በታንጋኒካ ሃይቅ አስገራሚዉ ጀልባ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2005ታሪኩ የሚጀምረዉ ከመጀመርያዉ ዓለም ጦርነት በፊት በጎ አቆጣጠር ከ1913 ዓ,ም በጀርመኑ ንጉስ ቪልሄልም ዘመን ጀምሮ በታንዛንያ ስለሚገኝ አንድ የጀርመን መርከብ መርከብ ነዉ። ይህ እስከዛሪ በታንጋኒካ ባህር ላይ የሚቀዝፈዉ የጀርመኑ መርከብ ከመቶ ዓመት በላይ እድሜን አስቆጥሮአል። የጀርመኖችን የቅኝ ግዛት ታሪክ ይዞ ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት ታሪክ ጽፎ፤ እድሜዉ ዛሪ ላለንበት በግሎባላይዜሽኑ ማለት ለአጥናፋዊዉ ትስስር ዘመን በቅቶ ዛሪም ከመቶ አመት በፊት እንደታሰበለት ተግባሩ በመካከለኛዉ አፍሪቃ በሚገኘዉ ሃይቅ ላይ ሰዎችን በመጓጓዝ ተግባሩን ቀጥሎአል።
ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ግዙፉ የፊልም ኢንዱስትሪ ሆሊዉድ ጀርመናዉያንን የእኩይ መንፈስ መገለጫዎች አድርጎ ያቀርባቸዋል ። በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1951 ዓ,ም የሆሊዉዶቹ የፊልም ተዋንያን ሃምፍሪ ቦጋርት እና ካትሪን ሄቡርን «AFRICAN QUEEN»በተሰኘዉ በታንጋኒካ ሃይቅ በተሰራው የተሳካ ፊልማቸው ላይ ባላጋራ ሆና የምትቀርበው፣ የጀግና ተጻራሪ ባህሪይ የተሰጣት ንግስት ሉዊዛ የተባለችው ናት ። በርግጥ ስሙ እንደሚያመለክተው የልዑላዊ ቤተሰብ አባል የሆነች ሴት ወይዘሮ አይደለችም ። እዚህ ላይ ስሙ የተሰጠው ለመርከብ ነዉ።
በፊልሙ ላይ የሚታዩት ሁለቱ ዋና ገጸ-ባህርያት ጥንዶች፤ መርከቢቱን ያሰምጧታል። በርግጥ ይህች የጀርመናዉያን መርከብ ከታንዛንያ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ይኖራት ይሆን?
በሆሊዉዱ ፊልም ላይ «AFRICAN QUEEN» የሚል ስያሜ የተሰጣት በታንጋኒካ ሃይቅ ላይ የምትገኘዉ ግዙፏ መርከብ በጎ,አ በ1913 ዓ,ም በሰሜናዊ ምስራቅ ጀርመን በኒደርዛክሰን ግዛት ኤምስ ላንድ አዉራጃዉስጥ በሚገኘዉ ፓፕንበርግ በተባለ ቦታ ነበር የተሰራችዉ። በጀርመኑ ንጉስ በዊልሄልም ዳግማዊ ትዕዛዝ የተሰራችዉ እና የቅኝ ግዛት ታሪክን የያዘችዉ ይህች መርከብ በዚያን ግዜ «ግራፍ ጎትዝን» Graf Götzen የሚል ስያሜ ተሰጥቶአት ነበር።
የጀርመኑ ንጉስ ዊልሄልም ዳግማዊ መርከቧ እንድትሰራ ያዘዘዉ በታንጋኒካ ሃይቅ ዳርቻ ከብሪታንያ እና ቤልጂየም ድንበር ለመለየት፤ የጀርመንን የቅኝ ግዛት ክልል አጉልቶ ለማሳየት ነበር። ጀርመናዉያኑ ተቀናቃኞቻቸዉን ብሪታንያዉያኑን እና ቤልጂጎችን በልጦ ለመገኘት ብቻ ሳይሆን የአካባቢዉን ነዋሪንም ቀልብ ለመሳብ አስበዉ ነበር ይህን መርከም ለመስራት የበቁት። መርከብዋ እንድትሰራ ታዞ ከተሰራች በኋላም Gustav Adolf Graf von Götzen የሚል የመሳፍንት ስም ተሰጥቶአታል። ጀርመናዊዉ Gustav Adolf Graf von Götzen በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1900 አመታት መጀመርያ በጀርመን ቅኝ ግዛት ስር የነበረዉ የምስራቅ አፍሪቃ አካባቢ ከንቲባ እንደነበር ተጠቅሷል። የአካባቢዉ ነዋሪዎች በ1905 እና 1907 ዓ,ም ፤ አሁንም በጎ አቆጣጠር ነዉ፤ ጀርመናዉያን ቅኝ ገዥዎችን በመቃወም «ማይ ማይ» የሚል አመጽ አስነስተዉ ባካሄዱት ትግል ብዙ ደም ፈሶ በጀርመኑ መስፍን ድል አድራጊነት አመጹ ተቀጭቷል ።
የጀርመኑ መስፍን አመጹን ካሸነፈ በኋላ አካባቢዉ እረጭ አለ፤ መርከቢቱም ከጦርነት መገልገያነት ወደ ሰዉ እና እቃ ማመላለሻነት ጥቅም ላይ ዋለች። ግን ይህች መርከብ በዝያን ዘመን ከተሰራችበት ከሰሜናዊ ምስራቅ ጀርመን ተነስታ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ወደሚገኘዉ ታንጋኒካ ሃይቅ እንዴት ለመድረስ ቻለች? በሰሜናዊ ምስራቅ ጀርመን ፑፕንበርግ ከተማ መርከቡዋ ከተገነባች በኋላ ታንጋኒካ ሃይቅ ለማድረስ ከባድ በመሆኑ እንደገና መርከቧ በመልክ መልክ ተቆራርጣ፤ በ5000 ሳጥን ታሽጋ በእቃ ማመላለሻ መርከብ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ አቅጣጫ የጀርመን ቅኝ ግዛት መዲና ወደ ነበረችዉ ወደ ዳሪሰላም ትላካለች። 1200 ቶን እንደሚመዝን የተነገረለት ቁርጥራጭ የመርከቢቱ ክፍል ከዳሪሰላም ከተማ ታንጋኒካ ሃይቅ 30 ኪሎ ሜትር እስኪ ቀረዉ ድረስ በባቡር ተጭኖ፤ ከዝያም ማመላለሻ ስለሌለ፤ በሰዉ ሸክም ሃይቁ ዳርቻ ድረስ ለመጋዝ መብቃቱ ተዘግቦአል።
በዝያን ግዜ ይህን የመርከብ ቁርጥራጭ ታንጋኒካ ሃይቅ ዳርቻ ላይ ሲገጣጥም የነበረዉ ጀርመናዊ ለቤተሰቦቹ በጻፈዉ ደብዳቤ «ስራዉ ጥሩ እየሄደልኝ ነዉ ጠንካራ የሆኑ 20 ህንዳዉያን እና 150 ጥቁር ሰራተኞች እያሰራሁ ነዉ፤ በርግጥ የመገጣጠሙን ስራ ስጀምር ደግሞ ተጨማሪ 100 ጥቁር ሰራተኞች ሳያስፈልገኝ አይቀርም» ሲል መጻፉ ተነግሮአል።
መርከቢቱ ተገጣጥማ ስታበቃ ታድያ አካባቢዉ ላይ በቅኝ ግዛት ሰፍረዉ የሚገኙት ብሪትናዉያን እና ቤልጂጎች በስራዉ ተደንቀዉ አይናቸዉን ማመን ነበር ያቃታቸዉ።
መርከቡ እንደተገጣጠመ የአንደኛዉ አለም ጦርነት በመቀስቀሱ በመስፍን ስም የምትጠራዉ መርከብ ማለት « ግራፍ ጎትዘን» ከብሪትኑ እና ቤልጂጎች ጋር መዋግያ የጥይት መከላከያ እና ፈንጂን አመላልሳለች። ይህ ታሪኳ ነዉ ታድያ ለሆሊዉዱ የፊልም ኢንዱስትሪ «AFRICAN QUEEN» በተሰኝ አዲስ ታሪክ በፊልም የተቀረጸላት። በርግጥ ፊልሙ የጀርመናዉያኑን ስራ አጉድፎ ያሳያል።
በጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር 1916 ዓ,ም ጦርነቱ በየብስ ላይ ተባብሶ በመቀጠሉ፤ ጀርመናዊዉ የመርከቢቱ ሰሪ፤ መርከቢቱ ጠላት እጅ ከምትወድቅ በማለት ታንጋኒካ ሃይቅ ዉስጥ እንድትሰምጥ አድርጓል።
«GRAF VON GOETZN» የሚለውን የአንድ ጀርመናዊ መስፍንን ስም ያነገበችዉ መርከብ ግን ሰምጣ አልቀረችም። የአንደኛዉ የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ቤልጂጎች መርከቢቱን ከሰመጠችበት አዉጥተዉ «ሊይምባ» የሚል ስም ሰጥተዉ ለስራ አሰማርዋት። ከአንዳንድ ግዜ ብልሽት በስተቀር ከመቶ አመት እድሜ በላይ ያስቆጠረችዉ በጀርመን የተሰራችዉ መርከብ፤ መጀመርያ ጀርመናዉያን ለሰዉ ማመላለሻነት እንዲሆን እንደሰሯት፣ አሁንም ከመቶ አመት በላይ በታንጋኒካ ሃይቅ 673 ኪሎ ሜትር ርዝመት እየቀዘፍች ሰዉ እና እቃን በማመላለስዋ ትታወቃለች።
የታንጋኒካ ሃይቅ በመካከለኛዉ አፍሪቃ የሚገኝ ረጅም ርዝመት ያለዉ ሲሆን በዓለማችን ከሚገኝ ሃይቆች መካከል በርዝመት ስድስተኛ በጥልቀት ደግሞ ሁለተኛ ነዉ።
አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ