በርሊን ፤ ለግሪክ የሜርክልና የሳርኮዚ ጥሪ
ዓርብ፣ ሰኔ 10 2003ዛሬ በርሊን ውስጥ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ጋር በጉዳዩ ላይ የመከሩት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተቻለ ፍጥነት ለችግሩ መፍትሄ መሻት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ። ሜርክል ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጀርመንና ፈረንሳይ በመጪው የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ ላይ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ ያሳስባሉ ። ስለ መርሃግብሩ አስፈላጊነት ያወሱት ሜርክል የግሪክ መንግሥትና ተቃዋሚዎችም የበበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል ።
« ግሪክ አሁን ለምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አዲስ መርሀ ግብር ያስፈልገናል ። ይህ በአንድ በኩል ግሪክ ግዴታዋን መወጣቷን ይጠይቃል ። ትናንት በስልክ ከግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓፓንድርዮ ጋር እንደገና ተነጋግሬ ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግሪክ ሃላፊነቷን እንዴት እንደምትወጣ እርሳቸውም ይህን ተፈፃሚ ለማድረግ ና አገራቸውም ትክክለኛውን አቅጣጫ እንድትይዝ በምን ዓይነት መንገድ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለማወቅ ችያለሁ ። እዚህ ላይ ላስታውሰው የምፈልገው ታቃዋሚዎች የግሪኩን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢደግፉና አገሪቱ ቀናውን መንገድ እንድትከተል ለማብቃት ቢተባበሩ የሚበጅ ይሆናል። »
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚም እንደ ሜርክል ሁሉ መንግስታቸው የአዲሱ መርሀ ግብር ደጋፊ መሆኑን አስታውቀው የግሪክ መንግሥት በጀመራቸው የተሃድሶ እርምጃዎች እንዲገፋም ጠይቀዋል ።
« እንደ ወዳጆቻችን እንደ ጀርመኖች ሁሉ እኛም ለግሪክ አዲስ መርሀ ግብር አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን ። የግሪክ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እናደንቃለን ። በተሀድሶውና በምጣኔ ሃብቱ የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለመጠናከር በተያዘው መንገድ እንዲገፋበትም እንጠይቃለን ። »
ሜርክልም የግሉ ዘርፍ በተሃድሶው ሂደት በፈቃደኝነት በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል ። ሁሉቱ መሪዎች በውይይታቸው ማጠቃለያ ስለ ግሪክ አጠቃላይ የፋይናንስ ይዞታ ከ3 ቱ የግሪክ ዓለም ዓቀፍ አበዳሪዎች ማለትም ከአውሮፓ ህብረት ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሙሉ ዘገባ እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል ።
ሂሩት መለሠ
ነጋሽ መሐመድ