1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሊያ የስብአዊ መብት ጥያቄ

ረቡዕ፣ የካቲት 2 1997

አዲሱ የሶማሊያ መንግስት የሰብአዊ መብቶች መከበሩን ማረጋገጥ ካልቻለ በሶማሊያ ሰላም ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የፓለቲካ ተንታኝ አስጠነቀቁ።

https://p.dw.com/p/E0kR
እሁድ እለት መቋዲሾ የገቡትን አዲሱን የሶማሊያ ፓርላማ አፈጉባኤ አበባ ይዛ የምትጠብቅ ታዳጊ
እሁድ እለት መቋዲሾ የገቡትን አዲሱን የሶማሊያ ፓርላማ አፈጉባኤ አበባ ይዛ የምትጠብቅ ታዳጊምስል AP

ሶማሊያ ዜጎቿን በበታተነዉና መንግስትነቷን ባጠፋዉ የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ በነበረችበት ወቅት ስለተፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ የሚያጣራ ኮሚሽን ማቋቋም ማስፈለጉን የአገሪቱ መንግስት ቢያምንም ነፃ አካል ላይሆን ይችላል የሚል ቅሬታ የሚያሰሙ ወገኖች አሉ።
ከ15 አመት በላይ መንግስት አልባ ሆና የቆየችዉ ሶማሊያ የእርስ በርስ ግጭት ባስከተለዉ መዘዝ 370,000 ሶማሊያዉያን ከቤት ንብረታቸዉ ሲፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ለስደት ተዳርገዋል።
የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ጋኒም አልናጃር በሶማሊያ የሁለት ሳምንታት ቆይታ አድርገዉ ሲመለሱ በሰጡት መግለጫ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት የሰብአዊ መብቶችን መከበር መሰረት ካላደረገ በቀር ለመነጋገር የታሰበዉ ሁሉ የሚሳካ አይመስለኝም ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀኃፊ ኮፊ አናን የዛሬ አምስት አመት የሶማሊያን ጉዳይ እንዲከታተሉ የተሾሙት ጋኒም አልናጃር ወደ አገሪቱ ለጉብኝት ሲሄዱ ይህ አራተኛቸዉ ሲሆን ሃላፊነታቸዉ በሶማሊያ የሰብአዊ መብቶች አከባበር ሁኔታን ማጥናትና ለመንግስታቱ ድርጅት ግኝታቸዉን ማሳወቅ ነዉ።
በቆይታቸዉም ከሶማሊያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ሞሃመድ ጌዲ ጋር በአገሪቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የሚያጣራ ቡድን ስለማቋቋም፤ በአገሪቱ የወንጀል ችሎትና የጦር ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ አጣሪ ቡድን የመኖር አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዉ ነዉ የተመለሱት።
አገሪቱ የሰብአዊ መብቶችን መጣስ የሚያጠና ቡድንም ሆነ የጦር ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ አካል ቢያስፈልጋትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸዉ አልሸሸጉም።
በመሆኑም እንደ አልናጃር አገላለፅ ከሆነ የተባበሩት መንግስታት የተባለዉን ድጋፍ ለማድረግ ግፋ ቢል በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ማለትም እስከ መጪዉ ግንቦት ወይንም ሰኔ ድረስ ለማስተካከል ይችላል።
የዛሬ 15 አመት አምባ ገነኑ የሞሃመድ ዚያድ ባሬ መንግስት ከወደቀ ወዲህ ሶማሊያ ህግ አልባ በመሆን በርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣ ተፈፅሞባታል።
ለረጅም ጊዜያት በአገሪቱ የሰፈነዉ ስርዓተ አልበኝነት ባስከተለዉ ችግር የአገሪቱን የተለያዩ ክፍሎች ለመቆጣጠር በተደረገዉ የእርስ በርስ ፍጅት በርካቶች ህይታቸዉን አጥተዋል ሌሎቹም ለስደት ተዳርገዋል።
በጎሳዎች መካከል በነበረዉ ግጭት አስገድዶ መድፈርን እንደ አንድ የመቅጫ መንገድና ሰዎችን ለማሰቃየት ተጠቅመዉበታል።
ያም ሆኖ በሶማሊያ የሚገኙት የፓለቲካ ተንታኝ አህመድ ሞሃመድ የአጣሪ ኮሚሽኑ መቋቋሙን አስመልክተዉ እዉነተኛና ከጣልቃ ገብነት ነፃ የመሆኑ ነገር ጥያቄ እንደሚያስነሳ ይናገራሉ።
እንደሳቸዉ ገለፃ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ሚሊሻዎች ነበሩ አስገድዶ መድፈርን እንደጦር መሳሪያ የተጠቀሙት።
ይሄዉ የሚሊሻ አካል ነበር መሳሪያ ይዞ እንዳገኘ ህዝቡን በጅምላ ሲገድል የነበረዉ፤ ከዚህም በመነሳት በሶማሊያ የተፈፀመዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለማጣራት ለመመስረት ያተቀደዉ ኮሚሽን ነፃ አካልነቱ ያጠራጥራል ባይ ናቸዉ።
በተጨማሪም ሞሃመድ የሚሉት ይህን ጉዳይ እንዲያጣራ በሶማሊያ እንዲቋቋም የተፈለገዉን አካል መቋቋም የአገሪቱ መንግስት የተቀበለዉ ሌላዉን አለም ለማስደሰት እንጂ ነፃነቱን አምኖ አይደለም።
የሶማሊያ የሰላም ድርድር በመንግስታት የልማት ግንኙነት የበላይ ጠባቂነት መካሄድ የጀመረዉ ከሶስት አመት በፊት ኬንያ ላይ ነበር።
ባለፈዉ አመት ሶማሊያን ለአምስት አመታት በጊዜያዊነት የሚያስተዳድር ፓርላማ ሲቋቋም
አብዱላሂ ዩሱፍ አህመድ ናይሮቢ ላይ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነዉ ተመረጡ።
አዲሱ መንግስትም የሚቋቋመዉ የእዉነት ኮሚሽን ነፃ አካል እንዳይሆን የሚያደናቅፈዉ ወጥመድ እንደሚኖር አምኗል።
የፕሬዝዳንቱ የፕሬስ አገልግሎት ሃላፊ ዩሱፍ ባሪባሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሰብአዊ መብቶችን ለማጠናከር ተገቢ የሆኑ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የፓለቲካ ራዕይ መሆኑን ነዉ የተናገሩት።
ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ ያለዉ የደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ጊዜያዊዉ የሶማሊያ መንግስት በዋና ከተማዋ መቋዲሾ ገብቶ ከመስራት ይልቅ በናይሮቢ እንዲቆይ ተገዷል።
ከአዲሱ አስተዳደር የተዉጣጣ ቡድን ባሳለፍነዉ የሳምንት መጨረሻ ወደመቋዲሾ በመጓዝ በሶማሊያ ማረፊያ ያገኙ እንደሆን አጣርቶ ተመልሷል።
በባለስልጣናቱ መካከልም ወደቦታችን እንድንገባ የዉጪ ሰላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ ያድርግልን በሚለዉ ሃሳብ አለመባባት ተፈጥሯል።
እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ቡድን በርሃብና በጦርነት የተጎሳቆሉትን ሱማሊያዉያን ለመርዳት በስፍራዉ የነበረዉ።
ይህ ጦር በወቅቱ ተሰጥቶት የነበረዉ ሰፋ ያለ ስልጣን ከአካባቢ ሃላፊዎች ጋር ባስከተለዉ ግጭት እ.ኤ.አ. በ1993 ላይ አንድ የማሌዢያና 18 የአሜሪካን ወታደሮችን በሰአታት ጦርነት ህይወታቸዉን አሳጥቷል።