1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሩዋንዳ፣ ህዝብ በዘግናኝ ሁኔታ የተጨፈጨፈበት 15ኛ ዓመት ዝካሬ፣

ማክሰኞ፣ መጋቢት 29 2001

የጅምላ ግድያው ከ 15 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበረ የተጀመረው። 800,000 ያህል ህዝብ ፣ በቆንጨራ እየተቆራረጠ፣ በጥይት እየተቆላ፣ መኖሪያ ቤቱ በአሳት እንዲጋኂ እየተደረገ፣ ሲረፈረፍ ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዝም ብሎ ነበረ የተመለከተው።

https://p.dw.com/p/HSF5
ምስል AP

ያኔ ሩዋንዳ ውስጥ፣ ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል ሠፍሮ እንደነበረ ቢታወቅም ፣ እርምጃ እንዲወስድ፣ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት ፈቃድም ሆነ ትእዛዝ ሳይሰጠው በመቅረቱ፣ አረመኔአዊውን ተግባር ዝም ብሎ ነበረ የተመለከተው።

ስለ ሩዋንዳው ጭፍጨፋ መታሰቢያ፣ የዶቸ ቨለ ባልደረባ ዳንኤል Daniel Pelz ያቀረበውን ሐተታ ፣ ተክሌ የኋላ እንደሚከለው አቀናብሮታል።

ሰላም አስከባሪው ኃይል ጭፍጨፋውን መሉ-ለሙሉ መግታት ባይቻለውም እንኳ፣ የብዙ ሰወችን ህይወት መታደግ በቻለ ነበር። ምነው ቢሉ፣ የጅምላ ግድያው ከመጀመሩ 2 ወር ቀደም ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሩዋንዳ ካሠማራቸው ልዩ ተጠሪው Jacques-Roger Boo-Boo እርዳታን የሚማጸን ፣አንድ የማስጠንቀቂያ መልእክት ደርሶት ነበር፣ እንዲህ የሚል----

( የቴሌግራም ድምፅ----)

«ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ ኒው ዮርክ--- ይበልጥ ኃይል የተቀላቀለበት የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ነው። በሌሊት የመድፍ ተኩስ ያጓራል፣ በፖለቲካና በጎሣ ልዩነት ላይ ያተኮረ ግድያ ይካሄዳል። የታጠቁ ኃይሎች፣ በገፍ የሰበሰቡትን ጦር መሣሪያ ለደጋፊዎቻቸው እንደሚያከፋፍሉ የደረሰን አስተማማኝ መረጃ ያስረዳል። ይህ ከቀጠለ፣ የፀጥታው ይዞታ ይበልጥ ይደፈርሳል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችና በሲቭሉ ህዝብ ደህንነት ላይ ከምር አሥጊ ሁኔታ ተደቅኗል።»

ልዩው ተጠሪ ያስተላለፉት መልእክት፣ በሩዋንዳ ፣አስፈሪ ዕልቂትን የሚጋብዝ ሁኔታ መደቀኑን ከሚያመላክቱት መረጃዎች አንዱ ነበረ። እ ጎ አ ከ 1993 ዓ ም ፍጻሜ ገደማ አንስቶ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጦር ሩዋንዳ ውስጥ ሠፍሮ ነበር። በቱትሲዎች ላይ ጥቃት መሠንዘር፣ ለሁቱ አክራሪዎች ጦር መሣሪያ ማከፋፈል፣ ለሚሊሺያ ጦረኞች ምሥጢራዊ ማሠልጠኛ ጣቢያ መገንባት ይህንና የመሳሰለውን መረጃ ሰላም አስከባሪዎቹ ለ ተ,መ, ድ, ያስተላልፉ ነበር። ሌሎችም ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በወቅቱ ታዝበው ነበር፣ ለምሳሌ ያህል፣ የብሪታንያ ተወላጅ የሆኑት ደራሲ ሊንዳ ሜልቨርን እንዲህ ይላሉ።

«የቤልጅግ መንግሥት አደጋ መደቀኑን በማወቅ፣ ግድያ ከመጀመሩ ጥቂት ሳምንታት እንደቀሩት፣ የአሜሪካና የብሪታንያ ዲፕሎማቶች ሰላም አስከባሪውን ኃይል ያጠናክሩ ዘንድ ለምኖ ነበር። አሜሪካና ብሪታንያ ወጪን አሳበው አይሆንም አሉ። የህዝብ ጭፍጨፋ ለማኬሄድ ያቀዱት ክፍሎች ፣ ምንም ቢያደርጉ ዓለም ጣልቃ ገብቶ እንደማያስቆማቸው ይህ ምልክት ነበር ። »

«ክህደት የተፈጸመበት ህዝብ፣ በሩዋንዳው የህዝብ መጨፍጨፍ፣ የምዕራቡ ዓለምድርሻ»(A people Beterayed: The Role of the West in Rwanda Genocide) የጻፉት ደራሲ ሊንዳ ሜልቨርን፣ ያኔ ከሩዋንዳው የህዝብ ጭፍጨፋ አንጻር የምዕራባውያኑን መንግሥታት አቋም የገመገሙ ሲሆን፣ በተቋቋመው ነፈሰ-ገዳዮችን በመረመረው ፍርድ ቤትም በታዛቢነት ሠርትዋል። እ ጎ አ ሚያዝያ 7 ቀን 1994 ዓ ም፣ ከ 15 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት መሆኑ ነው፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጁቬናል ሐብያሪማና አኤሮፕላናቸው በሮኬት ተመትቶ ህይወታቸው ስታልፍ ፣ የሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች፣ የተዘጋጁበትን የጭፍጨፋ እርምጃ ጀመሩ። የተ መ ድ ሰላም አስከባሪዎች እያዩ የአገሪቱ ጠ/ሚንትር ተጎትተው ተወስደው ተገደሉ 3,000 ቱትሲዎች ከሰላም አስከባሪው ፣ የቤልጅግ ባታሊዮን ጦር ወደሠፈረበት በመሸሽ የሙጥኝ አሉ። ከቤልጅግ ወታደሮችም ሲገደሉ ጦሩ አፈገፈገ ። ቱትሲዎቹ ፣ የሚከላከልላቸው ጠፍቶ ብዙም ሳይቆይ፣ በሁቱ ሚሊሺያ ጦረኞች ተጨፈጨፉ።

«ዓለም፣ ያኔ ትኩረቱ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ላይ ነበር። የህዝብ ጭፍጨፋው ሲጀመር፣ የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤትም ሆነ ፣ የምዕራባውያን ጋዜጦች፣ በቦልካን ይዞታ ላይ ነበረ ይበልጥ ያተኮሩት። የሩዋንዳን ጉዳይ ከመጤፍ የቆጠረው አልነበረም። ዓለም አቀፉ የአርዳታ ድርጅት «ኦክስፋም»፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አ ጎ አ ሚያዝያ 29 ቀን 1994 ዓ ም፣ በሩዋንዳ ስለ ህዝብ መጨፍጨፍ ሲያወሳ ፣ አንድም ጋዜጣ በዓምድ ላይ አላሠፈረውም። ፖለቲካውም ፣ ፕረሱም ኀልፊነቱን የተወጣ አልነበረም። »

በመጨረሻም፣ ዓለም አቀፍ ጦር ሩዋንዳ የገባው፣ ጭፍጨፋውን ለማስቆም ሳይሆን፣ ዜጎቻቸውን በአኤሮፕላን ለማስወጣት ነበር። ያኔ ሩዋንዳ ሠፍሮ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኀይል አዛዥ፣ ጭፍጨፋውን ለማስቆም የእርዳታ ያለህ ! በማለት ቢማጸኑም፣ የጸጥታ ጥበቃው ም/ቤት እንዲሁ የግድያ ተመልካች ሆነው እንዲቆዩ ችላ አላቸው። ጦራቸው፣ በውጊያ ተሠማርቶ ጭፍጨፋውን እንዳይገታ ሥልጣን ሳይሰጠው ቀረ። ምዕራባውያን ፖለቲከኞች የህዝብ መጨፍጨፍ የሚል ቃል እንኳ ከአንደበታቸው አይወጣም ነበረ። የያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሩዋንዳውን የህዝብ መጨፍጨፍ ፣ «የጎሣ ውጊያ» ነበረ ያሉት። የ ተ መ ድ፣ የሰላም ተልእኮ ኀላፊ የነበሩትና በኋላ፣ ዋና ጸሐፊ ለመሆን የበቁት፣ ኮፊ አናን፣ ለያኔው ድርጊት ኀላፊነትን በመቀበል ከተጸጸቱት ጥቂት ባለሥልጣናት ውስጥ አንዱ ናቸው።

«በምንም ዓይነት ልንረሳው አይገባም ፣ ሁላችንም ተሳስተናል። 800,000 አባሳ የሌለባቸው ወንዶችና ሴቶችና ህጻናት ከጭፍጨፋ ለማዳን ሳንችል ቀርተናል። የህዝብን መጨፍጨፍ ለመግታት የሚገባንን ያህል ባለማድረገችን ኀላፊነቱን መቀበል አለብን።»

አንዳንድ ታዛቢዎች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፣ ከሩዋንዳው ድቀት አንዳች የቀሰመው ትምህርት የለም በማለት ይነቅፋሉ። በሩዋንዳ የ ተ መ ድ ሰላም አስከባሪ አዛዥ የነበሩት ካናዳዊው ጀኔራል፣ Romeo Dallaire በቅርቡ፣ «ምዕራባውያን መንግሥታትን ከሩዋንዳ ቀጥሎ ህዝብ ሲጨፈጨፍ (የዳርፉሩን ውዝግብ ማለታቸው ነው)ዝም ብለው በመመልከታቸው በደለኞች ናቸው» ብለዋል።

Daniel Pelz/TekleYewhala

Negash Mohammed

►◄