1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢቦላ ታይቶአል መባሉ እና ማስተባበያው

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2007

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በኢትዮጵያ ሶስት የኢቦላ ተጠርጣሪ ህሙማን ተገኙ የሚል ደብዳቤ እየተሰራጨ ነው። የክልሉ ጤና ቢሮ ደብዳቤውን እንደማያውቀው የኢቦላ በሽታም በክልሉ አለመኖሩን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1Doqh
Symbolbild - Ebola Virus
ምስል picture-alliance/dpa

የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ክትትል እያደረገ መሆኑና በፍተሻው የኢቦላ ህመምተኞች አለመገኘታቸውን ገልጿል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ጥበቃ ቢሮ ስም ጥቅምት 4/2007 ተጽፎ ወጣ የተባለው ደብዳቤ ''የኢቦላ ቫይረስ ህሙማንን ይመለከታል'' የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። 'የቢሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ጥበቃ ቢሮ' የሚል ክብ ማህተም ያረፈበትና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ጥራት ቁጥጥር የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አየለ ጅራታ ስም የወጣው ደብዳቤ ፌስቡክን ጨምሮ የኢትዮጵያ ን ርዕሰ ጉዳዮች ይዘው በሚወጡ ድረ-ገጾች 'ሾልኮ የወጣው ደብዳቤ' በሚል ርዕስ በመዘዋወር ላይ ይገኛል።ለአሶሳ ሪፈራል ሆስፒታል እንደተጻፈ የሚገልጸው ይህ ደብዳቤ የቢሮው ጥምር የጤና ባለሙያዎች ቡድን በአሶሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ሶስት የኢቦላ ተጠርጣሪ ህሙማን መገኘታቸውን በስልክ ሪፖርት እንደተደረገ ያትታል። ''ህሙማኑን ለመርዳት የሚያስችል የህክምና ግብዓት በእጃችን ላይ የሌለ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ እና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በድን አካላቸው እንዲቃጠል እና እንዲቀበር ስንል በጥብቅ እናሳስባለን።'' በማለት ይህ ደብዳቤ ይደመደማል።

Karte Äthiopien englisch

የቢሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘካርያስ አዳሙ ስለ ደብዳቤው ተጠይቀው አናውቀውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገሮች ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍተሻ ያደርጋል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግስተዓብ ወልደ አረጋይ እስካሁን ባደረጉት ክትትል የኢቦላ ህመምኛ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ