በቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተላለፈው ብይን
ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2006ማስታወቂያ
ትናንት ቴላቪቭ ውስጥ ያስቻለው የእስራኤል ፍርድ ቤት በቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልሜርት ላይ የ6 ዓመት እስራትና የ290 ሺህ ዶላር ቅጣት በይኗል ። የ68 ዓመቱ ኦልሜርት ጉቦ በመቀበል በቀረቡባቸው በሁለት የክስ ጭብጦች ከ6 ሳምንታት በፊት የጥፋተኝነት ብይን ተላልፎባቸው ነበር ። ኦልሜርት ላይ ትናንት ውሳኔ የተላለፈው ለሁለት ዓመታት ከተካሄደ የፍርድ ሂደት በኋላ ነው ። ኦልሜርት 160 ሺህ ዶላር የሚደርስ ጉቦ ተቀብለዋል ሲል ፍርድ ቤቱ አስታውቋል ። ርሳቸው ግን ጉቦ አልተቀበልኩም ሲሉ ተከራክረዋል ። ብይኑንም ይግባኝ እንደሚሉ ጠበቆቻቸው አስታውቀዋል ። ይግባኑ በፍርዱ ላይ ለውጥ ካላስከተለ በስተቀር ኦልሜርት በጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 1 ፣ 2014 ዓመተ ምህረት ወህኒ ይወርዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ኦልሜርት በጉቦ ቅሌት እስር የተበየነባቸው የመጀመሪያው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ። ስለ ብይኑ የእስራኤል ሃይፋውን ወኪላችንን ግርማው አሻግሬን በስልክ አነጋግረናል ።
ግርማው አሻግሬ
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ