሚገኘው የሼል ኩባንያ ይህን ችግር ማስወገድ ይቻል ዘንድ ናይጀሪያ በንግድ ወደ ውጭ የምትልከው ነዳጅ ዘይት በሕጋዊ መንገድ የወጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ተያይዞ እንዲቀርብ፡ እንዲሁም የመንግሥቱን ታማኝነት በማሻሻል ሕገ ወጡን የነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚያበቃበትን አሠራር የሚያመቻች ዕቅድ እንዲዘጋጅ ሀሳብ አቅርቦዋል። የፖለቲካ ታዛቢዎች ደግሞ፡ ዘገባው እንዳመለከተው፡ ችግሩ ያበቃ ዘንድ በዚሁ አካባቢ ተቀናቃኝ ጎሣዎች በጠቅላላ እኩል ውክልና የሚያገኙበት አዲስ ምክር ቤታዊ ምርጫ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል። ምክንያቱም፡ ባለፉት የፀደይ ወራት በዚሁ አካባቢ የተካሄደውና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የተጭበረበረ ነው ያሉት ምርጫ በኒዠር ደለል ለሚታየው ውጥረት መባባስ አንዱ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ።