1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡርኪና ፋሶ የልጆች ጉልበት ብዝበዛ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 5 2004

በወርቅ ፍለጋ ይስማራሉ ፤ በማያውቁት ቤት ውስጥ በበቤት ሠራተኝነት ያገለግላሉ ፤ ወይም ደግሞ በፋብሪካዎች ስጋጃዎችን ይሰራሉ ። የዓለም የሥራ ድርጅት እንደሚለው ከ215 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ከመካከላቸው 115 ሚሊዮኑ እጅግ አደገኛ በሆኑ

https://p.dw.com/p/15Cmy
ምስል Tdh | R. Rorandelli

በወርቅ ፍለጋ ይስማራሉ ፤ በማያውቁት ቤት ውስጥ በበቤት ሠራተኝነት ያገለግላሉ ፤ ወይም ደግሞ በፋብሪካዎች ስጋጃዎችን ይሰራሉ ። የዓለም የሥራ ድርጅት እንደሚለው ከ215 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ከመካከላቸው 115 ሚሊዮኑ እጅግ አደገኛ በሆኑ የሥራ መስኮች ተሰማርተው ጉልበታቸውን ይበዘበዛሉ ። እነዚህ ልጆች መፃፍም ሆነ ማንበብ አይችሉም ። ጨዋታ በነርሱ ዘንድ አይታወቅም ። ዛሪ በዓለም ዙሪያ ታስቦ የዋለውን ፀረ የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ቀን ምክንያት በማድረግ የዶቼቬለዎቹ ያያ ቡዳኒና ዲርክ ኮፕ ያዘጋጁትን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።

የ20 ዓመቷ ዜናቡ ኢልቡዱ ታላቅ እህት ናት ፤ በስጋ የሚዛመዷትን ሳይሆን በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ ሴቶች ልጆችን ቴር ዴዝ ኦም በተባለው ድርጅት እንደ ታላቅ እህት ትንከባከባቸዋለች ። ዜናቡ ችግራቸውን ታውቃለች ። እርሷው ራሷ ቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ ውስጥ ለ 7 ዓመታት የቤት ሠራተኛ ነበረች ። ሥራውን የጀመረችው የ 9 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር ።

Kinderarbeit in Goldminen in Burkina Faso
ምስል DW

«ጠዋት በ 11:00 ሰዓት ላይ ባለቤቷ ትቀሰቅሰኛለች።ለገበያ ገንዘብ ይሰጠኛል ። ከዚያም ምግብ ማብሰል አለብህ ። የሰራኽው ምግብ አባወራው ካልጣፈጠው ችግር አለ።ከዱላ ብታመልጥ እንኳን ስድብ አይቀርልህም ። ምሳ መብላት እንኳን ብዙውን ጊዜ አሰቸጋሪ ነው ። መኝታህ ኩሽና ውስጥ አለያም በተገኘው ወለል ላይ ነው የሚሆነው። »

በቡርኪናፋሶና በሌሎችም የአፍሪቃ ሃገራት የሚገኙ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆች የዜናቡ እጣ ነው የሚገጥማቸው ። አብዛኛዎቹ ሥራ መፈለግ ያለባቸው ከ 9 እስከ 14 ዓመት እድሜያቸው ጀምሮ ነው ። ቤት ውስጥ ገንዘብ ስለሌለ ብዙዎቹ ቤተሰባቸውን ጥለው ይወጣሉ ፤ አለያም ይሸጣሉ ። የሚሰሩት ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ ነው ። ልጆቹ እንደ ባሪያ ነው የሚቆጠሩት ፤ ይደበደባሉ ፤ ይደፈራሉም ።አሊማ ፎጎ 21 ዓመቷ ነው ለ6 ዓመታት የቤት ሠራተኛ ነበረች ። ሁል ጊዜ ከአባወራዎች የወሲብ ጥቃት ራስዋን መከላከል ነበረባት ።

« አባወራው ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ ባለቤቱ ቤት አለመኖርዋን ካወቀ ፣ ከርሱ ጋር ከተኛሁ በወሩ መጨረሻ ተጨማሪ ገንዘብ እከፍልሻለሁ ሲል ይገፋፋኛል ። »

Kinderarbeit in Goldminen in Burkina Faso
ምስል DW

ልጅ የቤት ሠራተኞች ተጨማሪ ገንዘብ ሊሰጣቸው ቀርቶ ወደ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ከደሞዛቸው ጥቂቱን ነው የሚያገኙት ወይም ጭርሱኑ አይሰጣቸውም ። አብዛኛዎቹ የሥራ ውልም ሆነ ማህበራዊ ጥቅማ ጥቅሞች የሏቸውም ። የችግሩን ስፋት ያጤነው የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ከተለያዩ ሃገር በቀልና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መፍትሄ ለመሻት እየሞከረ ነው ። የእንቅስቃሴው ትኩረትም ባርነትን ፣ የልጆች ሴተኛ አዳሪነትን ፣ የህጻናት ውትድርናንና ሌሎች አደገኛ ሥራዎችን ማስቀረት ነው ። በቡርኪናፋሶ የቴር ዴዝ ኦም ድርጅት ፕሮጀክት ሃላፊ ሄርማን ዙንግራና እንደተናገሩት ድርጅታቸው ሴቶች ልጆችን በተለያየ መንገድ እየረዳ ነው ።

« በአሁኑ ጊዜ 700 ልጃገረዶች በየመንደራቸው እንዲማሩ ያስቻለ መርሃ ግብር አለን ። በተጨማሪም 100 ሴቶች ልጆች የሙያ ሥልጠና የሚያገኙበት ፕሮጀክትም አለን ለምሳሌ ሴቶቹ በምግብ ቤቶችም ሆነ በትናንሽ የልብስ ስፊት ድርጅቶች ይሰራሉ ። ወደ 100 የሚጠጉት ደግሞ በሰሜን ምዕራቧ ከተማ ቱጋን የ 2ተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው ። »

Kinderarbeit in Goldminen in Burkina Faso
ምስል DW

ይህ ግን አባይን በጭልፋ እንደማለት ነው ። እንዳለመታደል ሆኖ የዓለም የሥራ ድርጅት በምህፃሩ ILO እንደሚለው በቡርኪና ፋሶ ከ 500 ሺህ በላይ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ሠራተኞች ጉልበት ይበዘበዛል ። ይህ ብዝበዛ የሚፈፀመው ደግሞ በቤት ውስጥ ሥራ ብቻ አይደለም ወደ ግምሽ ያህሉ በሃገሪቱ በሚገኙት ወደ 600 በሚጠጉ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ነው የሚሰሩት ።

አትሞ

ከነዚህ ማዕድን ማውጫዎች በአንዱ ውስጥ የምትሰራው የ 15 ዓመቷ የዜናቡ ዲፓማ እጆች በስብርባሪ ድንጋዮች ተሰነጣጥቀዋል ። « ሴቶች ድንጋይ ማመላለስና መፈረካከስ ነው ሥራችን ። አድካሚ ነው በጣማ አድካሚ ነው »

የዜናቡን አስተያየት እኩያዋ ሳዩባ ቦኖኩንጉም ይጋራል

«መደበኛ የሥራ ሰዓት የለም ። ጠዋት እንጀምራለን ከሰዓት እናርፋለን ከዚያ እስከ እኩለ ለሊት ይቀጥላል ።

ያያ ቡዳኒና ዲርክ ኮፕ

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ